1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

ከሰሞኑ በምሥራቅ ወለጋ እገታ፣ ግድያ እና የጥቃቶች መደጋገም

ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2017

በምሥራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ገሊላ ወረዳ ከፊጤ በቆ ከተማ ተነስተው ወደ አንገር ጉቲን ከገበያ በመመለስ ላይ የነበሩ አራት ወጣቶች በታጣቂዎች ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ ሁለቱ መገደላቸውን ቤተሰቦች ለዶቼ ቬለ ገለጹ።

https://p.dw.com/p/4nUxJ
ኪረሙ ከተማ
ምሥራቅ ወለጋ ኪረሙ ከተማ ፎቶ ከማኅደር ምስል Privat

ከሰሞኑ በምሥራቅ ወለጋ እገታ፣ ግድያ እና የጥቃቶች መደጋገም

 እንደ ቤተሰቦቻቸው አስተያየት ወጣቶቹ የተገደሉት አጋቾች 500 ሺህ ብር ከቤተሰቦች ከተቀበሉ በኋላ ነው። ከታገቱት አራቱ ወጣቶች አንዱ በሦስት ጥይት ተደብድቦ ሕይወቱ ግን ባለማለፉ አሁን በነቀምቴ ሆስፒታል ህክምና ላይ ይገኛል። ከአጋቾች ያመለጠው አንደኛው ታጋች ደግሞ ቁስለኛው እንዲነሳና የሞቱትም እንዲቀበሩ ምክንያት መሆኑ ነው የተነገረው።
የእገታ ድርጊቱ አፈጻጸም
ነዋሪነታቸውን ጊዳ አያና ያደረጉና አሁን ግን ሌላ ቦታ እንዳሉ የነገሩን የአንደኛው ሟች ወንድም ስለሺ ጋረደው የተባሉ ተጎጂ ለዶይቼ ቬለ እንደገለጹት፤ ሁለት ወንድሞቻቸውን ጨምሮ አራት ወጣቶች በታጣቂዎቹ የተወሰዱት ቅዳሜ ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ነበር። 
«ከተጠለፉት አራት ወጣቶች ሁለቱ ወንድሞቼ ኢዩኤል ጋረደው እና ቶሎሳ ጋረደው ይባላሉ። ሦስተኛው የእህቴ ልጅ ሶሮማ ረጋሳ ነው የሚባለው። ሌላው አራተኛውም ኤሊያስ ዳባ የሚባል የአካባቢያች ልጅ ነው። እነዚህ አራቱ ልጆች ኅዳር 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ወደ አንገር ጉቴ ከተማ ለገበያ ሄደው በባጃጅ እየተመለሱ ሳለ ፋኖ የተባሉ የታጠቁ ጽንፈኞች አንገር ጉቴ ከተማ 01 ቀበሌ ላይ ጠልፎያቸው እንፈልጋችኋለን ብለው አስገድደው ወሰዱዋቸው። ቀኑ ቅዳሜ ነው ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ፤ በዕለቱ በተያዙበት ቦታ ለሦስት ሰዓታት ግድም አቆዩዋቸውና ከዚያ ከምሥራቅ ወለጋ ዞን ወደ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አቤዶንጎሮ ወረዳ ዳለቾ ወደሚባል ስፍራ ወሰዱዋቸው። ከዚያም ልጆቹ ከተያዙበት ኅዳር 7 እስከ ኅዳር 12 ልጆቻችንን ለመልቀቅ ገንዘብ አስገቡ እያሉ ደጋግመው ሲጠይቁን ነበረ። አንድ ሚሊየን ጠይቀውን እንደምንም እርዳታ ጠይቀን አምስት መቶ ሺህ አስገባንላቸው። ሐሙስ ኅዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ማታ 1፡30 አካባቢ ኢዩኤል ጋረደውና ኤሊያስ ዳባ የተባሉትን ገደሉዋቸው። ኢዩኤል ወንድሜ ነው። ሶሮማ የተባለውን የእህቴን ልጅ ሦስት ቦታ በጥይት ደብድበውት ሞቷል ብለው ጥለውት ቢሄዱም ጥሻ ውስጥ ወድቆ ከከባዱ ጉዳት ሊተርፍ ችሏል። ቶሎሳ ጋረደው የሚባለው ሌላኛው ታናሽ ወንድሜ ግን ወደ ገደል ገብቶ አምልጧቸው የቆሰለውን ወደ ህክምና እንድንወስድ የሞቱትንም እንድንቀብር ምክንያት ሆኗል» ነው ያሉት። 
ያመለጠውስ ወጣት እንዴት ሊተርፍ ቻለ? 
ወንድማቸው ስለሺ እንደሚለው፤ ደግሞም እንደሚያምነው «ፈጣሪ ጣልቃ ገብቶ ከዚህ በላይ እንዳንሰቃይ ይሆናል» ይላል። «ፈጣሪ ረድቶት በዚያ አምልጦ ገደል ውስጥ አድሮ በማግስቱ ወደ አንገር ጉቴ ከተማ መጥቶ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎችን ይዞ ወደ ስፍራው በመሄድ ቁስለኛችንን አሁን በነቀምቴ ሆስፒታል እያሳከምን ነው። አስከሬንም አንስተን ባለፈው እሑድ ቀብረናል» ነው ያለው።
የከፋው የአካባቢው አለመረጋጋት 
ሌላ የጊዳ አያና ወረዳ አንገር ጉቴ ከተማ ነዋሪ እንደገለጹት በአካባቢው በተለያዩ አቅጣጫዎች የተለያዩ ስያሜ ባላቸው ታጣቂዎች ጥቃቶች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ተቃጥቷል። «ኅብረተሰቡ ላይ ጥቃቱ የተቃጣው በሦስት አቅጣጫ ነው። አንደኛው ሐሙስ ዕለት ፋኖ የተባሉ ታጣቂዎች ወጣቶች ላይ የወሰዱት ጥቃትና ግድያ ነው። ሁለተኛው ጥቃት የተፈጸመው ከግዳ አያና ከተማ ወደ ጎቡ የሚሄድ የሕዝብ አሽከርካሪን በማስቆም የኦሮሞ  ነጻነት ሠራዊት የሚባሉ ታጣቂዎች ሕዝቡ አውርደው እነሱ ላይ ጉዳት ባያደርሱም ተሽከርካሪውን አቃጥለውታል» ብለዋል። 
አስተያየት ሰጪው አክሎም እሑድ ጠዋት ከጊዳ አያና ሰው ጭኖ ወደ ነቀምቴ በማምራት ላይ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና ላይ በታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶ አንድ ሰው ብቻ ቢቆስልም ሾፉሩ ባለመጎዳቱ ሊያመልጡ ችለዋል ነው ያሉት። የአካባቢው ጸጥታ መናጋትና ጥቃቶች ከምሥራቅ ወለጋ እና የአካባቢው ወረዳዎች ከባለሥልጣናት አስተያየት ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልሰመረም። ዶቼ ቬለ ክሱ ከሚቀርብባቸው ታጣቂ ቡድኖችም ለጊዜው ለዚህ ዘገባ ምላሽ የሚሆን አስተያየት አላገኘም። 

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