ከቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍስሃ ደስታ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ | ባህል | DW | 18.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

ከቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍስሃ ደስታ ጋር የተደረገ ቃለ-ምልልስ

በአጋጣሚ ምስራቁም ምዕራቡም በነበረበት ጊዜ ነበርኩ። የምስራቁ መሪ በነበረበት ወቅት፤ የምዕራቡ ኮል የነበረ ጊዜ፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌንሸር በነበረበት ጊዜ ሁለቱንም ጀርመኖች ጎብቻለሁ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 18:18

ፕሬዚዳንት መንግሥቱ በጣም ደስ የሚላቸዉ ይመስለኛል

«ወያኔ ኢህአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ እኛን ለእስር ዳረገን። በዚህም እኔ 20 ዓመት ፤ ከአራት ወር ፤ ከስድስት ቀን፤ አስራ አንድ ሰዓት ታስሬ ነዉ የወጣሁት። የኔ ጓደኞቼም እንደዚሁ ታስረዉ ነዉ የወጡት።»

Äthiopien Fisseha Desta (Privatarchiv Fisseha Desta)

ከቀድሞ የምዕራብ ጀርመን የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሃንስ ዲትሬሽጌንሸር ጋር

የኢትዮጵያ የቀድሞ  ምክትል ፕሬዚዳንት ኮነሬል ፍስሃ ደስታ ናቸዉ። ጀርመን በምስራቅና በምዕራብ የከፈላት ግንብ የተገረሰሰበትን 40ኛ ዓመት ስትዘክር፤ የሶሻሊስቱን ርዕዮተ ዓለም ትከተል የነበረዉ የኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ኮነሬል ፍስሃ ደስታ፤ በስልጣን ዘመናቸዉ የዝያን ጊዜዉን የምስራቅ ጀርመን መሪ ሄሪክ ሆኒከርን ከአንዴም ሁለት ሦስት ጊዜ አግኝተዋቸዋል። እንደዉም በዝያን ጊዜ ምስራቅ ጀርመን ተመሳሳይ ርዕዮተ ዓለምን የምታራምድ ወንድም ሃገርን ደጋፊ እንደነበረች ሁሉ ያስታዉሳሉ። ምዕራብ ጀርመንም ብትሆን የኢትዮጵያ ወዳጅ ነበረች። በተለይ በኢትዮጵያ የረሃብ አደጋ ተጋርጦ ሳለ በርካታ ርዳታን የለገሰች ሃገር ነች ሲሉ ኮነሬል ፍስሃ ደስታ፤ ከዝያን ጊዜዎቹ የሁለቱ ጀርመኖች ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የተነስዋቸዉን ፎቶግራፎች ልከዉልናል።

Äthiopien Fisseha Desta (Privatarchiv Fisseha Desta)

ኮነሬል ፍስሃ ደስታ በንጉሱ ዘመን ክብር ዘበኛ ነበሩ

« በአጋጣሚ ምስራቁም ምዕራቡም በነበረበት ጊዜ ነበርኩ። የምስራቁ መሪ ሄሪክ ኦኒከር በነበረበት ወቅት፤ የምዕራቡ ኮል የነበረ ጊዜ፤ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌንሸር በነበረበት ጊዜ ሁለቱንም ጀርመኖች ጎብቻለሁ። ከባለስልጣናቱ ጋርም ብዙ ግንኙነት አድርጌያለሁ። በተለይ በደርግ ዘመነ መንግሥት ድርቅ በነበረበት ወቅት ከፍተኛ ርዳታ ከሚሰጡን ሃገራት መካከል አንዱ ምዕራብ ጀርመን መንግሥት፤ስለነበር ፤ በዝያን ጊዜ ምዕራብ ጀርመንን ጎብኝቻለሁ።  ምስራቅ ጀርመን ከአንዴም ሁለቴ ከሁለቴም ሦስቴ ሄጃለሁ። ከመንግሥቱ ጋር ቅርበት ነበር ። እንደዉም የማስታዉሰዉ በ1969 ዓ.ም ወደ ምስራቅ ጀርመን ለጉብኝት ሄደን ነበር። በወቅቱ የሶማሌ ጦርነት የጀመረበት እና ሚሊሽያዉ ወደ ታጠቅ ጦር ሰፈር የከተተበት ነበር። ሚሊሽያዉ ምንም አይነት የጦር መሳርያ ስላልነበረዉ አንዱን ልዑክ ቡድን ወደ ምስራቅ ጀርመን ይዤ የሄድኩት እኔ ነበርኩ። በዝያን ጊዜ ሆኒከር ነበሩ። ጉዳዩን አስረድቼ ለአንድ ክፍለ ጦር የሚሆን የጦር መሳርያ እና ትጥቅ በራሳቸዉ መርከብ እንዲደርስልን አድርገዋል፤ ስለዚህም ምስራቅ ጀርመኖችም ባለዉለታዎቻችን ነበሩ።  አሁን ከ 30 ዓመት ጀመሮ ሁለቱ ጀርመኖች አንድ መሆናቸዉ ደስ የሚያሰኝ ሲሆን፤ ይበልጥ ይህ የሚያሳየዉ የኤርትራም ሁኔታ አሁን በተያዘዉ ሂደት ፤ አንድ ቀን የምንቀላቀልበት ጊዜ ይመጣል የሚል ተስፋ ያጭርብኛል። »  

የደርግ ዘመነ መንግሥት ከተገረሰሰ በኋላ ከ ሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በእስር የቆዩት ኮነሬል ፍስሃ ደስታ፤ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋባዥነት  ስለ ቀድሞዉ መስርያ ቤታቸዉ፤ የፓርቲ ጽ/ቤታቸዉ ፤ የፖለቲካ እቅድ ማዉጫ የነበረዉን ቦታ ጉብኝተዋል። ኮነሬል ቤተ-መንግሥቱን የሚያዉቁት በጓድ መንግሥቱ ዘመነ ስልጣን ብቻ አይደለም ፤ በጃንሆይ ጊዜም ያዉቁታል፤ ግብር ቤቱን ሁለት ጊዜ በንጉሰነገስቱ ተጋብዘዉበታል።  ኮነሬል ፍስሃ ደስታ ስለአንድነት ፓርክ እንዲህ ያወጉናል።

Äthiopien Fisseha Desta (Privatarchiv Fisseha Desta)

የደርግ ከተገረሰሰና ከ 20 ዓመታት በላይ እስር በኋላ «አብዮቱና ትዝታዬ» የሚል መጽሐፍን አሳትመዋል

«በእዉነት ግብዣዉን አልጠበኩትም ነበር። ጥሪዉ የደረሰኝ ድንገት ነዉ። መስከረም 29 ፤ 2012 ዓም አንድነት ፓርኩ ይመረቃል እና እዛ እንድትገኝ የሚል የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ደረሰኝ፤ በጥሪዉ መሰረት ሄድኩ። ቀደም ሲል ከሃረር ጦር አካዳሚ እንደወጣሁ፤ ክቡር ዘበኛ ተመድቤ ስለነበረ፤ የኛ ክፍል ደግሞ የንጉሰ ነገስቱ የጥበቃ ክፍል ስለነበር፤ ብሔራዊ ቤተ-መንግሥትም፤ ታላቁ ቤተ-መንግሥትም ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በደንብ ነዉ ማዉቃቸዉ። የዛን ቀን በግብዣዉ መሰረት ወደ ቤተ-መንግሥቱ  ሄድን፤ በግብዣዉ ላይ ተጋባዥ የዉጭ እንግዶችም ነበሩ። ጉብኝቱን በአጠቃላይ ለሁለት ከፍለን ያየነዉ እንደሆነ፤ አንደኛ  ቋሚ ቅርሶች ፤ ሁለተኛዉ ደግሞ ፓርኩን ነዉ። ቋሚ ቅርሶች የምንላቸዉ የአፄ ምንሊክ ግቢ እንደመሆኑ፤ የአፄ ምንሊክ መኖርያ ቤት፤ የፊታዉራሪ ኃብተጊዮርጊስ  ቢነግዴ  ማረፍያ ቤት፤ እንዲሁም አፄ ምንሊክ አንዳንድ ጉዳዮችና ችሎቶች የሚያዩባቸዉ የአፄ ምንሊክ የእንቁላል ቤት የሚባለዉ፤ ይሄ በንጉሱ ጊዜ እዛዉ እንዳለ የነበረ ነዉ።  ደርግ ስልጣን ሲይዝ ግን ለተወሰነ ጊዜ የጦር ፍርድ ቤት አድርጎ ተጠቅሞበታል። በመቀጠል ያለዉ ዙፋን ቤት የሚባለዉ ነዉ። በንጉሱ ጊዜ አንዳንድ እንግዶች የሚቀበሉበት ነበር። በደርግ ጊዜ ደግሞ ላዩ የስብሰባ አዳራሽ ሆኖ ከታች ግን ምድር ቤቱ ባለስልጣናት የታሰሩበት ቦታ ነበር። ቀደም ሲል የወይን መጠጦች የሚከማቹበት ግምጃ ቤት ነበር። እዚህ ላይ አንድ ነገር ግልፅ ማድረግ ያለብን እዝያ አስጎብኝዎችም አንዳንድ ጋዜጠኞችም በዚህ ቦታ ሰዉ ይገረፍ ነበር ሰዉ ይገደል ነበር የሚሉት ነገር አለ፤ ይፍ ፈፅሞ ስህተት ነዉ። 

