ከስፖርቱ ዓለም | ስፖርት | DW | 30.04.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

ከስፖርቱ ዓለም

የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት ጥቂት ጊዜ ቀርቶቅ ሳለ ሣምንቱ ያለፈው ዝግጅቱን ከፖላንድ ጋር በጋራ የምታስተናግደው የኡክራኒያ መንግሥት በተቃዋሚዋ የቀድሞ መሪ በዩሊያ ቲሞሼንኮ ላይ የሚፈጽመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከብራስልስ እስከ በርሊንና ከዚያም ባሻገር ብርቱ ዓለምአቀፍ ቁጣን ባስከተለበት ሁኔታ ነው።

የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ፍጻሜ ውድድር ሊከፈት ጥቂት ጊዜ ቀርቶቅ ሳለ ሣምንቱ ያለፈው ዝግጅቱን ከፖላንድ ጋር በጋራ የምታስተናግደው የኡክራኒያ መንግሥት በተቃዋሚዋ የቀድሞ መሪ በዩሊያ ቲሞሼንኮ ላይ የሚፈጽመው አስከፊ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ከብራስልስ እስከ በርሊንና ከዚያም ባሻገር ብርቱ ዓለምአቀፍ ቁጣን ባስከተለበት ሁኔታ ነው። በዚህ በጀርመን ቲሞሼንኮ ከእሥራት ካልተለቀቁ ኡክራኒያ ውድድሩን ከማስተናገድ መታገድ ይኖርባታል የሚል ድምጽ በርከት ባሉ ፖለቲከኞች ዘንድ እየጎላ ሲሄድ ነው የሚታየው።

ለግንዛቤ ያህል የአንዴዋ የኡክራኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዩሊያ ቲሞሼንኮ ሰብዓዊ ክብርን የሚያዋርድ የእሥራት ሁኔታቸውን በመቃወም ከአንድ ሣምንት ወዲህ በረሃብ ዓድማ ላይ ይገኛሉ። ቲሞሼንኮ ካለፈው ዓመት ወዲህ በእሥራት ላይ ሲሆኑ ነጻነታቸውን የተገፈፉት ያላግባብ እንደሆነ በርካታ ታዛቢዎች የሚያረጋግጡት ጉዳይ ነው። የተቃውሞው ወገን መሪ ፍትሃዊነቱ አጠያያቂ በሆነ ችሎት የሰባት ዓመት እሥራት ሲበየንባቸው ዕርምጃው ከፖለቲካው መድረክ እንዲሰወሩ ለማድረግ የተወጠነ ለመሆኑ ብዙም ጥያቄ የለውም።

ድርጊቱ ፕሬዚደንት ቪክቶር ያኑኮቪች በተለመደው ስታሊናዊ የፖለቲካ ዘይቤ ከበስተጀርባ ሆነው የመሩት የበቀል ዕርምጃ መሆኑ ነው የሚታመነው። ቲሞሼንኮ በእሥራት ላይ እንዳሉ ብዙ መነገላታት ሲደርስባቸው በጠባቂዎቻቸው እስከመብደብ መድረሳቸውንም ጠበቃቸው ሤርጌይ ቭላሴንኮ አረጋግጠዋል።

«ዩሊያ ቲሞሼንኮ አርብ ዕለት በወህኒቤት ሠራተኞች ተደብድበዋል። በዚሁም በሆዳቸውና በዕጆቻቸው ላይ መጎዳታቸው የታየ ነገር ነው። ቲሞሼንኮ በሃይል አምቡላንስ ተሽከርካሪ ላይ ተጭነው ወደ ሆስፒታል ከተወሰዱ በኋላም ዕሑድ ነበር ወደ እሥርቤት የተመለሱት»

ይህም ሆኖ ጀርመንና መሰል መንግሥታት የታመሙት የፖለቲካ እሥረኛ ቲሞሼንኮ በፍጥነት ነጻ ተለቀው የሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ የሚያደርጉትንግፊት የኡክራኒያ መንግሥት በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት በሚል ከመቃወም ሌላ የተሻለ መንገድ አልታየውም።

እናም ያኑኮቪች በዚሁ ግትርነት ከቀጠሉ ማዕቀብ መጣሉ አስፈላጊ ሲሆን የአውሮፓን ዋንጫ ውድድር በኡክራኒያ ተገኝተው ለመታዘብ ዕቅድ የነበራቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ሃሣባቸውን እንደሚቀይሩም የሚጠበቅ ነው። አለበለዚያ የጀርመን ሶሻል ዴሞክራቶች ፓርቲ ጠቅላይ ጸሐፊ አንድሬያ ናህለስ እንዳስገነዘቡት የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

