ከሰሞኑ፦ የአቶ ለማ ንግግር፣ የለገጣፎ ጉዳይ፣ አድዋ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 01.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ከሰሞኑ፦ የአቶ ለማ ንግግር፣ የለገጣፎ ጉዳይ፣ አድዋ

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በአንድ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር፣ የለገጣፎ ቤት ማፍረስ ዘመቻ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የእራት ምሽት መርኃ ግብር እና የአድዋ በዓል መታሰቢያ በዚህ ሳምንት በማህበራዊ መገናኛዎች አበይት መነጋገሪያ የነበሩ ጉዳዮች ናቸው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:44

ከሰሞኑ፦ የአቶ ለማ ንግግር፣ የለገጣፎ ጉዳይ፣ አድዋ

አወዛጋቢ ፖለቲካዊ አጀንዳዎች ፌስ ቡክ እና ትዊተርን በመሰሉ በኢትዮጵያውያን ዘንድ በሚዘወተሩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሳምንት ከሳምንት አይጠፉም። አንዱ ሲሄድ ሌላ ይመጣል። አንዱ ገና በቅጡ ሳይረግብ ሌላው በእግሩ ተተክቶ ያከራክራል፣ ያፋጫል፣ ያነታርካል ባስ ሲልም ያሰዳድባል። በዚህ ሳምንትም የሆነው ይህ ነው። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የለገጣፎ ቤቶች መፍረስ ጉዳይ እምብዛም ሳይደበዝዝ ነበር በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የተሰራጨው የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ንግግር ከፍ ያለ ውዝግብን የወለደው።

አቶ ለማ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በሌሎች ቦታዎች ላይ ስለሰፈሩ የኦሮሞ ተወላጆች ለታዳሚያኑ በኦሮምኛ ያቀረቡት ማብራሪያ ነበር የውዝግቡ መነሻ። “ርዕዮት” በተሰኘ የብዙሃን መገናኛ ወደ አማርኛ የተመለሰው ይሄው የፕሬዝዳንቱ ማብራሪያ “ቲም ለማ” ተብለው የሚታወቁትን የኢህአዴግ አመራሮች “ድብቅ አጀንዳ ያጋለጠ ነው” በሚል ብዙዎች ተቀባብለውታል። ከአተረጓጎሙ ትክክለኛነት እስከ ከአውድ ውጭ የመወሰድ ጉዳይ አንስተው የተከራከሩም ነበሩ። 

በጉዳዩ ላይ የነበረው ውዝግብ እና አተካሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ ነው የሚባልለትን የኢትዮጵያውያን የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የውይይት ባህል አንድ ማሳያ ሆኗል። በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን መምህር አቶ ክብሮም ብርሃነ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ላይ ያተኮሩ ጥናት ቀመስ ጽሁፎችን ለንባብ አብቅተዋል። በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋለው ባህል ፈረንጆቹ “confirmatory thought” የሚሉት አይነት መሆኑን ያስረዳሉ። ከአቶ ለማ ንግግር ጋር ተያይዞ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተስተዋለውም ይህንኑ አካሄድ የተከተለ ነው ይላሉ። 

አቶ ለማ በሚያስተዳድሩት የኦሮሚያ ክልል ስር ባለው ለገጣፎ ከተማ በህገወጥ መንገድ ተገንብተዋል በተባሉ ቤቶች ላይ የተወሰደው የማፍረስ ዘመቻ በዚህ ሳምንትም መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የቤት ማፍረስ ዘመቻውን አስመልክቶ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በነበረ ስብሰባ ላይ የተናገሩትም ትችት አስከትሎባቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ለገጣፎው ዘመቻ “ሲታቀድ፣ ሲሰራም አልሰማሁም፤ ሲፈጸምም አላውቅም። ምክንያቱም ከተማ ስለማላስተዳድር የእኔ ስራ አይደለም። ነገር ግን ህዝቡ በሙሉ አብይ ብሎ ነው የጮኸው። ትክክል ነው። ከእኔ የሚጠብቀው ነገር አለ ማለት ነው። ማስተካከል አለብህ ብሎ የሚያስበው ነገር ስላለ ነው” ብለው ነበር። 

ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ምላሽ ዘሚካኤል ኤም የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ “ኮሚክ” ብለውታል። “ለገጣፎ ቤት እንደፈረሰ አታውቅም ግን ሰው ሁሉ አንተ ላይ እንደጮህ ታውቃለህ። ለገጣፎ ላይ ስልጣን የለኝም ትላለህ፤ ቤቶቹ እንዲፈርሱ ግን ትዕዛዝ የሰጠው አንተ በሊቀመንበርነት የምትመራው ድርጅት ነው” ሲሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ውስጥ ያለውን ተቃሮኖ ለማሳየት ሞክረዋል። መልካም ሰው ሞላ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም “እኔን ያልገባኝ ለገጣፎ የሚደረገውን ሳይሰማ ወቀሳውን እንዴት ሰማ?” ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየታቸውን በጥያቄ መልክ አቅርበዋል። 

ሰናይ አማረ በዚያው በፌስ ቡክ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “የለገጣፎን ጉዳይ አልሰማሁም ያሉት ከወቀሳ ለማምለጥ” እንደው ጠይቀዋል። “እርሳቸው የአንድ ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትር ናቸው። ሲቀጥል የኦህዴድ [ኦዲፒ] ሊቀመንበር ናቸው። ኦሮሚያ ላይ በክልል ደረጃም በከተማ ደረጃም ማንኛውም ትላልቅ በተለይም በለገጣፎ የተሰራውን የህግ ማስከበር አይነት ፓለቲካዊ ውጥረት የሚፈጥሩ ውሳኔዎች የድርጅቱ ሊቀመንበር ሳያውቅ፣ የስራ አቅጣጫ ሳይሰጥ የማስፈጸም ተግባር ውስጥ አይገባም” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተጠያቂነት እንደማያመልጡ በጽሁፋቸው አመልክተዋል። 

በዚህ ሳምንት ሌላው መነጋገሪያ የነበረው ጉዳይም ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የአዲስ አበባ ከተማን ለማስዋብ ለታቀደ ፕሮጀክት ገቢ ለማሰባሰብ “ገበታ ለሸገር” የተሰኘ የእራት ምሽት መዘጋጀቱን ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ይፋ አድርጓል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የተጠነሰሰው ይህ ፕሮጀክት አዲስ አበባን የሚያቋርጡ ሁለት ወንዞች ዳርቻዎችን ተከትሎ ተግባራዊ የሚደርግ ሲሆን 56 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሸፍን ታስቧል።

 እስከ 29 ቢሊዮን ብር ያስወጣል ለተባለው ለዚህ ፕሮጀክት ገቢ በሚውለው የእራት ምሽት ላይ የንግድ ድርጅት ባለቤቶች፣ የኩባንያ ሥራ አስፈጻሚዎች ፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች እና የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት እንዲገኙ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጥሪ ቀርቦላቸዋል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በአንድ ገበታ ለመታደም የተጠየቀው ዋጋ ግን የበርካታ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎችን ቀልብ ስቧል። ለእራት በግለሰብ አምስት ሚሊዮን ብር መጠየቁ ያልተዋጠላቸው እንዳሉ ሁሉ እንዲህ አይነት ገቢ ማሰባሰቢያ የተለመደ መሆኑን አንስተው የተከራከሩም አልጠፉም።

አላዩ ገረመው በፌስቡክ “የዓለማችን ውዱ እራት አዲስ አበባ ላይ ተደግሷል” ሲሉ የእራቱ ዋጋ በውጭ ምንዛሬ ሲሰላ 178 ሺህ 571 ዶላር እንደሚያወጣ ጠቁመዋል። ናትናኤል ጋሻው የፕሮጀክቱን ዜና በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ ያጋሩት “መቀለዱ ነው?” ከሚል ጥያቄ ጋር ነበር። አያይዘውም “ይኽ ፕሮጀክት ለገጣፎ ላይ [ቤት] ለፈረሰባቸው ዕምባ ማበሻ ቢሆን መልካም ነበር” የሚል አስተያየታቸውን አስፍረዋል። 

ሳሙኤል ብዙነህ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ፕሮጀክቱን “ወቅቱን እና ጊዜውን ያላገናዘበ የመናፈሻ ግንባታ” ሲሉ ጠርተውታል። አምስት ሚሊዮን ብር ከፍለው እራቱን የሚታደሙት ግለሰቦች ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ አንስተው “አሁን ያለው የሀገሪቱ የንግድ እና የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንደሆነ እንኳን አምስት ሚሊየን ብር ቀርቶ አምስት ሺህ ብርም ከፍሎ ራት ለመብላት የሚጋብዝ፣ የሚያበረታታ እና እድል የሚሰጥ አይደለም” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ያሰናዱትን አይነት “የበጎ አድራጎት ምሳ እና እራት ግብዣዎች በተለይ በምዕራቡ ዓለም የተለመዱ ናቸው” ሲሉ የሚንደረደሩት ሌላኛው የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ዮናስ ሀጎስ “በጣም ጥሩ የሚባል የገቢ ማሰባሰብያ ዘዴ ነው” ሲሉ መሰል አካሄዶችን ያሞካሻሉ። በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ግን “የእራት ግብዣው የታቀደለት የወንዝ ዳር መናፈሻ ፕሮጀክት ቅንጦት ነው” ከሚሉ ወገኖች ጋር እስማማለሁ ይላሉ። “በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ባሉባት ሐገር ውስጥ፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቧ አፋጣኝ የምግብ እርዳታ የሚሻ ሆኖ ሳለ ይህን ፕሮጀክት መዘርጋት ቅንጦት ሊመስል ይችላል” የሚሉት ዮናስ “ገንዘቡ ለየትኛውም ዓላማ ቢዋጣና ቢለገስ ዓላማውን የመፈፀሙ ቅንነት በአስተዳዳሪዎቹ ዘንድ ስለሌለ የእራት ግብዣው ዓላማ ብዙ የሚያሳስብ ጉዳይ አይሆንም” ሲሉ ደምድመዋል። የፕሮጀክቱ እውን መሆን ያጠራጠራቸው የሚመስሉት ፉአድ ሁሴን “እስቲ ዕድሜ ይስጠን እናይዋለን - እንደ ባቡሩ” ብለዋል በፌስቡክ።

የዕለቱን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት የምናጠቃልለው በሳምንቱ ውስጥ ሰፊ ሽፋን ስላገኘው በአድዋ በዓል ይሆናል። ቀደም ባሉት ዓመታት አንድ የመወዛገቢያ አጀንዳ የነበረው የአድዋ ድል መታሰቢያ ዘንድሮ እምብዛም ሙግት ሲፈጥር አልተስተዋለም። የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች በዓሉ ከመድረሱ ቀናት አስቀድሞ በተለያየ መልኩ እያከበሩት ይገኛሉ።በርካቶች የአድዋ ጦርነት ዘመቻውን ታሪክ መዘከር መርጠዋል። ገሚሶቹ ደግሞ ዳግማዊ አጤ ምንሊክ የሚታወቁበትን የራስ መሸፈኛ እና ባርኔጣን አድርገው ፎቶ በመነሳት አስታውሰዋቸዋል። ስለ አድዋ የተቀነቀኑ ዘፈኖች እና ስለ ድሉ የተደረደሩ ስንኞችንም ብዙዎች በየገጾቻቸው አጋርተዋል።  

አሼ ሀመሩ የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ስለ አድዋ ተከታዩን በፌስ ቡክ ገጻቸው ብለዋል። “ኢትዮጵያውያን በብዙ ነገር ወደኋላ ብንቀርም ቢያንስ ባህላችን፣ ሃይማኖታችን፣ የህዝባችን ስነልቦና፣ በቅኝ ግዛት ባለመበላሸቱ ደስተኛ ነኝ። ዛሬ በብዙ መንገድ የምንኮራበት ባህል እና ቋንቋ ሳይጠፋ የጠበቀን በአባቶቻችን የደም መሰዋትነት ነው። የአባቶቻችን ተጋድሎ እና መሰዋትነት የሚዘከር፣ የሚወደስ፣ የሚከበር ነው። ክብር ለእናንተ። እንኳን ለጥቁር ህዝብ ኩራት እና መከታ ሆናችሁ” ሲሉ አወድሰዋል። 

ተስፋለም ወልደየስ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
   
  

Audios and videos on the topic