እርግጥ ነዉ ባለስልጣናቱ እዝያ ታስረዋል ግን ምርመራዉ የሚካሄደዉ በመርማሪ ኮሚሽን ከጊቢ ዉጭ ነበር፤ እዝያ ሰዉ የሚገረፍበት የሚገደልበት ቦታ አልነበረም። ስለዚህ ይህ  ፍፁም ሃሰት ነዉ መስተካከል አለበት፤ ታሪክ እንደዚህ ሆኖ ሊቀጥል አይችልም። ይህ የደርግ መሰብሰብያ አዳራሽ ፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት ብዙ ትልልቅ አዋጆች፤ ትልልቅ መሰረታዊ ጉዳዮች ዉሳኔ ያገኙበት ቦታ ነዉ። ከዚህ አዋጅ መካከል መሪትን ለአራሹ ያደረገዉ አዋጅ  የታወጀበት ቦታ ነዉ። ከዚህም በላይ ብሔራዊ አብዮታዊ ዘመቻ መምርያ ተቋቁሞ የሃገሪቱን የመከላከያ ኃይል ይመራበት የነበረ፤ በተለይም የሶማሌ ጦርነት በመቀነስ የዋና ዘመቻ መምርያ ሆኖ ያገለገለ፤ ታሪካዊ ቦታ ነዉ። ቀጥሎ ያለዉ አንድ ሦስት ሽህ ሰዉ የሚይዝ የግብር ቤት ነዉ ይህ የግብር ቤት የተሰራዉ በአፄ ምንሊክ ዘመነ መንግሥት ነዉ። የግብር ቤቱ በጃንሆይ ጊዜም ይሰራ ነበር ንጉሱ በየዓመቱ ሐምሌ 16 ግብር ያስገቡ ነበር። ከዝያ በኋላ ደርግ ስልጣን ላይ ከወጣ በኋላ ፤ በአብዛኛዉ ጊዜ የወታደር ምግብ መመገብያ ቤት ሆኖ ነበር የሚያገለግለግለዉ። ነገር ግን አንድ ጊዜ የማስታዉሰዉ በ1972 ዓም የኢሰፓአኮ የመጀመርያዉ ስብሰባ የተካሄደዉ በዚህ አዳራሽ ነዉ። እንግዲህ እነዚህን ስንጎበኝ ከወደታች ግን ለጉብኝት ያልተፈቀዱልን ቦታዎች ነበሩ።       

ኮነሬል ፍስሃ ደስታ ፤ በሐረር ጦር አካዳሚ ተመርቀዋል፤ በአሜሪካን ሀገር ከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርትን ተከታትለዋል።   በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የ ሕግ ትምህርታቸዉን በመከታተል ላይ ሳሉ አብዮቱ ፈነዳና ከክብር ዘበኛ ተመርጠዉ ደርግን መቀላቀላቸዉን አጫዉተዉናል ። ከኮነሬል ፍስሃ ደስታ ለሰጡን ቃለ ምልልስ በዶይቼ ቬለ ስም በማመስገን ሙሉ ቃለ ምልልሱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ     

Audios and videos on the topic