ከሳውዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን | ኤኮኖሚ | DW | 12.12.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ከሳውዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን

የሳውዲ አረቢያ መንግስት ህገወጥ ስደተኞች ያላቸውን የውጪ ዜጎች ከኣገሩ ለማስወጣት በጀመረው መጠነ ሰፊ ዘመቻ አኩዋያ የኢትዮጵያ መንግስትም 30 000 ያህል ዜጎችን ወደ ኣገራቸው ለመመለስ መገደዱን ባለፈው ወር ማስታወቁ ይታወሳል።

ዓለም ዓቀፉ የስደተኞች ተቐም IOM ዛሬ እንዳስታወቀው ግን ባልተጠበቀ ሁኔታ እስከ ኣሁን ብቻ ይህ ቁጥር በአራት እጥፍ ጨምሮ 120 000 ያህል ኢትዮጵያውያን ወደ ኣገር ቤት ተመልሷል። ገና ደግሞ ኣልተጠናቀቀም። ይህም ይላል IOM በዓለማችን በቅርብ ጊዜ ታሪክ የመጀመሪያው ትልቁ የስደት ተመላሾች ቁጥር መሆኑ ነው። በመሆኑም በኢትዮጵያ የIOM የበላይ ኃላፊ የሆኑት ሚ/ር ኦጊና ጆይሳሽ እንደገለጹት እነዚህን ከስደት ተመላሾች ለማጘጘዝም ሆነ ለመንከባከብ ሁኔታው ከድርጅታቸው ኣቅም በላይ እየሆነባቸው ነው።እናም IOM የሌሎች ዓለም ዓቀፍ ተቐማትን ድጋፍ ለመጠየቅ ተገዷል። በዚሁ መሰረት ኣሁን ለኣስቸኩዋይ ጊዜ ድጋፍ 9,5 ሚሊየን ዩሮ ወይንም 247 ሚሊየን ብር ያስፈልጋል።b

የተመላሾች ቁጥር በትንሹ 150 000 ገደማ ሊደርስ ይችላል ያሉት ሚ/ር ኦጊና የሚመጡት ደግሞ ባዶ እጃቸውን ከመሆኑም በላይ አብዛኞቹ የተጎሳቆሉ፣ የታመሙ፣ እና ህጻናትን የያዙ እንዲሁም የደረሱ ነፍሰጡሮች ጭምር በመሆናቸው የቁጥራቸውን ያህል ኣስፈላጊው ወጪም ባልተጠበቀ ሁኔታ እያሻቀበ መሆኑን ኣስረድቷል።

ዓለም ዓቀፉ የሰራተኞች ተቐም በምህጻሩ ILO እንደሚለው ደግሞ እነዚህ ከስደት ተመላሾች በዚያች ኣገር በነበሩበት ዓመታት ይህ ነው የማይባል ዓካላዊ እና ስነልቦናዊ በደል የደረሰባቸው ናቸው።

በሳውዲ አረቢያ ለአራት ዓመታት ያህል በአናጺነት ሲያገለግል የቆየው የ36 ዓመቱ ቀመር ዓሊም ህይወት በሳውዲ አረቢያ እያነቡ መኖር ነው ሲል ብሶቱን ገልጿል።

ከአስር ወራት በፊት ነበር ለልጆቼ በተቻለ ፍጥነት ገንዘብ ለመላክ ኣስቤ ወደ ሳውዲ አረቢያ የሄድኩት ያለችው የ30 ዓመቷ ገንዘብ ተፈራ በበኩልዋ ስራ ጀምራ ግን ደሞዝዋን ለመከፈል ሰባት ወር እንዳቆዩዋት በምሬት ኣውስታለች።

ተበድሬ የሄድኩትን ገንዘብ እንኩዋን ከፍዬ ሳልጨርስ ነው የመጣሁት ያለችው ኣንዲት ሌላ ኢትዮጵያዊት ሴትም እዚህ የስራ እድል ባለመኖሩ ቢያንስ እዳዋን ከፍላ ከህሊናዋ ጋር ለመታረቅ ስትል ተመልሳ ወደ አረብ ኣገር ለመሄድ እያሰበች መሆንዋን ለIOM ኣስረድታለች። አብዛኞቹ ተመላሾችም ወደየቀበሌያቸው ከመመለስ ይልቅ በአዲስ ኣበባ መቆየትን ይመርጣሉ ተብሏል።

91 ሚሊየን ገደማ ህዝብ ባላት ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ በከተሞች ያለው የስራ ኣጥነት መጠን 20 በመቶ ሲሆን በIOM መረጃ መሰረት የኣንድ ኢትዮጵያዊ ኣማካኝ ገቢ በቀን ከሁለት ዶላር በታች ነው።

ጃፈር ዓሊ

ነጋሽ መሃመድ

Audios and videos on the topic