«እንደ አንድ ፖለቲከኛ ወደዚያ መጓዙ ራሱ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም መንግሥት እንደ ድጋፍ አድርጎ ሊጠቀምበት እንደሚችል ግልጽ ነው»

በሌላ በኩል የውድድሩን መስተንግዶ ከኡክራኒያ ነጥቆ ለሌላ መስጠት ከጊዜው አጭርነት የተነሣ አስቸጋሪ ከመሆኑ ባሻገር የኡክራኒያን ሕዝብ እንደመቅጣትም ሊቆጠር የሚችል ነው። ስለሆነም ይህን የስርዓቱ ሰለባ ቲሞሼንኮ ራሳቸው እንኳ ልጃቸው የቭጌኒያ እንደጠቀሰችው የሚፈቅዱት አይደለም። ቀሪው አማራጭ እንግዲህ የኪየቩ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ረገጣን እንዲያቆም ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችም ሆኑ በውድድሩ የሚሳተፉ ስፖርተኞች በተገኘው ዘዴ ሁሉ ተቃውሞና ገፊት በማድረግ መቀጠላቸው ይሆናል።

እርግጥ የኡክራኒያ ሁኔታ የአውሮፓ እግር ኳስ ፌደሬሺኖች ማሕበር ዩኤፋም ሆነ መሰል ዓለምአቀፍ የስፖርት ተቋማት አንድን አገር አዘጋጅ አድርገው ከመምረጣቸው በፊት የፖለቲካውን ሁኔታ ደህና አድርገው እንዲያጤኑ እንደገና የሚያስገነዝብ ነው። የዜጎችን መብት የሚረግጡ ገዢዎች ገመናቸውን ለመሸፋፈን የተመቻቸ የተውኔት መድረክ ሊያገኙ አይገባቸውም።

BdT Hamburg Marathon 2010

አትሌቲክስ

በዚህ በጀርመን ትናንት ሃምቡርግና ዱሰልዶርፍ ላይ በተካሄዱ የማራቶን ሩጫ ውድድሮች በወንዶች የኢትዮጵያ አትሌቶች ለድርብ ድል በቅተዋል። በሃምቡርግ ማራቶን ሻሚ ዳዊት 42ቱን ኪሎሜትር በሁለት ሰዓት ከአምሥት ደቂቃ 59 ሤኮንድ ጊዜ በማቋረጥ ሲያሸንፍ የስፓኙ ሁሊዮ ሬይ ከስድሥት ዓመታት በፊት አስመዝግቦት የነበረውን የከተማይቱን ክብር-ወሰን ለማሻሻልም በቅቷል።

በውድድሩ ሌላው ኢትዮጵያዊ ዳዲ ያሚ ሁለተኛ ሲወጣ ሩጫውን በሶሥተኝነት የፈጸመው ኬንያዊው አውጉስቲን ሮኖህ ነበር። ከዚሁ ሌላ ሹሚ ዳጫሣ አራተኛ፤ እንዲሁም ፈቃዱ ለማ ስድሥተኛ ሆነዋል። በሴቶች ኬንያዊቱ ራኤል ኪያራ ስታሸንፍ ከኢትዮጵያ ነጻነት አበዮ ሁለተኛና እታለማሁ ኪዳኔም ሶሥተኛ በመሆን ሩጫውን ፈጽመዋል። ድንቅነሽ መካሻ ደገሞ ሰባተኛ ሆናለች።

በዱሰልዶርፍ ማራቶንም በወንዶች ኢትዮጵያዊው ሰቦቃ ቶላ ሲያሸንፍ ኬንያዊው ዱንካን ኮች ደግሞ ሁለተኛ ወጥቷል። በሴቶችም ኬናያዊቱ አግነስ ጄሩቶ አንደኛ ስትሆን የቤላሩሷ ናስታዚያ ስታራቮይታቫ ሁለተኛና መልካም ግዛውም ሶሥተኛ በመሆን የማራቶኑን ርቀት በስኬት አቋርጠዋል። ከዚሁ ሌላ ከተቀሩት የኢትዮጵያ አትሌቶች ከበቡሽ ሃይሌ አምሥተኛ ስትወጣ ፋንቱ እቲቻም ሰባተኛ ሆናለች።

እግር ኳስ

በአውሮፓ ቀደምት ሊጋዎች ውድድር ሪያል ማድሪድ ወደ ሻምፒዮንነት ፌስታው ሲቃረብ እንደ ጀርመን ሁሉ በፖርቱጋል፣ በሩሢያና በሰርቢያ ደግሞ የአንደኞቹ ማንነት ለይቶለታል። በስፓን ላ-ሊጋ ሬያል ማድሪድ ሴቪያን 3-0 ሲረታ ከአራት ዓመታት የባርሤሎና ልዕልና በኋላ ሻምፒዮንነቱን ለመረከብ የአንድ ጨዋታ ድል ይጎለዋል። ይህም በፊታችን ረቡዕ ሊሣካ የሚችል ነው። ባርሤሎና በበኩሉ ግጥሚያ ራዮ ቫሌካኖን 7-0 ሲቀጣ ሬያል በሰባት ነጥቦች ልዩነት መምራቱን እንደቀጠለ ነው። የስፓኙ ውድድር ሊያበቃ ሶሥት ግጥሚያዎች ብቻ የቀሩ ሲሆን ሬያል ማድሪድ ሻምፒዮን ለመሆን እንግዲህ አንዲት ድል ትበቃዋለች።

በጀርመን ቡንደስሊጋ ምንም እንኳ ውድድሩ በዶርትሙንድ ሻምፒዮንነት ቀድሞ ቢለይለትም የሰንበቱ ግጥሚያዎችም ችላ የሚባሉ አልነበሩም። ባየርን ሚዩኒክ ሽቱትጋርትን 2-0 በመርታት የሊጋ ሁለተኝነቱን ሲያረጋግጥ ሻልከም በርሊንን 4-0 በማሸነፍ ለመጪው ዓመት የአውሮፓ ሻምፒዮና ሊጋ ውድድር ቀጥተኛ ተሳትፎ በቅቷል። ከባድ ሽንፈት የደረሰበት በርሊን በአንጻሩ ከሁለተኛውዲቪዚዮን ሶሥተኛ ተጋጥሞ ራሱን ለማዳን እንደ ኮሎን ሁሉ በፊታችን ቅዳሜ የመጨረሻ ግጥሚያ ማሸነፉ ግድ ነው።

እርግጥ በርሊን ከተሸነፈ ኮሎኝ ተሸንፎም ቢሆን የመትረፍ ዕድል ይኖረዋል። የበርሊን ዕድል በአንጻሩ የመነመነ ሲሆን አሠልጣኙ ኦቶ ሬሃገል እንዳለው ከኳስ አምላክ የተሰጠውን የመጨረሻ ዕድል መጠቀም መቻሉ ግድ ነው።

«የኳስ አምላክ ለፊታችን ቅዳሜ ገና አንድ ዕድል ሰጥቶናል። እናም እኔ በርሊን ውስጥ ባለሁባቸው ባለፉት ሁለት ወራት ያልተቆጠበ ድጋፍ የሰጡንን ተመልካቾች ለመካስ እንደምንበቃ ተሥፋ አደርጋለሁ። እስካሁን ይህ በሜዳችን ባደረግናቸው ግጥሚያዎች አልተሳካልንም»

በነገራችን ላይ ካይዘርስላውተርን ቀደም ብሎ ወደ ሁለተኛው ዲቪዚዮን ሲከለስ በሌላ በኩል ግሮይተር ፉርትና ፍራንክፉርት ደግሞ ወደ አንደኛው ዲቪዚዮን ከፍ ማለቱ ተሳክቶላቸዋል። ከኮሎኝ ወይም ከበርሊን በመግጠም አንደኛውን ቡንደስሊጋ ለመቀላቀል ደግሞ ከዱስልዶርፍ፣ ፓደርቦርንና ከሣንት ፓውሊ አንዱ ዕድል አለው።

በእንግሊዝ ፕሬሞየር ሊግ ቀደምቱ ክለቦች ማንቼስተር ዩናይትድና ማንቼስተር ሢቲይ በዛሬው ምሽት እርስበርሳቸው የሚጋጠሙ ሲሆን ውጤቱ በሻምፒዮናው ላይ ወሣንነት ሊኖረው የሚችል ነው። ሻምፒዮናው ሊያበቃ ሶሥት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ ማኒዩ የሚመራው በሶሥት ነጥቦች ብልጫ ብቻ ነው። በተለይ ዛሬ ማንቼስተር ሢቲያ ካሸነፈ ውድድሩ እስከመጨረሻው ቀን ሳይለይለት ሊቀጥልም ይችላል።

