ከሳህል ወደ አትላንቲክ አዲሱ የስደት መንገድ  | አፍሪቃ | DW | 09.10.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

ከሳህል ወደ አትላንቲክ አዲሱ የስደት መንገድ 

ከአፍሪቃ ወደ አውሮፓ የሚያሻግሩት የስደት መንገዶች  እየተለወጡ ነው።-ባለፉት ጥቂት ወራት ብቻ ወደ ካናሪ ደሴቶች የመጡ ስደተኞች ካለፉት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር በስድስት እጥፍ ጨምሯል። የኮሮና ቀውስ ለዚህ አንዱ ምክንያት ነው ተብሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:03

የአፍሪቃውያኑ የስደት መከራ አኹንም ቀጥሏል

በርካታ ስደተኞች የሚመላለሱበት ባሕር ዛሬ በሚገርም ሁኔታ ፀጥታ ሰፍኖበታል። ጊኒያዊው ወጣት አብዱል ከሪም ካማራ ከባሕሩ ዳርቻ  ተቀምጦ ባለፈው የበጋ ወቅት  ወደ ስፔን ደሴት ሲመጣ ያጋጠመውን ያስላስላል። ወቅቱ የአትላንቲክ ማዕበል የጨመረበትና ለጉዞ አስጊ ስለነበር፤ ወጣቱ  በላስቲክ ጀልባ ውስጥ ሦስት ቀናትን አሳልፏል፡፡ ጉዞው የተጀመረው ደቡብ ሞሮኮ ሲሆን፤ በተዓምር ከሞት ተርፏል። «ከሚንሳፈፈው የላስቲክ ጀልባ በድንገት አየር ሲወጣ ተሰማን። «በእርግጥ ይህ የአንተ መጨረሻ  ሊሆን ይችላል» የሚል ስሜት ተሰማኝ። በዚያ ወቅት ማሰብ የቻልኩት ብቸኛው ነገር ያለ እኔ ድጋፍ ብቻዋን ስለምትቀረው ታናሽ እህቴ ነበር። በድንጋጤ ደርቄ ቀረሁ።»

በወቅቱ ጀልባው ውስጥ የነበሩ ስደተኞች ፍሳሹን መጠገን በመቻላቸው ፎየርተቬንቱራ የተባለ የስፔን ደሴት  መድረስ ቻሉ። አብዱል ከሪም ካማራ በዚህ ዓመት ካናሪ ደሴቶች ከደረሱ 5,000 ያህል አፍሪቃውያን ስደተኞች መካከል አንዱ ሲሆን ፤ይህ ቁጥር ከ 2019 ጋር ሲነፃፀር ከ 600 በላይ ብልጫ አለው። በአፍሪካ እና በስፔን ደሴቶች መካከል ያለው የስደት መስመር ቀደም ሲል ስደተኞች የሚጠቀሙበት ሲሆን፤ ከ2000 ዓ/ም አጋማሽ ጀምሮ በዚህ መንገድ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ደሴቶቹ መጥተዋል።መንገዱ በዓለም ላይ እጅግ በጣም አደገኛ መሸጋገሪያ በመሆኑ ጥቂት ጀልባዎች ብቻ የሚሻገሩ ሲሆን ፤እንደ ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች መረጃ  እዚህ ቦታ ከ16 ስደተኞች መካከል አንዱ  ይሞታል።

ያም ሆኖ ቦታው እንደገና በተደጋጋሚ መሸጋገሪያ መሆኑ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው።ጄኔቭ ውስጥ በስደት ላይ በሚሰራ አንድ የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ናብራም ፍሮውስ  እንደሚሉት ጉዳዩ  የዓለም አቀፉ ኮሮና ወረርሽኝ ተፅዕኖ ውጤት ነው። «የወረርሽኙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች በእርግጥ ለብዙ ሰዎች የመሰደድ ፍላጎትን ይጨምራሉ።በሌላ በኩል ሰዎችን ይገድባል።ምክንያቱም ለስደት የሚሆን ብዙ ገንዘብ አይኖራቸውም።»

አብዱል ካሪምም በካናሪ ደሴቶች በኩል ለመሻገሩ  ሁለት አጥጋቢ ምክንያቶች አሉት። አንድም በትውልድ ሀገሩ ጊኒ ምንም የወደፊት ተስፋ የለውም። በሌላ በኩል በአትላንቲክ መስመር የህገ-ወጥ ደላሎች  ዋጋ በአሁኑ ጊዜ ርካሽ መሆኑን ተገንዝቧል።ቀደም ሲል  ከ2000 ዩሮ በላይ የነበረው አሁን በ800 ዩሮ በላስቲክ ጀልባ ውስጥ አንድ ቦታ ማግኘት ችሏልና።  ፍሮውስ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የስደት መንገዶች  እየተለወጡ መምጣት ከኮርኖና ጋር  ብቻ የተያያዙ አይደሉም።ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአውሮፓ ሀገራት እንደ ኒጀር እና ሊቢያ ካሉ የመተላለፊያ ሀገሮች ጋር የተለያዩ ስምምነቶች አድርገዋል። የአፍሪካ አገሮች ወደ አውሮፓ የሚያመሩ ስደተኞችን  ሰሜን አፍሪቃ የባህር ዳርቻ ከመድረሳቸው  በፊት ለማስቆም፤ በምላሹ አውሮፓ ለእነዚህ ሀገሮች ከፍተኛ ድጎማዎችን በማድረግ ለልማት ያላቸውን ቁርጠኝነት የማሳደግ ስምምነት አላቸው።ያም ሆኖ እነዚህ ስምምነቶች የስደት መንገገዶች እንዲለወጡ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የላቸውም።በዚህ የተነሳ በካናሪ ደሴቶች ጉዳይ ስፔን የራሷ የፍልሰት ዲፕሎማሲ ሰለባ መሆኗ አያስገርምም ይላሉ ፍሮውስ። 

«ያለፈው ዓመት በሞሮኮ እና በስፔን መካከል የስደተኞች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ በጨመረበት ጊዜ እንኳ፤ ስፔን ከሳምንት በኋላ 30 ሚሊዮን ዩሮ ወደ ሞሮኮ ልካለች።ይህ ነው የፍልሰት ትብብር የሚባለው።» በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ በሚሰራ አንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ባልደረባ የሆኑት ማት ሄርበርት፤ በአንድ ነገር እርግጠኛ ናቸው።ወደፊት ወደ አውሮፓ የሚደረግ  ሰፊ ፍልሰት እንቅስቃሴ ይኖራል።

«በኮቪድ-19 ሳቢያ የሚደረገው አዲስ ፍልሰት የመጀመሪያው ይመስለኛል።  ሕገወጥ ስደተኞች ከምዕራብ አፍሪካ ፣ ከመካከለኛው አፍሪካ እና ከአፍሪካ ቀንድ ወደ ሰሜን አፍሪቃ የባህር ዳርቻዎች  የሚሄዱበት ጊዜ አልነበራቸውም ፡፡ በሚቀጥሉት ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ወራቶች ግን ያ እንደሚሆን ይጠበቃል።»
እንደ ሄርበርት ገለፃ የኮሮና ወረርሽኝ  ኢኮኖሚያዊ ቀውስ  በሰሜን አፍሪቃ ሀገራትም ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ቀደም ሲል ከሰሜን አፍሪቃ ወደ አውሮፓ የሚሻገሩ ስደተኞች በጣም ጥቂት ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ግን  ሰሜን አፍሪካቃውያን  ለስደት ወደ ጀልባ መግባት ጀምረዋል። በዚህ ዓመት ከ 7000 በላይ ቱኒዚያውያን የሜድትራንያንን ባህር ያቋረጡ ሲሆን ይህም  ከ2011 የፀደይ አብዮት ወዲህ ከፍተኛው ቁጥር ነው። አጎራባች ሊቢያም  በአንድ ወቅት ከማዕከላዊ የሜዲትራንያን የመሸጋገሪያ ሀገራት አንዷ የነበረች ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ግን ራሳቸው የሀገሬው ሰዎች የሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎችና የደላሎች ደንበኞች ሆነዋል።

ፀሐይ ጫኔ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች