ከስፖርቱ ዓለም | ስፖርት | DW | 07.01.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ከስፖርቱ ዓለም

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው 29ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀሩት በትክክል 12 ቀናት ብቻ ናቸው።

ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ የሚካሄደው 29ኛው የአፍሪቃ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት የቀሩት በትክክል 12 ቀናት ብቻ ናቸው። ጨዋታው የሚጀመረውም በፊታችን ጥር 11 ቀን ጆሃንስበርግ ላይ በአስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃና በካፕ-ቬርዴ መካከል በሚካሄድ የምድብ-አንድ መክፈቻ ግጥሚያ ይሆናል። የዘንድሮው ውድድር በተለይም ከ 31 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተሳትፎ ለበቃችው ለኢትዮጵያና ለእግር ኳስ አፍቃሪዎቿ የተለየ ክብደት ነው ያለው።

ኢትዮጵያ በአፍሪቃ የእግር ኳስ መድረክ ላይ ወደ ቀድሞ ገናና ቦታዋ የመመለሷ ተሥፋ በተለይ ብሄራዊው ቡድን ሱዳንን 2-0 ረትቶ ለፍጻሜው ከደረሰ ወዲህ በሰፊው በመንጸባረቅ ላይ ነው የሚገኘው። የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ምንም እንኳ በምድብ-ሶሥት ከዛምቢያ፣ ከናይጄሪያና ከቡርኪና ፋሶ የመወዳደር ከባድ ዕጣ ቢገጥመውም ቢቀር ከሩብ ፍጻሜ የመድረስ ግብ ይዞ ወደ ውድድሩ እንደሚያመራ ነው አሠልጣኝ ስዩም ከበደ የሚናገሩት።

ለዚህም ቡድኑ በትጋት በመዘጋጀት ላይ ሲሆን በዛሬው ዕለት ዶሃ ላይ ከቱኒዚያ ጋር የአቅም ፍተሻ ግጥሚያ ያካሂዳል። 23 ተጫዋቾችን ያቀፈው ብሄራዊ ቡድን በፊታችን ረቡዕ ደግሞ አዲስ አበባ ላይ ምናልባትም ከታንዛኒያ ከገጠመ በኋላ ወደ ደቡብ አፍሪቃ እንደሚያመራ ነው የሚጠበቀው። የምድብ-ሶሥት ግጥሚያ ጥር 13 ቀን የሚከፈት ሲሆን የኢትዮጵያ የመጀመሪያ ተጋጣሚ የዋንጫ ባለቤት የሆነችው ዛምቢያ ናት። እርግጥ ፈተናው ከባድ ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በሙሉ ልብ ነው ለዚህ ግጥሚያ እየተዘጋጀ ያለው።

በሌላ በኩል ዛምቢያ ባለፈው ቅዳሜ ከአንጎላ ጋር ባደረገችው የወዳጅነት ግጥሚያ 2-0 በመረታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለተከታታይ ሶሥተኛ ሽንፈት በቅታለች። መለስ ብሎ ለማስታወስ ዛምቢያ ባለፈው ወር በሳውዲት አረቢያና በታንዛኒያም ተሸንፋ ነበር። ታዲያ ድክመቷ የሚቀጥል ከሆነ ለኢትዮጵያ እሰዬ በሆነ። ነገር ግን ልምድ የሚያሳየው ሌላ ነው።

ዛምቢያ ያለፈውን የአፍሪቃን ዋንጫ ለመውስድ ከመብቃቷ በፊትም ደካማ የዝግጅት ጊዜ ማሳለፏ ይታወሳል። እናም ቡድኑ አይቮሪ ኮስትን ያህል ታላቅ ቡድን በፍጹም ቅጣት ምትም ቢሆን በፍጻሜው አሸንፎ ለመጀመሪያ ጊዜ ለዋንጫ መብቃቱ እጅግ ያስደነቀ ነበር። ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለስኬት የማይበቃበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ጨርሶ ዕድል አልባ አይደለም።

በሌላ በኩል አይቮሪ ኮስትንና ጋናን ለመሳሰሉት ሃገራት ግቡ ከፍጻሜ ደርሶ ዋንጫ መውሰድ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም። በተለይም በታዋቂ አምበሉ በዲዲየር ድሮግባ የሚመራው የአይቮሪ ኮስት ብሄራዊ ቡድን ለተከታታይ አምሥተኛ ጊዜ ትልቅ የዋንጫ ባለቤትነት ዕድል ነው የሚሰጠው። ቡድኑ ቀደም ሲል በግብጽ፣ በጋና፣ በአንጎላ፤ እንዲሁም በጋቦንና ኤኩዋቶሪያል ጊኒ የጋራ መስተንግዶ ያልሰመረለትን ዘንድሮ ማሳካት ይጠበቅበታል። በፍጹም ቅጣት ምት በለየላቸው ግጥሚያዎች ሁለቴ ለጥቂት ዋንጫው ያመለጣት አይቮሪ ኮስት እርግጥ ከዚህ አንጻር ከባድ ግፊት ነው ያለባት።

ለማስታወስ ያህል አይቮሪ ኮስት ለመጨረሻ ጊዜ ጋናን አሸንፋ የዋንጫ ባለቤት የሆነችው ከ 21 ዓመታት በፊት ነበር። እንግዲህ አሁን ድሮግባን፣ ኮሎንና ያያ ቱሬን የመሳሰሉትን «ወርቃማ ትውልድ» የሚል ቅጽል ስያሜ የተሰጣቸው ድንቅ ተጫዋቾች ያቀፈ ቡድን ታሪክ ሰርቶ የማለፍ የመጨረሻ ዕድሉን መጠቀም ይኖርበታል። በተረፈ አልጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ዛምቢያ፣ አንጎላ፣ ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክ ኮንጎ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያና አስተናጋጇ ደቡብ አፍሪቃም እስከ ፍጻሜው ሊዘልቁ የሚችሉ ናቸው።

የሶሥተኛው የአፍሪቃ ዋንጫ ባለቤት የኢትዮጵያ ጉዞ ደግሞ እስከየት እንደሚሆን ጠብቆ መታዘቡ ግድ ነው። ሣምንት በዚሁ በደቡብ አፍሪቃው የአፍሪቃ ዋንጫ ውድድርና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዕጣ ላይ ሰፊ ዝግጅትይኖረናል።

አትሌቲክስ

ባለፈው ቅዳሜ ቻይና ውስጥ ተካሄዶ የነበረው የአዲሱ 2013 ዓ-ም የሢያሜን ዓለምአቀፍ ማራቶን ሩጫ ውድድር የኢትዮጵያ አትሌቶች ድል የገነነበት ሆኖ አልፏል። በጠረፍ ከተማይቱ ሢያሜን በተካሄደው ውድድር በወንዶች ጌታቸው ተርፋ ሲያሸንፍ ፓውል ኪፕቹምባ ከኬንያ ሁለተኛ ወጥቷል። ሩጫውን በሶሥተኝነትና በአራተኝነት የፈጸሙት ኢትዮጵያውናኑ ሣህሌ ዋርጋና ገ/ጻዲቅ አብራሃ ነበሩ። ኬንያዊው ፒተር ሎታጎር ደግሞ አምሥተኛ ሆኗል።

የሢያሜን ዓለምአቀፍ ማራቶን በሴቶችም የኢትዮጵያ ድል የሰመረበት ነበር። ፋጡማ ሣዶ አንደኛ ሆናለች። ኬንያዊቱ ኦይኒስ ጄፕኪሩዊ ሁለተኛ ስትወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመችው ኢየሩሣሌም ኩማ ናት። የቻይና ተወዳዳሪ ዋንግ ቹኪን አራተኛ ስትወጣ ወርቅነሽ ቶላም ሩጫውን በአምሥተኝነት ፈጽማለች።

የአውሮፓ እግር ኳስ ሊጋዎች

በአውሮፓ ቀደምት የእግር ኳስ ሊጋዎች ሻምፒዮና የጀርመን ቡንደስሊጋ ከለቦች የክረምት እረፍታቸውን አብቅተው ሞቃታማ በሆኑ አካባቢዎች ልምምድ ሲጀምሩ በስፓኝ፣ በኢጣሊያ፣ በእንግሊዝና በፈረንሣይ ግን ውድድሩ ቀጥሏል። በስፓኝ ፕሪሜራ ዲቪዚዮን ቀደምቱ ባርሤሎና የከተማ ተፎካካሪውን ኤስፓኞልን 4-0 በመሸኘት አመራሩን ከዘጠኝ ወደ 11 ነጥቦች ሊያሰፋ በቅቷል። ለዚህም ምክንያት የሆነው የሁለተኛው የአትሌቲኮ ማድሪድ ከማዮርካ 1-1 በሆነ ውጤት መወሰን ነው።

ለባርሣ ጎሎቹን ያስቆጠሩት ፔድሮ፣ ሻቪና ሊዮኔል ሜሢ ነበሩ። ሶሥተኛው ሬያል ማድሪድ በበኩሉ ግጥሚያ ሬያል ሶሢየዳድን 4-3 ሲያሸንፍ አትሌቲኮን እስከ አምሥት ነጥብ ልዩነት ሊቃረብ ችሏል። ከአንደኛው ከባርሤሎና ግን 16 ነጥቦች ይለዩታል።

በኢጣሊያ ሤሪያ-አ ቀደምቱ ጁቬንቱስ ቱሪን በገዛ ሜዳው በዝቅተኛው ክለብ በሣምፕዶሪያ ያልተጠበቀ የ 2-1 ሽንፈት ደርሶበታል። ሣምፕዶሪያ ለድል የበቃው ለዚያውም ተጫዋቹ ጋይታኖ ቤራንዲ በ 31ዋ ደቂቃ ላይ ተቀጥቶ ከሜዳ ወጥቶበት ነው። ለቡድኑ ሁለቱን ጎሎች በሁለተኛው አጋማሽ ያስቀጠረው ደግሞ የ 19 ዓመቱ ወጣት አርጄንቲናዊ ማውሮ ኢካርዲ ነበር። ሁለተኛው ላሢዮ በበኩሉ ግጥሚያ ካልጋሪን 2-1 ሲረታ የጁቬንቱስ አመራር ወደ አምሥት ዝቅ ብሏል። ናፖሊ ሶሥተኛ ሲሆን ፊዮሬንቲናና ኢንተር ሚላን በቅርብ ይከተሉታል።

በኢጣሊያ ሣምንቱ የኤሢ ሚላን ተጫዋቾች ዘረኝነትን በመቃወም ሜዳ ለቀው የወጡበት ሁኔታ የጋረደውም ነበር። ጋናዊው የሚላን የመሃል ሜዳ ተጫዋች ኬቪን-ፕሪንስ-ቦአቴንግ ባለፈው ሐሙስ በአንድ የወዳጅነት ግጥሚያ ላይ የደረሰበትን የዘረኞች ዘለፋ በመቃወም ጨዋታውን ሲያቋርጥ ጓደኞቹም ተከትለውት ከሜዳ በመውጣት የተለየ ድጋፍ አሳይተዋል። ዕርምጃው በርከት ባሉ ተጫዋቾችና ፖለቲከኞች ቢወደስም የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር የፊፋ ፕሬዚደንት ሤፕ ብላተር ግን «ሜዳን ለቆ መውጣት መፍትሄ አይሆንም» የሚል አቋም ነው የያዙት።

ብላተር አንድ የተሸነፈ ቡድን ምናልባት ከሜዳ ሊሸሽ ቢሞክርስ የሚል ሃሣብ አንስተዋል። እርሳቸው እንደሚሉት ብቸኛው መፍትሄ በሚመለከታቸው ክለቦች ላይ ማዕቀብን ማጠናከር ነው። የሆነው ሆኖ እስካሁን አቻ ያልታየለት የኤሢ ሚላን ተጫዋቾች ቦአቴንግን በመደገፍ የወሰዱት ዕርምጃ ሊደነቅ የሚገባው ነው። ዘረኝነት ለአንዲት ደቂቃ እንኳ ኳስ ሜዳ ዝር እንዲል ዕድል መስጠት አያስፈልግም። በነገራችን ላይ በአውሮፓ ስታዲዮሞች በተለይም በአፍሪቃውያን ተጫዋቾች ላይ የዘረኝነት ስድብ ማውረዱ ባለፉት ዓመታት እየጨመረ ነው የመጣው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ሣምንቱ የፌደሬሺኑ ዋንጫ የ FA Cup ውድድር ነበር። በፌደሬሺኑ ዋንጫ ውድድር ሶሥተኛ ዙር ኔዘርላንዳዊው የማንቼስተር ዩናይትድ አጥቂ ሮቢን-ፋን-ፐርሢ ተቀይሮ ሜዳ ከገባ በኋላ ጠቃሚ ጎል አስቆጥሮ ክለቡን ከሽንፈት በማዳን ብልህነቱን እንደገና አስመስክሯል። ማኒዩ ከዌስት ሃም ዩናይትድ 2-2 ሲለያይ ቼልሢይ ሣውዝሃምተንን በፍጹም የበላይነት 5-1 አሸንፏል።

ቶተንሃም ሆትስፐር ደግሞ ካቬንትሪይ ሢቲይን 3-0 ሲረታ ሊቨርፑልም ማንስፊልድ ታውንን 2-1 አሸንፏል። አርሰናል ደግሞ ከስዋንሢይ ሢቲይ 2-2 ነው የተለያየው። እነዚህ በሙሉ የአንደኛ ዲቪዚዮን ክለቦች ውጤት ሲሆኑ በጠቅላላው ወደ ተከታዩ ዙር ያለፉት ክለቦች ሰላሣ ይሆናሉ።

በፈረንሣይ ሊጋም ሣምንቱ የብሄራዊው ዋንጫ ውድድር ሲሆን ኦላምፒክ ሊዮን 64 ክለቦች በተሳተፉበት የመጀመሪያ ዙር ተሸንፎ ሲወጣ ከ 15 ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። ሌሎች አራት የአንደኛው ዲቪዚዮን ክለቦችም በዝቅተኛ ቡድኖች ተሸንፎ ከውድድሩ የመሰናበት ዕጣ ገጥሟቸዋል። የፈረንሣይ ሻምፒዮና መሪ ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን በአንጻሩ የአምሥተኛ ዲቪዚዮኑን አማተር ክለብ አራስን 4-3 ማሸነፉ ሆኖለታል።

ትናንት በወጣው የተከታዩ ዙር ዕጣ መሠረት ቀደምቱ ክለቦች ቦርዶና ማርሤይ ዝቅተኛ ቡድኖች ሲደርሷቸው ከሁለት ሣምንት በኋላ በሚካሄዱት ግጥሚያዎች ፓሪስ-ሣንት-ዠርማን ከቱሉዝ፤ እንዲሁም ሞንትፔሊየር ከሶሾው ይገናኛሉ።

በፖርቱጋል ሻምፒዮና ለአንደኝነት የሚፎካከሩት ፖርቶና ቤንፊካ በየበኩላቸው ግጥሚያ ሲያሸንፉ ቤንፊካ በሶሥት ነጥቦች ብልጫ ይመራል። እርግጥ ፖርቶ ገና አንድ ቀሪ ግጥሚያ በዕጁ አለው። ሁለቱ ቀደምት ክለቦች በፊታችን ሰንበት ሊዝበን ላይ እርስበርስ የሚገናኙ ሲሆን ግጥሚያው በመጠኑም ቢሆን በሻምፒዮናው ሂደት ላይ ወሣኝነት ሊኖረው የሚችል ነው።

በተቀረ የዓለም እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ፊፋ በዛሬው ምሽት ስዊትዘርላንድ ዙሪክ ላይ በሚካሄድ ስነ ስርዓት የ 2012 ዓ-ም የዓለም ድንቅ ተጫዋችን መርጦ ይሰይማል። ለምርጫው የቀረቡት ሶሥት ዕጩዎች የሬያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ፣ እንዲሁም ሊዮኔል ሜሢና ኢኒየስታ ከባርሤሎና ሲሆኑ አሁንም ተሸላሚው ለተከታታይ አራተኛ ጊዜ ሊዮኔል ሜሢ ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች ግምት ነው። በሌላ በኩል ከብራዚል በኩል የወጣት ኮከቧ የኔይማር ከዕጩዎቹ አንዱ አለመሆን በፊፋ ላይ ቅሬታን ማስከተሉ አልቀረም።

ቴኒስ

በዛሬው ዕለት የወጣ የኤቲፒ የዓለም ቴኒስ ማዕረግ ተዋረድ የሰርቢያው ኖቫክ ጆኮቪች በ 12920 ነጥቦች አንደኛ ሆኖ መቀጠሉን አረጋግጧል። የስዊሱ ሮጀር ፌደረር በ 10265 ሁለተኛ ሲሆን የብሪታኒያው ኤንዲይ መሪይ በ 8000 ነጥቦች ሶሥተኛ ሆኖ ይከተላል። አራተኛው የስፓኙ ራፋኤል ናዳል ሲሆን የአገሩ ልጅ ዴቪድ ፌሬር ሊደርበው እየተቃረበ መሆኑን ነው አዲሱ ተዋረድ የሚያመለክተው።

በሴቶች የዓለም ቴኒስ ማሕበር የማዕረግ ተዋረድ የቤላሩሷ ቪክቶሪያ አዛሬንካ በአመራሯ ስትቀጥል ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ ሁለተኛ ናት። ያለፈው ዓመት ድንቅ ተጫዋች አሜሪካዊቱ ሤሬና ዊሊያምስ ደግሞ ወደ ሶሥተኛው ቦታ ከፍ ስትል ለቁንጮነት ብርቱ ተፎካካሪ እየሆነች መጥታለች።

መሥፍን መኮንን

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 07.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17FUp
 • ቀን 07.01.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17FUp