ከሳዉዲ የመመለስ ስጋት እና ፈተና | ኢትዮጵያ | DW | 21.06.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ከሳዉዲ የመመለስ ስጋት እና ፈተና

ሳዑድ አረቢያ ያለ ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሚኖሩ የዉጭ ዜጎች እንዲወጡ የሰጠችዉ የጊዜ ገደብ ሊያበቃ 5 ቀናት ቀርተዋል። እስካሁን በርካታ ኢትዮጵያዉያን ወደሀገር ገብተዋል። ቀሪዎቹም አስፈላጊዉን ዝግጅት አጠናቀዉ የበረራ ቀናቸዉን እየጠበቁ ነዉ። የመመለስ ፍላጎቱ የሌላቸዉ የመኖራቸዉን ያህል መመለስ ብንፈልግም አቅም የለንም የሚሉም ይገኛሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:20

መመለስ ቢፈልጉም ገንዘብ ማጣት እንቅፋት ሆኗል፤

በሳዑዲ በረሃ ከብቶችን ከሚጠብቁ ኢትዮጵያዉያን አንዱ የሆነዉ መንገሻ የመጣንበት መንገድ ብዙ ዉጣ ዉረድ ያለበት ቢሆንም «የሳዑድ አረቢያ መንግሥት እንዲህ ያለዉን ዉሳኔ ከወሰነ ምን አማራጭ አለን መዉጣት ነዉ እንጂ» ሲል ይተክዛል። ለመመለስ ግን ችግር አለ ባይ ነዉ። ዕዳ። ወደ ሳዉዲ ከገባ ጥቂት ወራት የሆነዉ ይህ ኢትዮጵያዊ እሱ ብቻ ሳይሆን እሱን መሰል ሌሎች ወገኖቹም ከሀገራቸዉ ወጥተዉ እዚህ ለመድረስ ብዙ ገንዘብ ተበድረዋል።

«እዚህ መጥተሽም ለመክፈል አትችይም፤ ገና አዲስ ነዉ የመጣሽዉ። በጨለማ እና በገደል ላይ በስንት መከራ ወጥተሽ ወርደሽ እንደ አዉሬ በሌሊት ተጉዘሽ ነዉ እዚህ ቦታ ላይ ሥራ ለማግኘት የምትችይዉ። ሥራ ባገኘሽ ሰዓት ደግሞ አንድ ወር ሰርተሽ የዚያን ዕዳ ሳትከፍይ አሁን ይሄ ነገር መጣ፤ ስለዚህ እኛ ወደ ሀገር አሁን ለመግባት ብንፈልግ ገንዘብ የለንም።»

መንገሻ እና ከ15 ይበልጣሉ ያላቸዉ መሰሎቹ የሳዑዲ መንግሥት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸዉ እዚያ የሚገኙ የዉጭ ዜጎች እንዲወጡ የ90 ቀናት ጊዜ መስጠቱን የሰሙት ወደሀገር ቤት በቅርቡ ደዉለዉ ከቤተሰቦቻቸዉ ነዉ። መረጃ ለማጣራት ወደ ኤንባሲ ደዉለዉ ኤምባሲዉ ወደሚገኝበት ስፍራ መሄድ ካልቻሉ ርዳታ ማግኘት እንደማይችሉ ተነገረንም ይላል። ከመነሻዉ ለዚህ የስደት ሕይወት ያበቃዉ ችግር ቢመለስም መፍትሄ እንደማይኖረዉም ያምናል።

«መንግሥት እዚያ ያደራጀልን ነገር የለም። እኔ ትምህርት እየተማርኩ እያለ ማትሪክ ዉጤት በቀረ ሰዓት መንጃ ፈቃድ አዉጥቼ እየሠራሁ ነበር፤ ግን መንጃ ፈቃድ አዉጥተሽ የማንን መኪና ነዉ የምትነጂዉ? የትኛዉ ድርጅትስ ነዉ የሚቀጥርሽ?»

እነመንገሻ ከሪያድ በእሱ ግምት ከ600 ኪሌ ሜትር በሚበልጥ ርቀት ላይ ነዉ የሚገኙት። እዚያዉ የሚገኝ ሌላዉ ኢትዮጵያዊ ከዚህ ቀደም ሳዑዲ እንደገባ ተይዞ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ ነበር። ዳግም  በተመሳሳይ መንገድ ከመጣ ሁለት ወር ሆነዉ።

«ሀገር ቤት ገብቼም የምሠራዉ የለኝም፤ የገጠር ልጅ ነኝ ትምህርትም አልተማርኩም፤ እናት አባት ማሰቃየት ብቻ ነዉ እንጂ ራሴን የምችልበት ነገር የለኝም።»

ቀድሞ የነበረችዉን ትንሽ መሬት እንዳጣ የሚናገረዉ ይህ ግለሰብ  «ባለፈዉ ወደ ሀገር ቤት በገባን ጊዜ  ለሌባ ተዳረግን» ሲልም ያማርራል።

«ሌባ አዘጋጅቶ ነዉ እንጂ የጠበቀን አንዳንድ ሠርተዉ የገቡትን ሰዎች ለመቀማት ሀገራችን ላይ ስንወርድ ሌላ ምንም የጠበቀን ነገር የለም።»

በሳዉዲ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ሊቀመንበር አቶ ሻዉል ጌታሁን እንዲህ ባለ ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖች መኖራቸዉን እንደሚያዉቁ ቁጥራቸዉም ቀላል እንዳልሆነ ገልጸዉልናል። በእነሱ አቅምም የተወሰኑትን ለመርዳት ሞክረዋል።

«የዕርዳታ ፈላጊዉ ቁጥር እና እኛ ጋር ያለዉ አቅም በምንም መልኩ የሚመጣጠን አይደለም። በጣም ብዙ ሰዉ ችግረኛ ነኝ ባይ ነዉ። ነገር ግን ያንን ሁላ እንረዳለን የምንለዉ ምን ነገር የለም።»

እነመንገሻ እነሱ ያለፉበትን ስቃይ የበዛበት የስደት መንገድ ተከትለዉ የሚመጡ ሌሎች ወገኖቻቸዉን በገንዘብ እየረዱ ነዉ።  አሠሪዎቻቸዉ አሁን በረመዳን የፆም ወቅት ላይ በመሆናቸዉ የመንግሥትን ማሳሰቢያ አልሰሙም ባይባልም እነሱን ግን እንዲሄዱ እንዳልገፏቸዉ ይናገራሉ። ከፆም ፍቺዉ በኋላ ምን ሊከተል እንደሚችል ግን ርግጠኛ አይደሉም። ለወትሮዉ የሚከብደዉ የአሠሪዎቹ ባህሪ የመንግሥት አዋጅ ከመጣሱ ጋር ሲደመር ምን ይዞ እንደሚመጣባቸዉም አያዉቁም። ሁሉንም ለፈጣሪ ትተዉታል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic