ከስደት ተመላሾችና አገር በቀሉ ድርጅት | አፍሪቃ | DW | 04.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

ከስደት ተመላሾችና አገር በቀሉ ድርጅት

በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች ለሕይወት አስጊ በሆነ መንገድ ወደ ተለያዩ ሃገራት እየፈለሱ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ በርካታ ሰዎች ለሕይወት አስጊ በሆነ መንገድ ወደ ተለያዩ ሃገራት እየፈለሱ ይገኛሉ። የስደት ሕይወት እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱም ቁጥራቸዉ ጥቂት አይደለም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:10
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:10 ደቂቃ

ከስደት ተመላሾች

ይሁን እንጂ ወደ ሀገራቸዉ ገብተዉ በጥሪት እጦት ምክንያት ሕይወትን እንደ አዲስ ለመጀመር ሲቸገሩ ይታያል። «ላይቭ አዲስ» የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት እነዚህን ከስደት ተመላሾች ለመርዳት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል። የዶቼ ቬለዋ ኮሌታ ወንጂ በዚህ ላይ ዘገባ አጠናቅራለች፤ ፀሐይ ጫኔ ታቀርበዋለች። 

ኢትዮጵያ በርካታ የሌሎች ሃገራት ስደተኞችን የምትቀበለዉን ያህል የዜጎችዋ ፍልሰትም ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንደመጣ የተለያዩ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በቅርቡ እንኳ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን እንደ ጎርጎርጎረሳዉያኑ ዘመን ቀመር ነሐሴ 2016  የሃገርዋ ዜጎች ጥለዋት በሸሹትና በጦርነት በምትታመሰዉ የመን በህገ ወጥ ስደት የታሰሩ 2000 ኢትዮጵያዉያን መለቀቃቸዉን ዘግቦ ነበር።
 ይህ የሚያሳየዉ ደግሞ ወደ መካከለኛዉ ምስራቅና ወደ አዉሮጳ ለመሻገር ወደተለያዩ አፍሪቃ ሃገሮች የሚደረገዉ ለሕይወት አደገኛና ፈታኝ ጊዞ አሁንም ድረስ መቀጠሉ ነዉ። 
 በአስቸጋሪዉ የስደት ጉዞ ከህገወጥ ደላሎችና በአሰሪዎቻቸዉ በሚደርስባቸዉ ጉዳት ብዙዎቹ ስደተኞች ለሥነ- ልቦና ቀዉስ ተዳርገዋል። ያም ሆኖ ግን አስቸጋሪዉ ጉዞና ህይወት ኢትዮጵያዉያኑን ስደተኞች ወደ ሃገር እንዲመለሱ አላደረጋቸዉም። ለዚህ ደግሞ አዲስ ሕይወት ለመጀመር የሚያስችል ጥሪት አለመኖር አንዱ ሆኖ በምክንያትነት ይጠቀሳል። 
«ላቭ አዲስ» የተባለዉ በአዉሮጳ ሕብረት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለት አገር በቀል ድርጅት፤ ይህንን በመገንዘብ ይመስላል ከስደት ተመላሾችን የሥራ ፈጠራ ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በግል ሥራ እንዲሰማሩ እየጣረ ነዉ። አዲስ አበባ ከተማ የሚገኘዉ ይኸዉ ድርጅት ከስደት ተመላሾችና በሕገ ወጥ ዝዉዉር ጎዳት የደረሰባቸዉን ሰዎች ይረዳል ነዉ የተባለዉ ። 
አልዓዛር  በሻ ከተጠቃሚዎቹ ዉስጥ አንዱ ነዉ። አልዓዛር እንደሚናገረዉ በጓደኞቹ ምክር ተገፋፍቶ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትንህርቱን አቋርጦ በጎርጎረሳዉያኑ የዘመን ቀመር በ2014 ወደ ዱባይ ሄዶ ነበር ። ይሁን እንጂ ሕይወት በዱባይ እንዳሰበዉ ቀላል አልነበረምና በሕገ ወጥ ነንገድ ከመሄዱ ጋር ተያይዞ ቪዛ በመከልከሉ በአምስተኛ ወሩ ወደ ሃገሩ መመለሱን ይገልፃል ። 
« በዱባይ ሁኔታዉ በጣም አስቸጋሪ ነበር ለአምስት ወራት በጣም ነዉ የተሰቃየሁት የጎዳና ላይ ወሮበሎች ሊገድሉኝ ነበር።
 አልዓዛር ከስደት እንደተመለሰ «ላይቭ አዲስ» የተባለ ድርጅት ከስደት ተመላሾችን እንደሚረዳ በመስማቱ ድርጅቱ ዘንድ እንደ ሄደ ይናገራል። ከድርጅቱ በተደረገለት ድጋፍም የ 21 ቀናት ስልጠና ከወሰደ በኋላ እንጀራ ለመሸጥ እንዳቀደ ይገልፃል። 
« በመጀመርያ በአራት የኤሌትሪክ ምድጃዎች እንጀራ መጋገር እጀምራለሁ። አሁን ሁለት የኤሌትሪክ ምድጃዎች አሉኝ ። «ላይቭ አዲስ» ገንዘብ ይሰጠኛል ቀሪዎቹን ሁለት ምድጃዎች እገዛለሁ» 
አልዓዛር የስራ እቅዱን ለ 31 የሥደት ተመላሽ ሰልጣኝ ጓደኞቹ አቅርቦ አስተችቶአል። የላይቭ አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ተሾመ እንደሚናገሩት በስደት ተመላሾቹ የሚቀርቡት እቅዶች ወደ ተግባር ከመለወጣቸዉ በፊት በደንብ እንዲታዩ ይደረጋል። 
« የንግድ እቅዱን ከከለስን በኋላ በተሻሻለዉና በፀደቀዉ እቅድ መሠረት ወደትግበራ እንገባለን። ወደ ሥራ ለመግባት በአጠቃላይ ሁለት ሳምንት አይፈጅም። ከዝያም የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ይደረጋል። »
እንደ አቶ አለማየሁ ገለፃ ድርጅቱ ከስደት ተመላሾቹ ስልጠና ከወሰዱ በኋላ ለሚሰማሩበት ሥራ ፍቃድ እንዲያገኙ በአካባቢዉ ከሚገኙት የአስተዳደር አካላት ጋር ትስስር እንዲፈጥሩ ይደረጋል። 
« ላይቭ አዲስ ንግዱን ሲጀምሩ ቢያንስ ለስድስት ወራት ምክር የሚሰጡ ክትትል የሚያደርጉና ሞያዊ እገዛ የሚሰጡ የማኅበረሰብ አመቻቾችን ይመድባል። » 
አልዓዝአርና 31 ከስደት ተማላሽ ጓደኞቹ ከላይቭ አዲስ ጋር አሁን አዲስ መንገድና ሕይወት ጀምረዋል። ይሁን እንጂ ከችግሩ ስፋትና ዓይነት አንጻር አባይን በጭልፋነዉና ሌሎች ላይቭ አዲስን የመሰሉ በርካታ ድርጅቶች ሃገሪቱ የሚያስፈልጓት ይመስላል። 
 

ኮሌታ ወንጂ / ፀሐይ ጫኔ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic