1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሲሊከን ቫሊ ወደ አፍሪቃ

Eshete Bekeleረቡዕ፣ ነሐሴ 18 2008

መቀመጫቸውን በካሊፎርኒያ ያደረጉ አፍሪቃውያን እውቀት እና ገንዘባቸውን አጣምረው ገበያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማሰልጠኛ ማዕከል የተሰኘ ተቋም በአዲስ አበባ ከፍተዋል። ማሰልጠኛ ማዕከሉ ስራ የሚጀምረው በመስከረም ወር ሲሆን በየሶስት አመቱ ወደ ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች የመስፋፋት እቅድ አለው።

https://p.dw.com/p/1Jp7d
PEEK eye test app EINSCHRÄNKUNG
ምስል Peek

[No title]

መቀመጫውን በሲሊከን ቫሊ ያደረገው ህሩይ አማኑኤል ከኮደርስ ፎር አፍሪካ ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን ገበያ የተሰኘ የሶፍትዌር ፕሮግራሚንግ ማሰልጠኛ በኢትዮጵያ ከፍቷል። ወደ አስራሁለት ሚሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ የተቋቋመው ገበያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማሰልጠኛ ማዕከል አፍሪቃውያን ባለሙያዎችን በዘርፉ በማሰልጠን ከዓለም አቀፍ ደንበኞች ጋር የማገናኘት እቅድ አለው። ቢዎቹን ለጊዜው በኢትዮጵያ ኬንያ እና በሲሊከን ቫሊ ይክፈት እንጂ የደቡብ አፍሪቃ እና የናይጄሪያ ገበያዎች ላይም ትኩረቱን አድርጓል። በኬንያ የሚገኘው ቢሮ የማርኬቲንግ ሥራው ላይ ትኩረት አድርጓል። የአስተዳደር እና የህግ ሰራተኞቹ በሲሊከን ቫሊ ይገኛሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ የማሰልጠኛ ማዕከል ሆናለች። ህሩይ አማኑኤል ተባባሪ መስራች እና ኤ.ጄ ቬንቸርስ የተባለው የመዋዕለ ንዋይ ኩባንያ ባለድርሻ ነው።
«የገበያውን ፍላጎት መሰረት በማድረግ በየስድስት ወራቱ አዳዲስ ስልጠናዎች ይኖሩናል። የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ዴቭ አፕ የተባለው የተንቀሳቃሽ ስልክ አፕልኬሽን እና የዌብሳይት ንድፍ ላይ ያተኩራሉ። እነዚህ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያላቸው የትምህርት አይነቶች ናቸው። የምናመጣቸው መምህራን እና የምናቀርባቸው የትምህርት አይነቶች ከፍ ያለ ደረጃ እና ጥልቀት ያላቸው ናቸው።የምናመጣቸው መምህራን ሙሉ በሙሉ አፍሪቃውያን በመሆናቸው ትምህርቶቹ የአፍሪቃን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ ናቸው።»
Symbolfoto Terrorismus und Social media
ምስል picture-alliance/AP Photo/E. Vucci
ገበያ የተሰኘው ተቋም ሃሳብ ያመነጨው ,ኮደርስ ፎር አፍሪካ (C4A) መሥራች አማዱ ዳፌ አማካኝነት ነው። አማዱ የአፍሪቃ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎችን ከዓለም አቀፍ ደንበኞች ጋር ለማገናኘት መዋዕለ ንዋይ ሲያፈላልግ ከህሩይ አማኑኤል ጋር ተገናኙ። የአማዱ ውጥን አፍሪቃውያን ባለሙያዎች በዓለም አቀፉ ገበያ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ትምህርት እና ስልጠና መስጠት፤ባለሙያዎቹንም ከደንበኞች ጋር ማገናኘት ነው። አማዱ ኮደርስ ፎር አፍሪቃ በተሰኘው ኩባንያው በኩል በተለያዩ የአፍሪቃ አገሮች ለባለሙያዎች ስልጠናዎችን አቅርቧል። ህሩይ በበኩሉ በሲሊከን ቫሊ በሚገኘው ኩባንያው ለአዳዲስ ኩባንያዎች መዋዕለ-ንዋይ ያቀርባል። ህሩይ ገበያ የተሰኘው አዲስ ኩባንያ ከመመስረቱም በፊት በኢትዮጵያ ገበያ የመሰማራት ፍላጎት እንደነበረው ይናገራል።
« የአገሪቱን ለውጥ ለመታዘብ ችያለሁ። ወደ አገሩ የሚመለሰው ዲያስፖራም ቢሆን ዘላቂ ጥቅም በሚሰጡ የስራ ዘርፎች ላይ ሲሰማራ አይታይም። ወደ ኢትዮጵያ መጥተው መጠጥ ቤት፤ ሆቴል፤ ምግብ ቤት የመሰሉ ለመስራት ቀላል የሆኑ ስራዎች ላይ ይሰማራሉ። ይህ ለትርፍ በጣም ቀላል ነው። አሁን ኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገች ነው። ስለዚህ ለእኔ እና ለስራ አጋሮቼ ገንዘብ አሊያም ትርፍ ዋንኛ አላማችን አይደለም። የተለየስራ መስራት ስለፈለግን ነው በትምህርት ላይ መዋዕለንዋያችንን ያፈሰስንው። በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በተለይም በቴክኖሎጂው የጥራት ጉድለት ይታያል። ቢሮክራሲውን ጨምሮ በርካታ ችግሮች አሉ። ምንም አይነት ስራ በኢንተርኔት ማከናወን አይቻልም። አንድ ወረቀት ለማግኘት በየቀኑ ከቢሮ ወደ ቢሮ መዞር ያስፈልጋል። ወደዚህ የመጣንው ለገንዘብ ስንል ባለመሆኑ እነዚህ እኛን ተስፋ አያስቆርጡንም።»
አፍሪቃ በዓለም አቀፉ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ገበያ ያላት ድርሻ እጅጉን ውስን ነው። ህሩይ ግን ከአንድ ቢሊዮን በላይ ዜጎች ያላት አፍሪቃ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ገበያ ለውጥ ታመጣለች የሚል እምነት አለው። በኢትዮጵያ ያለው ውስን እና ደካማ የኢንተርኔት መሰረተ-ልማትም በሒደት ይለወጣል የሚል ተስፋ አሳድሯል።
«የኢንተርኔት ግንኙነት ችግሩ በጊዜ ሒደት ይፈታል። ይሻሻላል። በኢትዮጵያ ስራ ለመጀመር አሁን ሁነኛው ጊዜ ነው። እንደ ማንኛውም የስራ አይነት ነገሮች ዝቅተኛ በሆኑበት ጊዜ መጀመር አዋጪ ነው። በኢትዮጵያ ያለው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ገበያ ያላደገው እና የማይታወቀው በኢንተርኔት ግንኙነት ችግር እና በስልጠና ያለመኖር ነው። ሰዎች በኢትዮጵያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን ያመርታሉ። ነገር ግን በዓለም አቀፍ ገበያ የሚያስፈልገው የጥራት ደራጃ ላይ አልደረሱም። ሁሉም ሰው በፈለገው መንገድ ነው የሚሰራው። ድረ-ገጾች እንኳ ሁሉም ሰው እንደፈለገው ነው የሚሰራቸው። እኛ ለማድረግ እየሞከርን ያለንው የጥራት ደረጃውን የደንበኞችን ፍላጎት ማሟላት ወደ ሚያስችል ደረጃ ከፍ ለማድረግ ነው። የኢትዮጵያ ገበያ በሚፈለገው ደረጃ ባለማደጉ የምናሰለጥናቸውን ባለሙያዎች ከዓለም አቀፍ ደንበኞች ጋር ለማገናኘት ነው ጥረት በማድረግ ላይ ያለንው። ባለሙያዎቹን ካሰለጠንን በኋላ በመላው አፍሪቃ በሚገኙ የሥራ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ እናደርጋለን።»
የኢትዮጵያ መንግስት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍን ለማሳደግ በሰኔ 2015 ዓ.ም የአይ.ሲ.ቲ. መንደር ግንባታ ጀምሯል። መንደሩ ዘርፉን ለማሳደግ እና አገር በቀል ለሆኑ ጀማሪ ኩባንያዎች የሥራ ከባቢ ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተገልጧል። የስልጠና ማዕከሉን በአዲስ አበባ የከፈተው ገበያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ስልጠና ማዕከል ሰልጣኞችን በመስከረም ወር መቀበል ይጀምራል። ተቋሙ በሚያቀርባቸው ስልጠናዎች የቅንጡ ስልኮች ማስተናባሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የትምህርት አይነቶች እንደሚጀምርም አስታውቋል። ከዚህ በተጨማሪ ሰልጣኞች አሰፈላጊ የቋንቋ፤የደንበኞች ግንኙነት እና የንግድ ሥራ ትንተናዎችም ያገኛሉ።
« ዋንኛ ትኩረታችንን በኬንያ፤ደቡቡብ አፍሪቃ እና ናይጄሪያ ላይ አድርገናል። የመረጥናቸው አገሮች ከፍ ያለ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ገበያ እና አገልግሎት ያላቸውን ነው። የማሰልጠኛ ማዕከላችን ዋና ቢሮ ግን ኢትዮጵያ ላይ ይሆናል።»
DW Shift Internet Telefonie
ምስል BR
ገበያ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ዋንኛ ትኩረት ለአፍሪቃውያን ወጣቶች ከፍ ያለ ጥራት ያለው ስልጠና ማቅረብ ይሁን እንጂ ሰልጣኞችን ከደንበኞች ጋር በማገናኘት ትርፋማ ለመሆን አቅዷል። ኩባንያው ሊከተለው ያቀደው የአሰራር ስልት ህንድ እና ቻይናን የመሰሉ አገሮች ከዩናይትድ ስቴትስ እና አውሮጳ ደንበኞች ሥራ የሚቀበሉበትን አሰራር ይመስላል። ወጣቶቹ ዓለም አቀፉ ገበያ የሚፈልገውን ደረጃ ያሟላ ስልጠና እና እውቀት የሚገበዩት አፍሪቃውያን ወጣቶች ባሉበት ሆነው ከደንበኞች ጋር የሚገናኙበት ስራቸውንም የሚሰሩበት ስልት ነው።
«ትምህርት ቤቱ የፓን አፍሪካን አካዳሚ ነው የሚሆነው። ኮደርስ ፎር አፍሪካ ከተባለው ድርጅት ጋር በጥምረት ነው የምንሰራው። የሶፍትዌር ስራዎችን በመላው አፍሪቃ ይሰራሉ። ከተለያዩ የአፍሪቃ አገሮች በርካታ የስራ ጥያቄዎች ይቀርቡላቸዋል። ስራውን ተቀብለው ከአፍሪቃውያን ባለሙያዎች ጋር ያገናኛሉ። ስራዎቹ ዓለም አቀፍ ጭምር ናቸው። ይሁንና የደንበኞቻቸውን ፍላጎት በፈለጉት ፍጥነት ማሟላት አልቻሉም። በቂ ባለሙያዎች የሏቸውም። አሁን በየቀኑ ከአስር እስከ አስራ አምስት የሶፍትዌር ባለሙያዎች ፍለጋ ጥያቄ ከደንበኞች ይቀርብልናል። አሁን ባለው ሁኔታ በፍጥነት ይህን ማቅረብ አንችልም። ለዚህም ነው ትምህርት ቤቱን ወደ መመስረት ያመራንው። ወደ ፊት እራሳችን ባለሙያዎቹን በማሰልጠን ከደንበኞች ጋር እናገናኛቸዋለን። ሀሳባችን በየሶስት አመቱ ወደ ሌሎች የአፍሪቃ አገሮች መስፋፋት ነው። የሚቀጥለው እቅዳችን ከምስራቃዊው አፍሪቃ ወደ ምዕራብ ይሆናል። በሚቀጥሉት አምስት አመታት አምስት ሺ ተማሪዎች ለማስመረቅ አቅደናል።»
ህሩይ ወደ ስራቸው ከመግባታቸው በፊት የአህጉሪቱን ፍላጎት ማጥናታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል። የኩባንያው የገበያ ጥናት ባለሙያ ሙቶኒ ንኮይ አፍሪቃ የኢንዱስትሪ አብዮቱ ቢያመልጣትም አዲሱ ትውልድ ግን የዲጂታል ቴክኖሎጂው አብዮት እንዲያመልጠው አይፈልግም የሚል እምነት አለው። ህሩይ የኢንፌርሜሽን ቴክኖሎጂ ባለሙያዎች ለስራቸው የሚያስከፍሉት ዋጋ ውድ እየሆነ መምጣት ለእነሱ መልካም አጋጣሚ እንደሆነ ያምናል።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