ከሰሞኑ፦ የወለጋው እገታ፤ የጌታቸው አሰፋ ጉዳይ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 04.01.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ከሰሞኑ፦ የወለጋው እገታ፤ የጌታቸው አሰፋ ጉዳይ

የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ በኢትዮጵያ ያለው የሰላም እና መረጋጋት እጦት ለብዙዎች አሳሳቢ እንደሆነ አለ። እዚህም እዚያም የሚቀሰቀሱ ግጭቶች በርካቶችን ለሞት፣ ለጉዳት እና መፈናቀል ዳርጓቸዋል። በኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞን ይህ ችግር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጎልቶ ከሚታይባቸው አካባቢዎች አንዱ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:14

ከሰሞኑ፦ የፕሬስ ሴክረተሪ ሹመት አነጋግሯል

በወለጋ አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ የሚባሉ ታጣቂዎች ይፈጽሙታል በሚባለው ጥቃት በየዕለቱ የሰው ህይወት እያለፈ እና ንብረት እየወደመ እንደሚገኝ የኦሮሚያ ክልል በየጊዜው ባወጣቸው መግለጫዎች አስታውቋል። በወለጋ እና በሌሎች የአሮሚያ አካባቢዎች ያሉ ጥቃቶችን ለመቆጣጠር ወደ ቦታዎቹ የመከላከያ ሰራዊት እንደተሰማራ ቢነገረም በክልሉ ሰላም መድፍረሱ አሁንም ቀጥሏል።

የኦሮሚያ ክልል ገዢ ፓርቲ (ኦዲፒ) በተለይ በወለጋ እና ጉጂ ለሚፈጸሙ ጥቃቶች በዋናነት ጣቱን የሚቀስረው በኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ላይ ነው። የኦሮሞ ፖለቲካን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ሁለቱ የፖለቲካ ድርጅቶች መቆራቆሳቸውን ትተው እንታገልለታለን ለሚሉት ህዝብ በአንድነት እንዲሰሩ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ሲወተውቱ ቆይተዋል። በክልሉ ከሰሞኑ የተከሰቱ ሁነቶች ግን በኦነግ ላይ መረር ያሉ አስተያየቶች እንዲሰነዘሩ ምክንያት የሆኑ ይመስላሉ። 

ሰለሞን ደቻሳ የተባሉ የፌስ ቡክ ጸሀፊ ከኤርትራ የተመለሰውን የኦነግ አንጃ የሚመሩትን አቶ ዳውድ ኢብሳን በስም ጠቅሰው ትችታቸውን አስፍረዋል። “መንግስት እንኳን ተሳስቶ ቢሆን ዳውድ ኢብሳ በፍፁም ከመንግስት ሃይል ጋር ጦርነት መግጠም አልነበረበትም። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። ዳውድ ኢብሳ በጦርነት አሸንፎ አይደለም የመጣው። ሰውዬው እንዴት አዙሮ ማሰብ ተሳነው? ለ27 አመት ያልተደረገ ጦርነት እንዴት አሁን ይደረጋል? በምንም ሎጂክ ለመቀበል ይከብዳል” ሲሉ ጽፈዋል። የኦዲፒ ደጋፊው ደረጀ ገረፋ በኦነግ በኩል የሚታየው አካሄድ “ያሳዝናል” ባይ ናቸው። ረዘም ካለ ጽሁፋቸው ተከታዩን ቀንጭበናል። 

“ከዚህ በፊት ‘ኦነግ የተወሰኑ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ በሚቀጥለው ምርጫ ቢቀርብ፣ ያለውን ገናና ስም ተጠቅሞ መንግስትን የመፈተን እድሉ እጅግ ሰፊ ነው። ኦነግ 27 ዓመት ሙሉ ካደረገው የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ልቆ የሚገኘው በ1983 እና 84 በአንድ ዓመት ውስጥ ያደረገው ሰላማዊ እንቅስቃሴ እጅግ የገዘፈ ነው። ስለዚህ ታጣቂዎቻችሁን አስፈቱ እና ካድሬ በማድረግ ወደ ህዝብ ልቀቁ። እስከዚያም ሽግግሩን አግዙ’ ብንል‘እንከላከላለን’ አላችሁ። በቃ መንግስት ህግን አስከብራለሁ ካለ እና እናንተ ደግሞ እንከላከላለን ስትሉ አፍረን እና የምንለውን አጥተን ዝም አልን። ያው እየሆነ ያለው ይታወቃል።

አሁን ደግሞ ሰሞኑን መከላከያ እና የኦሮሚያ ፖሊስ የህግ የበላይነትን ለማስከበር ሲንቀሳቀሱ በአንዳንድ አካባቢዎች የህወሓት ታጣቂዎች ጭምር ተይዘዋል ስንል መጀመሪያ ነጠላ አዘቅዝዝቀው ለቅሶ የጀመሩት የኛዎቹ ጉዶች ናቸው። እኛ በዚያ አከባቢ ትክክለኛው ኦነግ አይንቀሳቀስም አላልንም። ወይም በኦነግ ስም የሚንቀሳቀሱት የህወሃት ታጣቂዎች በኦነግ መልካም ፈቃድ እና ተዋህደው እየተዋጉ ነው አላልንም። እሱን የሚያውቀው መንግስት፣ ህወሓት እና እናንተ ናችሁ። እኛ እስካሁን ያለን መረጃ እዚያ አልደረሰም። እናንተ ግን አለቀሳችሁ። ለምን?” ሲሉ ደረጀ ገረፋ ጠይቀዋል። 

ጎራ ለይቶ የሚደረገው ክርክር በተጋጋለበት በዚህ ሳምንት በወለጋ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አሳሳቢነትን የጠቆመ መረጃ የማህበራዊ ድረ ገጾችን አጨናንቆት ነበር። በታዋቂ አራማጆች (አክቲቪስቶች) እና የማህበራዊ ድረ ገጽ ጸሀፊያን አማካኝነት ትላንት የወጣው መረጃ  የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ደለሳ ቡልቻ በታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን ይፋ አድርጓል። ዶ/ር ደለሳ ከትናንት በስቲያ ከደምቢ ዶሎ ወደ አዲስ አበባ ለሥራ በመምጣት ላይ እያሉ በቄለም ወለጋ ዞን ሀዋ ገላን ወረዳ በገባ ሮቢ ከተማ በአካባቢዉ በሚንቀሳቀሱ ህገ ወጥ ታጣቂዎች ከሹፌራቸው ጋር መታገታቸውን የኦዲፒ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ዘግየት ብሎ አረጋግጧል።

ተፈጸመ የተባለው እገታ በበርካታ የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ተወግዟል። መንግስቱ ዲ. አሰፋ የተባሉ የፌስ ቡክ ጸሀፊ “አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፕሬዚዳንት በታጠቀ ኃይል ሲታገት፣ መንግሥት ዝምታ ሲመርጥ መቼስ ምን ይባላል?!” ሲሉ ግርምታቸውን አካፍለዋል። “እንደው በእንደዚህ ዓይነት ዓይን ያወጣ የሽብር ሥራ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ምንድነው? የትግል ግቡስ ምን ሲሆን ነው ለሕዝብ እታገላለሁ የሚል ተቋም ወይም ድርጅት እንዲህ ዓይነት ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚፈጽመው? አደገኛ አዝማሚያ ነው። መንግሥት አስቸኳይ መፍትሔ ማፈላለግ አለበት፣ ለሕዝብም ስለጉዳዩ በግልጽ ሊናገር ይገባል” ብለዋል። 

ቲዲም ኮስ ተክሌ ደግሞ በዚያው በፌስ ቡክ “የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መታገቱን እየሰማን ነው። ይህ እውነት ከሆነ መቼስ ከዚህ በላይ የሚያሳፍር ድርጊት ይኖራል ብዬ አላስብም። ጌታቸው አስፋ መቀሌ ነው አልተባለም ነበር? ወለጋ ምን ይሠራል? አሁን ጥያቄው መንግስት በቀጣይ በዚህ የሽብር ቡድን ላይ ምን አይነት እርምጃ ይወስዳል የሚለው መሆን አለበት” ሲሉ ጽፈዋል። እርሳቸው በአስተያየታቸው የጠቀሷቸው የቀድሞው የደህነንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ እንደ ኦነግ ሁሉ ለበርካታ ሳምንታት መነጋገሪያነታቸው አልበረደም።

 ያሉበት ትክክለኛ አድራሻም ሆነ መልካቸው በግልጽ የማይታወቀው የአቶ ጌታቸውን ጉዳይ ወደ ሰሞነኛ አጀንዳ ያመጣው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ መረጃ ነው። ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ለተወካዮች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጻም ሪፖርት ባለፈው ማክሰኞ ሲያቀርቡ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ  የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል አቶ ጌታቸውን አሳልፎ እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረቡን ገልጸዋል።  

ቶፊቅ ከበደ በፌስ ቡክ ገጻቸው “ጌታቸው አሰፋን በቁጥጥር ስር ለማዋል የትግራይ ክልል ፍቃድ አያስፈልግም”ሲሉ ተከራክረዋል። “ምክትሉ ያሬድ ዘሪሁን ተይዞ ፤ ትግራይ የተወሰነ ወታደራዊ አቅም ስላጎለበተች አለቃውን (ጌታቸው አሰፋ) መያዝ ካልተቻለ ለጉልበተኛ የህግ የበላይነት ላይሰራ ነው ማለት ነው። የጌታቸው ጉዳይ ፈጣን መቋጫ ያስፈልገዋል” ብለዋል።  እጥፍ ወርቄ መላኩ በትዊተር “ጌታቸው አሰፋ ማደኛ ወጣበት። ግን ማን ቀድሞ ትግራይ ገብቶ ያምጣው? በሌሉበት የሚከሰሱ ሰዎች ድሮ ብዙ ነበሩ። ዘንድሮ  እስር ቤት በሌሉበት መክሰስ አይቻልም ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።  አብዱሰላም ማዕሩፍ “ጌታቸው አሰፋ የህሊና እረፍት የሚያገኘው ፍርዱን ሲያገኝ ብቻ ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው አስተያየታቸውን አጋርተዋል።

አስፋው ገዳሙ በዚያው በትዊተር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቀድሞው የደህንነት መስሪያ ቤት ኃላፊ ላይ ያራምዱታል ያሉትን አቋም በንጽጽሮሽ ተችተዋል። “መንግስቱ ኃይለ ማርያም ወደ ሀገሩ ተመልሶ በሰላም እንዲኖር ህገመንግስቱ ይታያል ያሉን ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ‘ጌታቸው አሰፋ ካልታሰረ እንቅልፍ የለኝም’ ማለታቸው ‘ለሰብአዊ መብት ተቆርቁሬ ነው’ ቢሉ እንዴት ይዋጥልኝ? ይልቅ ጌታቸውን ፈራሁት ቢሉ ምክንያታዊ ይሆናሉ” ብለዋል። ኃይላይ አለም የተባሉ የፌስ ቡክ ጸሀፊ “አቶ ጌታቸው አሰፋ የአገሩን ደህንነትና ሰላም አስጠብቆ በማስቆየቱና ለሰራው የላቀ አሰተዋፅኦ በኢትዮጵያ መንግስት ሊሸለም ይገባል” ሲሉ በፌደራል መንግስት የሚፈለጉትን የቀድሞ የመንግስት ባለስልጣን አሞካሽተዋል። 

በማህበራዊ ድረገጾች ሰሞነኛ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የፕሬስ ሴክረተሪ ሹመት ጉዳይ አንዱ ነው። በጽህፈት ቤቱ ስር ያለው የፕሬስ ሴክሬተሪያት የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤትን ተግባር እና ኃላፊነትን በመተካት የዛሬ ሶስት ወር ግድም ነበር የተቋቋመው። ለቦታው በኃላፊነት የተመደቡት ቢልለኔ ስዩም በየጊዜው በማህበራዊ ድረገጾች መነጋገሪያ ሲሆኑ በመቆየታቸው አዲስ ሰው ተሾመ መባሉ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ተጠቃሚዎች ዘንድ ትኩረትን ስቧል።

የፕሬስ ሴክሬተሪያት ኃላፊነቱን ሹመት ያገኙት የቀድሞው የአማራ ክልል የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን መሆናቸው በመንግስት እና ለመንግስት ቅርበት ባላቸው መገናኛ ብዙሃን ቢዘገብም ዘግየት ብለው የወጡ መረጃዎች ግን ተያይዘው የወጡ መረጃዎችን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ከትተውታል። በማህበራዊ ድረገጾች የተለቀቀው የአቶ ንጉሱን ሹመት የሚያመለክተው ደብዳቤ ምደባቸው ከጥር 22 ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንደሚሆን ማሳየቱም ተጨማሪ ጥያቄ ወልዷል።

የሹመቱ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለDW ያረጋገጡት አቶ ንጉሱ የእርሳቸው ምክትል ሆነው ተመድበዋል ስለተባሉት ስለ አቶ ካሳሁን ጎፌ ሹመትም ሆነ ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል ስለተባሉት ቢልለኔ ስዩም መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ምንጮችም የፕሬስ ሴክረተሪ ቢልለኔ ስዩም እና ምክትላቸው ሄለን ዮሴፍም ከሥራ መደባቸው እንዳልተነሱ እና አሁንም በስራቸው ላይ እንደሚገኙ ለDW ገልጸዋል። 

እስካሁንም ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ያልተሰጠበት የፕሬስ ሴክረተሪ ሹመት ጉዳይ በማህበራዊ ድረገጾች አወያይቷል። ቢልለኔ ከቦታቸው ተነሱ መባላቸውን “ትክክለኛ ውሳኔ ነው” ሲሉ ከጻፉ ውስጥ ታምሩ ሁሊሶ ይገኝበታል።  ታምሩ በፌስቡክ ገጹ“የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ወይዘሪት ቢልለኔ ስዩምን በማንሳት አቶ ንጉሱን በቃል አቀባይነት መተካቱ ከስህተቱ ፈጥኖ የሚታረም መሆኑን ያሳየበት ነው” ሲል አዲሱን ሹመት አድንቋል። 

ኪራም ታደሰ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም በኃላፊዋ ዙሪያ የነበረው ውዝግብ አስታውሰው በፌስ ቡክ አስተያየታቸው አጋርተዋል። “በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የሴክሬታሪ ኃላፊ ‘ሹም ሽር’ በሚል ተያይዞ እዚሁ ‘ፌስቡክ’ ላይ በተለይ በወንዶች ፊት አውራሪነት እና የሴቶቹን ማቀርቀር አድፍጠው በሚደግፉ ሴቶች ጭምር የሚዘዋወረው [ጽሁፍ] ግር የሚያሰኝ ይመስላል፡፡ የአብዛኞቹ ‘የፌስቡክ’ ተቺዎች መነሻ ሆኖ የታየው የቢልለኔ ካለ ቅፅል መጠራት መፈለግ ነው፡፡ ጎበዝ - ወንዳዊነት ክፉኛ የተጠናወተው ማህበረሰብ ለኪሳራ ቢዳረግ እንጂ ጠብ የሚል ውጤት አምጥቶ እንደማያውቅ የስልጡን ዓለም ተሞክሮ ያስተምረናል” ብለዋል።

ተስፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic