ከስፖርቱ ዓለም | ስፖርት | DW | 27.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ከስፖርቱ ዓለም

ሰንበቱን በዓለምአቀፉ የስፖርት መድረክ ላይ ከሁሉም የላቀ ትኩረትን ስቦ ያለፈው ሁለት የጀርመን ክለቦች ለመጀመሪያ ጊዜ እርስበርስ የተገናኙበት የአውሮፓ እግር ኳስ ሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ ነበር።

በለንደኑ ዌምብሌይ ስታዲዮም 90 ሺህ ተመልካች በተገኘበት ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በተካሄደው ፍጻሜ ግጥሚያ ባየርን ሙንሺን ዶርትሙንድን 2-1 ሲረታ በጥቅሉ ለአምሥተኛ የአውሮፓ ዋንጫው በቅቷል። በየርን ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ ሁለቴ ለፍጻሜ ደርሶ በኢንተር ሚላንና በቼልሢይ ሲረታ በሶሥተኛ ሙከራው ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ዕድል መልሳ አልከዳችውም። ይህ የቀሰቀሰው ስሜትም ከጨዋታው በኋላ ጎልቶ ነበር የታየው።

መለስ ብለን ካስተዋን በጨዋታው ሂደት በአጠቃላይና በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በመሠረቱ ጠንከር ብሎ የታየው የዋንጫው ባለቤት ባየርን ሣይሆን ዶርትሙንድ ነበር። ሆኖም ቡድኑ በተደጋጋሚ ያገኛቸውን ጥሩ የጎል ዕድሎች ሊጠቀምባቸው ሳይችል ቀርቷል። ጨዋታው እስከ እረፍት ጎል አልባ ሆኖ ሲቆይ በሁለተኛው አጋማሽ ከመጠቃት ወደ ማጥቃት የተሻገረው ባየርን በ 60ኛዋ ደቂቃ ላይ ቀንቶት በክሮኤሺያው ብሄራዊ ቡድን ተጫዋች በማሪዮ ማንጁኪች አማካይነት የመጀመሪያዋን ጎል ያስቆጥራል። ኳሷን ከግራ ክንፍ ግሩም አድርጎ ያቀበለው የኔዘርላንዱ አርየን ሮበን ነበር።

ይሁን እንጂ ዶርትሙንድ 1-0 ቢመራም ጨርሶ መረበሽ አልታየበትም። በተለይም በግሩም አጥቂው በሌቫንዶቭስኪ አማካይነት ከአንዴም ሁለቱ የባየርንን ተከላካዮች እጅጉን ይፈትናል። በዚሁ የማጥቃት ሂደቱም በ68ኛዋ ደቂቃ ላይ ፍጹም ቅጣት ምት ሲያገኝ የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ ጉንዶጋን የባየርንን በረኛ ማኑዌል ኖየርን ወደ ግራ ልኮ በአስተማማኝ ሁኔታ በስተቀኝ ከጎሉ ውስጥ ይከታታል። ውጤቱ በዚህ መልክ መልሶ እኩል ለእኩል ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ብርቱ ትግል በተመላበት አጨዋወት ወሣኟን ሁለተኛ ጎል ለማስቆጠር መጣር ይቀጥላሉ።

የባየርን ሙንሺን ሁለተኛና ወርቃማ የድል ጎል የተቆጠረችው እንግዲህ መደበኛው ጊዜ አብቅቶ ጨዋታው ሊራዘም ነው የሚል ስሜት በተመልካች ዘንድ ባደረባት ወቅት በ 89ኛዋ ደቂቃ ላይ ነበር። አርየን ሮበን በዶርትሙንድ ጎል አጠገብ የተፈጠረውን የተከላካዮች መደናበር ተጠቅሞ ኳሷን በሰከነ ሁኔታ ከመረቡ ይከታታል። ግጥሚያው በዚሁ ሲለይለት ጎል አግቢው አሪየን ሮበን እንደገለጸው ውጤቱ በባየርን ተጫዋቾች ዘንድ የቀሰቀሰው የደስታ ስሜት እንዲህ የሚባል አልነበረም።

ግጥሚያው በጥቅል ሲታይ ላቅ ብለው ለታዩት ለዶርትሙንድ ተጫዋቾችና ለደጋፊዎቻቸው ውጤቱ መሪር ነበር። ዶርትሙንድን ምናልባትም ቀደም ሲል እንደተፈራው የሃያ ዓመት ወጣት የመሃል ሜዳ ተጫዋቹ የማሪዮ ገትሰ ታፋውን ታሞ መቅረት በመጨረሻ ሳይጎዳው አልቀረም። ወጣቱ ተጫዋች ግሩም አከፋፋይ ብቻ ሣይሆን አደገና ጎል አግቢ መሆኑም ይታወቃል። ከዚህ አንጻር መኖሩ ለዶርትሙንድ ምናልባትም በተለይ ቡድኑ ተጠናክሮ በታየበት በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙ በበጀ ነበር።

ያም ሆነ ይህ ለጀርመን የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በጥቅሉ ዋንጫዋ ማንም ያሸንፍ ማን ወደ ጀርመን የምትመጣ በመሆኗ ሰንበቱ የፌስታ ሆኖ ነው ያለፈው። ዓለምአቀፉና የጀርመን ፕሬስ ጨዋታውን በማድነቅ የጀርመን ቡንደስሊጋ በዓለም ላይ አንደኛ ሆኗል ወደ ማለቱ አዘንብለዋል። ይሁን እንጂ ስሜታዊነቱ ቀርቶ ጨዋታው በትክክል ከታየ በአንድ የሻምፒዮና ሊጋ ፍጻሜ ግጥሚያ የሚጠበቀው የቴክኒክና የጥበብ ጥራት የሚገባውን ያህል የሰመረበት ነበር ማለቱ በመጠኑም ቢሆን የሚያዳግት ነው።

እርግጥ የጀርመን ክለቦች የአጨዋወት ስልት የሆነው ፍጥነትና ትግል ግጥሚያውን ለአንድ አፍታ እንኳ አልተለየውም። መሃል ሜዳውን በመቆጣጠር ታክቲክ ከሁለቱም ወገን በታየው አጨዋወት ብዙ የኳስ መነጣጠቅ፤ ማበላሸትና የቅብብል መሰናከል እንዲሁም ጠለፋና ግጭቶች በብዛት ተከስተዋል። ኳስን በመቆጣጠር ቴክኒካዊና ታክቲካዊ ስክነት በሰፈነበት በአጭር ቅብብል ዘይቤ ስልታዊ የማጥቃት አጨዋወት ምናልባትም የቡድኖቹ ባህርይ ሊሆን ይችላል እምብዛም አልነበረም።

ቢሆንም በውድድሩ ግማሽ ፍጻሜ ሃያላኑን የስፓኝ ክለቦች ያሰናበቱት የጀርመን ክለቦች ለፍጻሜ መድረሳቸውና ባየርንም የዋንጫዋ ባለቤት መሆኑ የሚገባው ነው። ክለቦቹ ይህን የዘንድሮውን ጥንካሬያቸውን በመጨው የውድድር ወቅት ጠብቀው ይቀጥሉ ወይም አይቀጥሉ ግን በጊዜው የሚታይ ይሆናል። በነገራችን ላይ የባየርኑ የሻምፒዮና ሊጋ ድል የአሠልጣኙን የዩፕ ሃይንከስን ተፈላጊነትም ከፍ ሊያደርግ በቅቷል። ሬያል ማድሪድ ለተሰናባች አሰልጣኙ ለሆሴ ሞሪኞ ተተኪ የሚፈልግ ሲሆን ሃይንከስ ወኪሉ ትናንት እንዳስታወቀው ለዚሁ ዝግጁ ነው።

በተቀረ በሌሎች የአውሮፓ ሊጋዎች በተካሄዱ ጠቃሚ ግጥሚያዎች በኢጣሊያ ላሢዮ የከተማ ተፎካካሪውን ኤ ኤስ ሮማን በስታዲዮ ኦሊምፒኮ 1-0 በመርታት ትናንት ለስድሥተኛ ጊዜ የኢጣሊያ ፌደሬሺን ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። የዋንጫው ድል ላሢዮን በመጪው የውድድር ወቅት ለአውሮፓ ሊግ ተሳትፎም የሚያበቃ ነው። በፖርቱጋል ዋንጫ ደግሞ ቪክቶሪያ ጊማሬሽ ከኋላ ተነስቶ ቤንፊካን 2-1 በመርታት ላልተጠበቀ ድል በቅቷል።

ለቤንፊካ ሽንፈቱ ከአውሮፓ ሊግ ፍጻሜና ከፖርቱጋል ሻምፒዮና ሌላ ሶሥተኛው ሲሆን ለሊዝበኑ ክለብ እጅጉን መሪር ነው። በስኮትላንድ ዋንጫ ደግሞ ሤልቲክ ግላስጎው ለ 36ኛ ጊዜ አሸናፊ ሲሆን በፍጹም ቅጣት ምት በለየለት የስዊድን ዋንጫ ፍጻሜም ጎተቦርግ ቀንቶታል። በተረፈ የአውሮፓው ሊጋዎች ውድድር በመጠናቀቅ ላይ ሳለ የስፓኙ ክለብ ባርሤሎና ራሱን በብራዚሉ ብሄራዊ ተጫዋች በኔይማር እንደሚያጠናክር ታውቋል። የ 21 ዓመቱ ኮከብ በዛሬው ዕለት ውል እንደሚፈርም ይጠበቃል።

የስፓኙ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን በሌላ በኩል ከሌላው የላቲን አሜሪካ ኮከብ ከራዳሜል ፋልካኦ ሳይሰናበትም አይቀርም። አትሌቲኮ ማድሪድን በበርካታ ጎሎቹ ለሊጋ ሶሥተኝነትና ለብሄራዊ ዋንጫ ያበቃው የኮሉምቢያ ኮከብ ወደ ሞናኮ ሊሻገር መቻሉ እየተነገረ ነው። አትሌቲኮ ለዚህ ድንቅ ተጫዋች ተተኪ ማግኘቱ ቀላል የሚሆንለት አይመስልም።

ሰንበቱን ኒውዮርክ ላይ ተካሂዶ በነበረው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር በአጭር ርቀት በወንዶችና በሴቶች የአሜሪካና የጃሜይካ አትሌቶች አይለው ሲታዩ በመካከለኛ ርቀት ደግሞ የኢትዮጵያና የኬንያ ተወዳዳሪዎች ግሩም ውጤት አስመዝግበዋል። በወንዶች አንድ መቶ ሜትር አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ ሲያሸንፍ በሁለት መቶ ሜትር የጃሜይካው ዎረን ዋይር ቀደምቱ ሆኗል። በአራት መቶ ሜትርና በአራት መቶ መሰናክል ድሉ የአሜሪካውያኑ የዮሹዋ ማንስና የማይክል ቲንስሊይ ነበር።

በስምንት መቶ ሜትር ኬንያዊው የዓለም ሻምፒዮን ዴቪድ ሩዲሻ ሲያሸንፍ በአምሥት ሺህ ሜትር ደግሞ ሃጎስ ገ/ሕይወት ቀዳሚ ሆኗል። በሴቶች አንድ መቶና ሁለት መቶ ሜትር ያሸነፉት የጀሜይካ አትሌቶች ናቸው። በሴቶች ሶሥት ሺህ ሜትር መሰናክል ኬንያዊቱ ሉዲያ ቼፕኩሩዊ ስታሸንፍ እቴነሽ ዲሮና ሶፊያ አሰፋ ሁለተኛና ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። በ 1,500 ሜትር ደግሞ ለስዊድን የምትወዳደረው የቀድሞ የኢትዮጵያ አትሌት አበባ አረጋዊ አንደኛ ወጥታለች።

ከዚሁ ሌላ በኦታዋ ማራቶን ትናንት የኢትዮጵያ አትሌቶች ድርብ ድል ተጎናጽፈዋል። በወንዶች ታሪኩ ጁፋር አሸናፊ ሲሆን ኬንያዊው ሉካ ሮቲች ሁለተኛ፤ እንዲሁም ሌላው የኢትዮጵያ ተወዳዳሪ ጋሻው መለሰ ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። አንድ የኢትዮጵያ አትሌት በኦታዋው ማራቶን ለድል ሲበቃ የትናንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነበር። በሴቶች ያሸነፈችው ደግሞ የሺ ኢሣኢያስ ነበረች። በዚህ በአውሮፓ በታላቁ የማንቼስተር ሩጫም በአሥር ኪሎሜትር ውድድር ጥሩነሽ ዲባባ ትናንት አንደኛ ወጥታለች። በወንዶች የኡጋንዳው ሞሰስ ኪፕሢሮ አሸናፊ ሆኗል።

ቪንቼንሶ ኒባሊ በትናንትናው ዕለት የዘንድሮው ጂሮ-ዲ-ኢታሊያ የቢስክሌት እሽቅድድም አሸናፊ ሆናል። ኒባሊ በ 2010 እና 2011 ሶስተኛ ሲወጣ የዘንድሮው የመጀሪያው የጂሮ አጠቃላይ ድሉ መሆኑ ነው። የኢጣሊያው ተወላጅ ባለፈው ዓመት በቱር-ዴ-ፍራንስ ሶሥተኛ መሆኑም ይታወሳል። ትናንት ብሬሺያ ላይ በተጠናቀቀው በ 21ኛውና በመጨረሻው ደረጃ እሽቅድድም ቀዳሚ የሆነው ደግሞ የብሪታኒያው ማርክ ካቨንዲሽ ነበር። በዓለም የመንገድ የቢስክሌት እሽቅድድም አጠቃላይ ነጥብ የስዊሱ ፋቢያን ካንቼላራ በአንደኝነት የሚመራ ሲሆን ቪንቼንሶ ኒባሊ ሁለተኛና የስሎቫኪያው ፔተር ሣጋን ሶሥተኛ ሆነው ይከተላሉ።

በትናንትናው ዕለት ሞናኮ ላይ ተካሂዶ በነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም ሁለት የጀርመን ተወዳዳሪዎች ግንባር ቀደም ለመሆን ችለዋል። ኒኮ ሮዝበርግ በእሽቅድድሙ አሸናፊ ሲሆን ሁለተኛ የወጣው ያለፉት ዓመታት የዓለም ሻምፒዮን ዜባስቲያን ፌትል ነው። የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ሶሥተኛ ሲወጣ የእንግሊዙ ሉዊስ ሃሚልተንም እሽቅድድሙን በአራተኝነት ፈጽሟል።

መሥፍን መኮንን

Audios and videos on the topic