በኢጣሊያ ሊጋም ሁኔታው የእንግሊዙን መሰል ሲሆን ለዋንጫ የሚፎካከሩት ጁቬንቱስና ኤሲ ሚላን የሚለያዩት እንዲሁ በሶሥት ነጥቦች ብቻ ነው። በተቀረ በኔዘርላንድ አያክስና በፈረንሣይ ሞንትፔሊየር ግንባር ቀደም እንዲሆኑ ሲቀጥሉ በፖርቱጋል ሻምፒዮናው ሁለት ግጥሚያዎች ቀርተው ከወዲሁ ለይቶለታል። ፖርቶ ማሪቲሞን 2-0 አሸንፎ ለ 26ኛ ጊዜ የፖርቱጋል ሻምፒዮን ሲሆን ለዚህም የጠቀመው የሁለተኛው የቤንፊካ በእኩል ለእኩል ውጤት መወስን ነው። ከዚሁ ሌላ በሰርቢያ ፓርቲዛን ቤልግሬድ ለ 24ኛ ሻምፒዮንነቱ ሲበቃ ዜኒት ፔተርስበርግም በተከታታይ ለሁለተኛ ጊዜ የሩሢያ ሻምፒዮን ሆኗል።

በአፍሪቃ ክፍል-ዓለም አንጋፋው ክለብ አሣንቴ ኮቶኮ ትናንት ለ 22ኛ ጊዜ የጋና ፕሬሚየር ሊግ ሻምፒዮን ሊሆን በቅቷል። የኩማሢው ክለብ አፍሪቃ ውስጥ ስኬታማ ከሚባሉት አንዱ መሆኑ ይታወቃል። ኮቶኮ ዘንድሮ ለሻምፒዮንነት የበቃው ገና ውድድሩ ሊያበቃ አራት ግጥሚያዎች ቀርተው ሳለ በ 15 ነጥቦች ልዩነት በመምራት ነው። ኮቶኮ በዘንድሮው ድሉ ከሶሥት ዓመታት በኋላ እንደገና ወደ አፍሪቃ ሻምፒዮና ሊጋ የሚመለስ ሲሆን በክፍለ-ዓለሙ ውድድር ሁለቴ ልድል በቅቶ ነበር። ታዲያ የኮቶኮ መመለስ ሻምፒዮናውን ይበልጥ እንደሚያምቅ ጨርሶ አያጠራጥርም።

ቴኒስ

የስፓኙ ኮከብ ራፋኤል ናዳል ትናንት በባርሤሎና-ኦፕን ፍጻሜ ግጥሚያ የአገሩን ልጅ ዴቪድ ፌሬርን በለየለት 7-6,7-5 ውጤት በማሸነፍ በአሸዋ ሜዳ ላይ የማይበገር ንጉስ መሆኑን እንደገና አስመስክሯል። በዓለም የማዕረግ ተዋረድ ላይ ሁለተኛው የሆነው ራፋ በባርሤሎና ፍጻሜ ለድል ሲበቃ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ናዳል ከሣምንት በፊት በሞንቴ ካርሎ የዓለም አንደኛ የሆነውን ኖቫክ ጆኮቪችን እንዲሁ በፍጹም ልዕልና በማሸነፍ ለተከታታይ ስምንተኛ ድሉ መብቃቱም አይዘነጋም።

የስፓኙ ኮከብ አሁን በሁለት ውድድሮች በያንዳንዳቸው ቢያንስ ሰባት ጊዜ በማሸነፍ ብቸኛው የቴኒስ ኮከብ ለመሆን በቅቷል። በነገራችን ላይ የትናንቱ ቀን ናዳል ከአሥር ዓመት በፊት በ 15 ዓመት ዕድሜ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተጫወተበት ቀንም የገጠመ ነበር። ራፋ ባለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ባጋጠመው የአካል ጉዳት የተነሣ ግንባር-ቀደም ቦታውን ሲያጣ ዘንድሮ ግን ስኬታማ ጉዞ የሚያደርግ ነው የሚመስለው።

በዚህ በጀርመን በሽቱትጋርት የሴቶች ዓለምአቀፍ ቴኒስ ፍጻሜ ግጥሚያ ደግሞ ሩሢያዊቱ ማሪያ ሻራፖቫ የዓለም አንደኛዋን የቤላሩሷን ቪክቶሪያ አዛሬንካን በቀላሉ 6-1,6-4 በመርታት ለዓመቱ የመጀመሪያ የዓለም ቴኒስ ማሕበር ፍጻሜ ድል በቅታለች። ለሩሢያዊቱ ኮከብ የትናንቱ ድል 25ኛው መሆኑ ነበር።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 30.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14nET
 • ቀን 30.04.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/14nET