ከስፖርቱ ዓለም | ስፖርት | DW | 10.06.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ከስፖርቱ ዓለም

ብራዚል ውስጥ በሚቀጥለው የጎርጎሮሳውያኑ 2014 ዓ-ም ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ዙር ለማለፍ ሰንበቱን ከአፍሪቃ እስከ አውሮፓና ላቲን አሜሪካ በርካታ ማጣሪያ ግጥሚያዎች ተካሂደዋል።

በአፍሪቃ ክፍል-ዓለም አይቮሪ ኮስት፣ ኮንጎና ቱኒዚያ ለምድብ ድላቸው ሲቃረቡ ኢትዮጵያም ምድብ-አንድ ውስጥ ቦትሱዋናን በውጭ 2-1 በማሸነፍ በሁለት ነጥቦች ብልጫ አመራሯን እንደያዘች ቀጥላለች። ጎሎቹን በመጀመሪያው አጋማሽ ውስጥ ያስቆጠሩት ጌታነህ ከበደና ሣላዲን ሰይድ ነበሩ።

የምድቡ ሁለተኛ ደቡብ አፍሪቃም ማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክን 3-0 ስትረታ በፊታችን ዕሑድ አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገው ግጥሚያ ወሣኝ ነው። ኢትዮጵያ በዚህ ግጥሚያ ካሸነፈች የምድብ አንደኝነቷን በመጠበቅ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ትችላለች። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከ 31 ዓመታት ቆይታ በኋላ ባለፈው ጥር ለአፍሪቃ ዋንጫ ፍጻሜ ተሳትፎ ሲበቃ አሁን ደግሞ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ላይ እያለመ ነው።

ቡድኑ ከቦትሱዋና የሚመለሰው ዛሬ ማምሻውን ሲሆን አጠቃላይ ሁኔታውን፣ ዝግጅቱንና ተሥፋውን በተመለከተ መሪውን አቶ ብርሃኑ ከበደን በስልክ አነጋግረናል።

ባለፈው ሰንበት በኔዘርላንድ ሄንገሎ ላይ ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር በአምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊው ሙክታር-ኢድሪስ-አወል የኬንያ ተፎካካሪዎቹን አውጉስቲን ቾጌንና ሣይረስ ሩቶን ከኋላው በማስቀረት አሸናፊ ሆኗል። በ 1,500 ሜትር ድሉ የኬንያ ሲሆን መኮንን ገ/መድህን ከኢትዮጵያ ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። በሴቶች አምሥት ሺህ ሜትር ሩጫ አልማዝ አያናና ቡዜ ዲሪባ ከአንድ እስከ ሁለት በመከታተል ቀደምቱ ነበሩ።

ለስዊድን የምትወዳደረው አበባ አረጋዊ ደግሞ በ 800 ሜትር አሸናፊ ሆናለች። በትናንትናው ዕለት በሞሮኮ ራባት ላይ ተካሂዶ በነበረ ዓለምአቀፍ የአትሌቲክስ ውድድርም የኢትዮጵያ አትሌቶች ለተወሰነ ስኬት መብቃታቸው አልቀረም። በወንዶች 800 ሜትር መሐመድ አማን የአሜሪካና የኬንያ ተፎካካሪዎቹን ቀድሞ ሲያሸንፍ በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ደግሞ ጋሪ ሮባ ለሶሥተኝነት በቅቷል።

በአምሥት ሺህ ሜትር የኬንያው ቶማስ ሎንጎሢዋ ሲያሸንፍ ሁለተኛ የወጣው ለባህሬይን የሚወዳደረው አወቀ አያሌው ነበር። የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች ደግሞ በሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ብርቱ ጥንካሬ አሳይተዋል። ሕይወት አያሌው ሩጫውን በአንደኝነት ስትፈጽም እቴነሽ ዲሮም ሶሥተኛ ሆናለች።

በፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ጀርመናዊው የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ የካናዳ ግራንድ-ፕሪ አሸናፊ ሆኗል። ድሉ ለሬድ ቡሉ ዘዋሪ ለዜባስቲያን ፌትል በዘንድሮው የውድድር ሂደት ሶሥተኛው መሆኑ ነው። በዚሁ እሽቅድድም የፌራሪው ፌርናንዶ አሎንሶ ሁለተኛ ሲወጣ የሜርሤዲሱ ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።

የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር አራተኛ፤ የጀርመኑ ኒኮ ሮዝበርግ አምሥተኛ፤ ዣን-ኤሪክ-ቬርኒዬ ከፈረንሣይ ስድሥተኛ! ፌትል ከትናንቱ ድሉ በኋላ በአጠቃላይ 132 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን የስፓኙ ተወላጅ ፌርናንዶ አሎንሶ በ 98 ሁለተኛ ነው፤የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነንም በ 88 በሶሥተኝነት ይከተላል። በቡድንም እንዲሁ ሬድ ቤል፣ ፌራሪና ሜርሴደስ ቀደምቱ ናቸው።

የስፓኙ ራፋኤል ናዳል በፓሪስ-ኦፕን ውድድር ፍጻሜ ትናንት ለስምንተኛ ጊዜ በማሸነፍ አዲስ ክብረ-ወሰን ለማስመዝገብ በቅቷል። ባለፈው ዓመት በጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት የተነሣ ለሰባት ወራት ማረፍ ተገዶ የነበረው ናዳል ለዚህ ታላቅ ድል የበቃው የአገሩን ልጅ ዴቪድ ፌሬርን በአስደናቂ ሁኔታ 6-3,6-2,6-3 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ነው። አንድ ቀን ቀደም ሲል በግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያው የዓለም አንደኛውን የሰርቢያ ኮከብ ኖቫክ ጆኮቪችን ማሸነፉም አይዘነጋም። የ 27 ዓመቱ ናዳል በዚሁ በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ወደ ሁለተኛው ቦታ ከፍ ለማለት ችሏል።

በጥንድ አሸናፊዎቹ አሜሪካውያኑ ወንድማማቾች ቦብና ማይክ ብራያን ነበሩ። በሴቶች ደግሞ ድሉ እንደተጠበቀው የዓለም አንደኛዋ አሜሪካዊት የሤሬና ዊሊያምስ ሆኗል። ሤሬና ለዚህ የፍጻሜ ድል የበቃችው ሩሢያዊቱን ማሪያ ሻራፖቫን በማሸነፍ ነበር። ሻራፖቫ ባለፈው ዓመት የፓሪስ-ኦፕን አሸናፊ እንደነበረች የሚታወስ ነው። በሴቶች ጥንድ ድሉ የሩሢያውያቱ የኤካቴሪና ማካሮቫና የኤሌና ቬስኒና ሆኗል።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic