ከስፖርቱ ዓለም | ስፖርት | DW | 13.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ከስፖርቱ ዓለም

ባለፈው ሣምንት መጨረሻ የመጀመሪያው የአትሌቲክስ ዳያመንድ ሊግ ውድድር ዶሃ ላይ ሲከፈት በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ክለቦች ውድድር ደግሞ ባርሤሎናና ፓሪስ ሣንት ዠርማን በየፊናቸው የየሊጋቸው ሻምፒዮን ለመሆን በቅተዋል።

በቅድሚያ ለዘንድሮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዓመት መክፈቻ በሆነው ባለፈው አርብ የዶሃ ዓለምአቀፍ ውድድር ላይ እናተኩርና ምሽቱ 11 አትሌቶች የዓመቱን ግሩም ውጤት ያስመዘገቡበት ሆኖ ነው ያለፈው።

ኬንያዊው የ 800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን ዴቪድ ሩዲሻ ሩጫውን በ 1 ደቂቃ ከ 43,87 ሤኮንድ ጊዜ በመፈጸም ሲያሸንፍ የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ መሐመድ አማን ሁለተኛ ወጥቷል። በሶሥተኝነት ከግቡ የደረሰው ደግሞ ሌላው ኬንያዊ ጆብ ኪኞር ነበር። ሩዲሻ በለንደኑ ኦሎምፒክ የራሱን ክብረ-ወሰን በማሻሻል የ 1 ደቂቃ ከ 40,91 ሤኮንድ ጊዜ ማስመዝገቡ ይታወሳል።

ኬንያዊው አትሌት ዶሃ ላይ ያንን ጊዜ ባይደግመውም የሮጠው የዓመቱን ፈጣን ሰዓት እንደሆነ በማመልከት በሚቀጥሉት ሣምንታት ውስጥ የተሻለ ውጤት አመጣለሁ ብሏል። በነገራችን ላይ ዴቪድ ሩዲሻ ባለፉት ሶሥት ዓመታት ውስጥ የተሸነፈው በመሐመድ አማን ብቻ ነው። በ 100 ሜትር ሩጫ አሜሪካዊው የ 2004 ዓ-ም የኦሎምፒክ ሻምፒዮን ጀስቲን ጋቲን እንዳለፈው ዓመት ሁሉ አሸናፊ ሆኗል።

አካል አጎልባች መድሃኒት በመውስድ ለአራት ዓመታት ከታገደ በኋላ ወደ ውድድሩ የተመለሰው የ 31 ዓመት አትሌት ሩጫውን በ9,97 ሤኮንድ ጊዜ ሲፈጽም ሌላው አሜሪካዊ ተወዳዳሪ ማይክል ሮጀርስ ሁለተኛ እንዲሁም የጃማይካው ኔስታ ኮሊንስ ሶሥተኛ ሆኗል። እርግጥ የለንደኑ ኦሎምፒክ የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ ጋቲን ያሸነፈው የጃሜይካ የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮኖች ዩሤይን ቦልትና ዮሃን ብሌክ በሌሉበት ነው።

1500 Meter Finale Weltmeisterschaften Leichtathletik 2011

በ 1,500 ሜትር ኬንያውያኑ አስቤል ኪፕሮፕና ቤትዌል ቢርገን ተከታትለው ሲያሸንፉ የኢትዮጵያው ተወዳዳሪ አማን ወቴ ሩጫውን በሰባተኝነት ፈጽሟል። በ 3000 ሜትር ሩጫ ኢትዮጵያዊው ሃጎስ ገ/ሕይወት ግሩም በሆነ ሁኔታ በማሸነፍ 19ኛ ዓመት ልደቱን በድል ለማክበር በቅቷል። የወጣቶች የዓለም ሻምፒዮን የሆነው ሃጎስ የአራት ጊዜው የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የቀነኒሣ በቀለ ሁነኛ ተተኪ ለመሆን እንደሚችል ታዛቢዎች እየተናገሩለት ነው።

በዚሁ ሩጫ ኬንያዊው ቶማስ ሎንጎዚዋ ሁለተኛ ሲወጣ የኔው አላምረው ሩጫውን በሶሥተኝነት ፈጽሟል። ኤርትራዊው አብራር አደምም ስምንተኛ ሆኗል። በሴቶች የለንደን ኦሎምፒክ የ 100, 200ና የ4x100 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረችው አሜሪካዊት አሊስን ፌሊክስ በአራት መቶ ሜትር ሩጫ በቦትሱዋናዋ የዓለም ሻምፒዮን በአማንትሌ ሞንቾ ስትሸነፍ በሴቶች 1,500 ሜትር ሩጫ ደግሞ የስዊድኗ ተወዳዳሪ አበባ አረጋዊ አንደኛ ሆናለች።

ኬንያዊቱ ፌይት ኪፕየጎን ሁለተኛ ስትወጣ ገንዘቤ ዲባባም ሶሥተኛ ሆናለች። የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶች በተለይ በ 3000 ሜትር መሰናክል ቀደምቱ ባይሆኑም ብርቱ ጥንካሬ ለማሣየት በቅተዋል። ድሉ የኬንያ ቢሆንም ሶፊያ አሰፋ፣ ሕይወት አያሌውና እቴነሽ ነዳ ከሁለት እስከ አራት በመከታተል ድንቅ ውጤት ነው ያስመዘገቡት። ባለፈው ቅዳሜ ጃሜይካ-ኪንግስተን ላይ ተካሂዶ በነበረ የአትሌቲክስ ውድድር ደግሞ አሜሪካዊው ታይሰን ጌይ በ 100 ሜትር ሩጫ ድንቅ በሆነ 9,86 ሤኮንድ ጊዜ ለማሸነፍ በቅቷል።

ጌይ ሩጫውን ከአሥር ሤኮንድ በታች በሆነ ጊዜ በማሸነፍ በዚህ ዓመት የመጀመሪያው ሲሆን ውጤቱ በፊታችን ነሐሴ ወር ሞስኮ ላይ ለሚካሄደው የአትሌቲክስ የዓለም ሻምፒዮና ተፎካካሪዎቹን የሚቀሰቅስ ነው። በሴቶች መቶ ሜትር በለንደን ኦሎምፒክ የናስ ሜዳሊያ ተሸላሚ የነበረችው ጃሜይካዊት ቬሮኒካ-ካምፕቤል-ብራውን አሸናፊ ስትሆን በ 200 ሜትር አሊሰን ፌሊክስ በአምሥተኝነት ተወስና ቀርታለች። በ 110 ሜትር መሰናክል ድሉ በወንዶችና በሴቶችም የአሜሪካ ሆኗል።

በትናንትናው ዕለት ቼክ ሬፑብሊክ ውስጥ ተካሂዶ በነበረ የፕራግ ማራቶን ሩጫ ኬንያውያን አይለው ታይተዋል። በወንዶች ከኬንያ የመነጨው የካታር ተወዳዳሪ ኒኮላስ ኬምቦይ ሲያሸንፍየኢትዮጵያው ግርማይ ብርሃኑ ሁለተኛ ወጥቷል። የኬንያው ተወዳዳሪ ፓትሪክ ቴሬር ሶሥተኛ ሲሆን ተሾመ ገላና ደግሞ ውድድሩን በአሥረኝነት ለመፈጸም በቅቷል። በሴቶች ሁለቱ የኬንያ አትሌቶች ካሮሊን ሮቲችና ፊልስ ኦንጎሪ ቀዳሚ ሲሆኑ እሕቱ ኪሮስ ከኢትዮጵያ ደግሞ ሶሥተኛ ወጥታለች።

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ባርሤሎናና ፓሪስ ሣንት ዠርማን ባለፈው ሰንበት ሻምፒዮንነታቸውን ለማረጋገጥ በቅተዋል። ለባርሤሎና ሻምፒዮናው በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ውስጥ 22ኛው ሲሆን ባለፉት አምሥት ዓመታትም አራተኛው ነው። ባርሣ ድሉን ከውድድሩ ፍጻሜ ቀድሞ ያረጋገጠው አትሌቲኮ ማድሪድን 2-1 በማሸነፉና ሁለተኛው ሬያል ማድሪድም ከኤስፓኞል 1-1 በሆነ ውጤት በመወሰኑ ነበር። የሬያሉ አሰልጣኝ ሆሴ ሞሪኞ ከሰንበቱ ጨዋታ ይልቅ በፊታችን አርብ ከአትሌቲኮ ጋር በሚካሄደው ኪንግስ ካፕ ፍጻሜ ግጥሚያ ላይ ይበልጥ ያተኮሩ ነው የሚመስለው።

ያለፈውን ዓመት ሻምፒዮንነቱን መድገም ለተሳነው ለሬያል ማድሪድ በዕውነትም በዘንድሮው ውድድር ወቅት የሚቀረው ብቸኛ የዋንጫ ዕድል ይሄው መጪው ግጥሚያ ይሆናል። ባርሤሎና ውድድሩ ሊያበቃ ሶሥት ግጥሚያዎች ቀርተውት 91 ነጥቦች ሲኖሩት ሬያልን የሚያስከትለው በአሥር ነጥቦች ልዩነት ነው። አትሌቲኮ ማድሪድ 81 ነጥቦች ካሉት ከሬያል በዘጠኝ ዝቅ ብሎ ሶሥተኛ ሲሆን በጎል አግቢነት ሊዮኔል ሜሢ 46 አስቆጥሮ በማይደረስበት ሁኔታ ይመራል።

በፈረንሣይም ፓሪስ ሣንት ዠርማን ውድድሩ ሊጠናቀቅ ገና ሁለት ጨዋታዎች ቀርተው ሳለ በሰባት ነጥቦች ብልጫ ሻምፒዮንነቱን አረጋግጧል። የፓሪሱ ክለብ ሶሥተኛውን ኦላምፒክ ሊዮንን 1-0 ሲረታ መልሶ ለሻምፒዮንነት የበቃውም ከ 19 ዓመታት በኋላ ነው። ቡድኑ ታላቅ ድሉን በማክበር ላይ ባለበት ወቅት ይሁንና ኢጣሊያዊ አሠልጣኙ ካርሎ አንኼሎቲ ይቆዩ አይቆዩ ገና እርግጠኛ ነገር አይደለም። አንኼሎቲ ምናልባትም ሆሴ ሞሪኞን በመተካት ወደ ሬያል ማድሪድ የመሻገራቸው ወሬ ሣምንቱን ሲናፈስ ነው የከረመው። ከሚላን ጋር ሁለት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ የዋንጫ ባለቤት የነበሩት የካርሎ አንኼሎቲ ተፈላጊነት ከፍተኛ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሻምፒዮናው ቀድሞ የለየለት ጉዳይ ሲሆን ሰንበቱን ዋናው ማተኮሪያ የፌደሬሺኑ ዋንጫ የ FA CUP ፍጻሜ ግጥሚያ ነበር። በዚህም ግጥሚያ በፌደሬሺን ዋንጫ ውድድሮች እንደተለመደው ዳዊት ጎልያድን ማሸነፉ እንደገና ዕውን ሆኗል። በሚሊዮኖች የሚቆጠር መዓት ገንዘብ አፍሶ ከዋክብትን ያሰባሰበው ቀደምት ክለብ ማንቼስተር ሢቲይ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን እንይከለስ በመንገዳገድ ላይ በሚገኘው አነስተኛ ቡድን በዊጋን አትሌቲክ 1-0 ተረትቶ ዋንጫውን ያስረክባል ብሎ የጠበቀ ብዙ አልነበረም።

በሌላ በኩል በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ማንቼስተር ዩናይትድ በዘንድሮው ውድድር በሜዳው የመጨረሻ በሆነ ግጥሚያው ስዋንሢይ ሢቲይን 2-1 በመርታት ከ 26 ዓመታት በኋላ ለሚለዩትዝነኛ አሠልጣኙ ለሰር አሌክስ ፈርጊሰን የክብር ስንብት አድርጓል። በፕሬሚየር ሊጉ ውድድር ማንቼስተር ሢቲይ ሁለተኛና ቼልሢይም ሶሥተኛ ሲሆን ፍራንክ ላምፓርድ ቼልሢይ ከኤስተን ቪላ ባደረገው ግጥሚያ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር በጠቅላላው በ 203 ግቦች በክለቡ ታሪክ ግንባር ቀደሙ ሆኗል።

በጀርመን ቡንደስሊጋ በሁለት ሣምንት ጊዜ ውስጥ በዌምብሊይ ስታዲዮም በንጹህ የጀርመን ክለቦች ፍጻሜ ከዶርትሙንድ በሚያደርገው ግጥሚያ የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋን ለመጠቅለል በመጠባበቅ ላይ የሚገኘው ባየርን ሙንሺን ባለፈው ሰንበት አውግስቡርግን 3-0 በመርታት ቀድሞ ያረጋገጠውን የጀርመን ሻምፒዮና በይፋ አክብሯል። ቡድኑ ከቡንደስሊጋው ባሻገር በአውሮፓና በጀርመን ፌደሬሺን ዋንጫም ገና ሁለት የድል ዕድሎች ሲቀሩት ሶሥቱንም ከጠቀለለ ታሪካዊ ነው የሚሆነው።

በሌላ በኩል ዶርትሙንድ ከቮልፍስቡርግ 3-3 ሲለያይ ትኩረቱ ይበልጡን በመጪው የዌምብሌይ ግጥሚያ ላይ ያለመ ነው የሚመስለው። በተቀረ ዘንድሮ ፈተና ገጥሞት የቆየው የቀድሞ ጠንካራ ክለብ ብሬመን ከፍራንክፉርት 1-1 በመለያየት ከመከለስ አደጋ ሲያመልጥ በአንጻሩ ከርሱ በታች የሆኑት የዱስልዶርፍ፣ የአውግስቡርግና የሆፈንሃይም ዕጣ የሚለይለት በፊታችን ሰንበት የመጨረሻ ግጥሚያዎች ነው።

ኦሎምፒያኮስ ፒሬውስ በግሪክ ዋንጫ አስቴራስ ትሪፖሊስን ከተጨማሪ ሰዓት በኋላ 3-1 በማሸነፍ በክለቡ ታሪክ ውስጥ ለ 26ኛ ጊዜ የብሄራዊው ዋንጫ ባለድል ሆኗል። ክለቡ በቅርቡ የሊጋው ሻምፒዮን መሆኑም ይታወሳል። በፖርቱጋል ሻምፒዮናው ሊጠቃለል አንድ ግጥሚያ ብቻ ቀርቶ ሳለ ሰንበቱን በሁለቱ ቀደምት ክለቦች መካከል በተደረገው ግጥሚያ ፖርቶ ቤንፊካን 2-1 ረትቶ በመጨረሻዋ ሰዓት አመራሩን ነጥቋል።

ፖርቶ ከሰንበቱ ግጥሚያ ወዲህ በአንዲት ነጥብ ብልጫ እየመራ ሲሆን ለተከታታይ ሶሥተኛ ሻምፒዮንነቱ የተቃረበ ነው የሚመስለው። አብዛኛውን ጊዜ ቁንጮ ሆኖ የቆየው ቤንፊካ ሊዝበን በመጨረሻዋ ደቂቃ ዋንጫዋን ካጣ የደጋፊዎቹ ሃዘን ቀላል የሚሆን አይመስልም። ለማንኛውም በፊታችን ሰንበት የመጨረሻ ግጥሚያ ፖርቶ ከሶሥተኛው ክለብ ከፓኮስ በውጭ የሚጫወት ሲሆን ቤንፊካ ደግሞ 15ኛውን ሞሬይሬይዜን በሜዳው ያስተናግዳል።

በትናንትናው ዕለት ባርሤሎና ላይ ተካሂዶ የነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ የስፓኙ ተወላጅ ፌርናንዶ አሎንሶ ሆኗል። የፌራሪው ዘዋሪ በስፓኝ ግራንድ-ፕሪ ሲያሸንፍ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በእሽቅድድሙ የፊንላንዱ ኪሚ ራይኮነን ሁለተኛ ሲወጣ የብራዚሉ ፌሊፔ ማሣም ለሶሥተኝነት በቅቷል። ያለፉት ዓመታት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል በአንጻሩ ከአራተኝነት ሊያልፍ አልቻለም።

የአውስትራሊያው ማርክ ዌበር ፌትልን ተከትሎ አምሥተኛ ሲሆን የብሪታኒያው ዘዋሪ ሉዊስ ሃሚልተን ወደ ኋላ በመቅረት 12ኛ ወጥቷል። በጠቅላላው ከሚደረጉት 19 እሽቅድድሞች አምሥቱ ካለፉ በኋላ አሁን ዜባስቲያን ፌትል በ 89 ነጥቦች የሚመራ ሲሆን ራይኮነን በ 85 ሁለተኛ ነው፤ አሎንሶ ደግሞ በ 72 ይከተላል።

ትናንት በተጠናቀቀው የማድሪድ ማስተርስና የማድሪድ-ኦፕን ፍጻሜ የስፓኙ ራፋኤል ናዳልና አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ በፍጹም ልዕልና ለድል በቅተዋል። ናዳል የስዊሱን ስታኒስላቭ ቫብሪንካን በለየለት 6-2,6-4 ውጤት ሲያሸንፍ ይህም ሶሥተኛው የማድሪድ ድሉ ይሆናል። ራፋኤል ናዳል በአካል ጉዳት ለሰባት ወራት አርፎ ከተመለሰ በኋላ በዚህ በያዝነው ዓመት አምሥተኛ ድሉን ማክበሩም ነው።

በሴቶች አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ የሩሢያ ተጋጣሚዋን ማሪያ ሻራፖቫን በተመሳሳይ ሁኔታ 6-1,6-4 አሸንፋለች። ሁለቱ ባለድሎች አሁን የሚያተኩሩት በመጪው የፍሬንች-ኦፕን ላይ ነው።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic