ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የሰብአዊ ልማት ማሽቆልቆል | ኢትዮጵያ | DW | 19.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ከሰሃራ በታች ባሉ ሃገራት የሰብአዊ ልማት ማሽቆልቆል

በአፍሪቃ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙ የአፍሪካ አገሮች ዘንድ ሰብዓዊ ልማት ከመሻሻል ይልቅ እያሽቆለቆለ ነዉ ሲል የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት ገለፀ። ድርጅቱ በ189 አገሮች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ከመረመረ በኋላ ሰሞኑን ባወጣዉ ዘገባ፤ ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የሰብአዊ ልማት አላቸዉ ከተባሉ አገሮች ተርታ 174ኛ ደረጃ ተቀምጣለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:45

ኢትዮጵያ በ174ኛ ደረጃ ትገኛለች።

የተባበሩት መንግስታት የልማት ድርጅት በምህፃሩ «ዩኤንዲፒ» ሰሞኑን ይፋ ባደረገዉ የ2016  የሰዉ ሃብት ልማት  ዘገባ እንዳመለከተዉ በአፍሪካ በተለይም ከሰሃራ በታች በሚገኙት አገሮች ዘንድ ሰብዓዊ ልማት በመሻሻል ፈንታ ይበልጡን ወደ ታች ወርዷል።።  ድርጅቱ  በስዊድን ርዕሰ ከተማ ስቶክሆልም ይፋ ያደረገዉ ዘገባ የ189 አገሮችን የሰብአዊ ልማት ደረጃ ዝርዝር  ያካተተ ነዉ። ድርጅቱ 10 ሀገሮችን ከፍተኛ የሰብአዊ ልማት እንዳላቸው ሲገልጽ፣ 41 አገሮችን ደግሞ በዝቅተኛ ደረጃ  አስቀምጧል። ከነዚህም ዉስጥ አንዷ ኢትዮጵያ ስትሆን በ174ኛ ደረጃ ትገናለች። 

የጤናና ትምህርት ተደራሽነት፤አማካኝ የሰዉ ልጅ እድሜ፤ለህይወት የሚያስፈልጉ ነገሮች አቅርቦትና ገቢ ፤የጻታ እኩልነትና ሌሎችም  በመስፈርትነት ተቀምጠዋል። ከሰሃራ በታች የሚገኙ ሀገራት በእነዚህ መስፈርቶች ሲመዘኑ ባለፉት ሁለት አስርተ አመታት 60 በመቶ  የሚሆነዉ ህዝብ በዝቅተኛ ደረጃ ይገኛል ተብሏል።  ከአምስት አመት በታች ያሉ አንድ ሶስተኛ ህፃናት በምግብ እጥረት፣  ከ35 በመቶ የሚሆኑ  ሰወች  በማይምነት ፤70 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በቀን ከአራት ዶላር በታች በሆነ ክፍያ የሚሰሩ መሆናቸዉ ተዘርዝሯል። 


 ዩኤስ አሜሪካ በሚገኘዉ በዊስኮንሰን ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዳንኤል ተፈራየአንድ  ከመስፈርቶቹ ሁሉ የነፍስ ወከፍ ገቢ መጨመር ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዉ ፤የአንድ ሀገር የነብስ ወከፍ ገቢ ካላደገ በትምህርት በጤናና በሌሎችም ለህይወት አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች መሻሻልና እድገት ሊመጣ እንደማይችል አብራርተዋል። 
«የሰዉ ሀይል ልማት ለሁሉም» በሚል ርእስ አፍሪካን በተለይም ከሰሃራ በታች ያሉ አፍሪካ ሀገራትን በተመለከተዉ የድርጅቱ ዘገባ   የሀገራቱ  ወጥነት የሌለዉ የሀብት ክፍፍል ፤የፃታ እኩልነት አለመኖር ፣የርስበርስ ግጭትና በሽታ የሰባዊ ልማት ለማሽቆልቆሉ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። በተለይ በሴቶች፣በልጃገረዶች፣በስደተኞች ና በገጠር ነዋሪወች ሰፊ የሀብት ክፍፍል ልዩነት መኖሩ ተመልክቷል።ዶክተር ዳንኤል ግን ሌላም ምክንያት አለ ይላሉ ።

«ዋናዉ ችግር የዉስጥ ችግር ነዉ ።መሪወች አስተያየታቸዉ የላቀ ከሆነ፤ሀገሮች ይበለፅጋሉ ።ኢኮኖሚ ወደፊት ሊራመድ የሚችለዉ ሰፋ ብሎ ህዝቡ ሲሳተፍበት ነዉ።ህዝቡ በኢትዮጵያም ይሁን በሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ተሳታፊነት የለዉም ።ዴሞክራሲያዊ ስርዓቶች የሉም በአፍሪካ ዉስጥ።የተወሰኑ ሰወች ብቻ ነዉ የሚሳተፉበት። ብዙ ህዝብ ቢሳተፍበት ግን ብልፅግናዉም የዚያኑ ያህል ይስፋፋል።»

የሰዉ ልጅ አማካኝ እድሜ በስድስት ዓመት መጨመርና የኤለክትሪክና የባንክ አጠቃቀም በመጠኑም ቢሆን መሻሻል ለሀገራቱ በመልካም ኣጋጣሚነት ተነስተዋል። ከጎርገሮሳዊዉ የዘመን ቀመር ከ1990 እስከ 2015 ዓም  ባሉት ጊዜያት መሻሻሎች ቢታዩም አሁንም ድረስ በአለም ከሦስት ሰወች አንዱ በዝቅተኛ የሰብዓዊ ልማት ላይ ይገኛል ሲል ድርጅቱ  ጨምሮ አመልክቷል።

ፀሐይ ጫኔ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic