ከሞያሌ የተሰደዱ ነዋሪዎች እየተመለሱ ነዉ | ኢትዮጵያ | DW | 10.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ከሞያሌ የተሰደዱ ነዋሪዎች እየተመለሱ ነዉ

ኢትዮጵያ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሰየመች በኋላ ከኢትዮጵያ ሞያሌ ወደ ኬንያ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥራቸዉ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱን የኬንያ ቀይ መስቀል ለዶይቼ ቬሌ ገለፀ። በኬንያ መጠለያ ጣብያ የሚገኙት ተሰዳጆች አብዛኞቹ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ አሁንም ስጋት ቢኖራቸዉም የተወሰኑት እየተመለሱ መሆኑን ድርጅቱ አስታውቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 02:57

«ጠ/ሚ መሾሙን ተከትሎ የስደተኞች ቁጥር በጣም ቀንሰዋል» የኬንያ ቀይ መስቀል

በኦሮሚያ ክልል በቦራና ዞን በሞያል ከተማ የኢትዮጵያ የመከላክያ ሰራዊት በንፁሃን ዜጎች ላይ የግድያ ርምጃ መዉሰዱን ተከትሎ ወደ 50ሺህ የሚጠጉ ቀየያቸዉን ጥለዉ መፈናቀላቸዉን መዘገባችን ይታወሳል።ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ ተሰደዉ በካምፕ ዉስጥ የሚገኙት ወደ 10, 500 እንደሚጠጉም የኬንያ ቀይ-መስቀል ማኅበር መረጃ ያመለክታል። 
በመጋቢት ወር 2010 ዓ,ም የመጀመርያ አካባቢ የስደተኞቹ ቁጥር እንደሚጨምር የኬንያ ቀይ-መስቀል ማኅበር የሕዝብ ግኑኝነትና የኮሙኒኬሽን አስተዳዳር ኖኤላ ናሙላንዳ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዉ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ቁጥራቸዉ ጭማሪ እንዳላሳየና የሰብዓዊ ሁኔታዉ መቆጣጠር እንደተቻለ የማኅበሩ የአከባቢዉ የቀይ መስቀል ዋና ስራ አስከያጅ ታላሶ ቹቻ ዛሬ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

ታላሶ ቹቻ: «የሰብዓዊ ሁኔታዉ አስቸኳይ ከነበረበት ደረጃ አሁን ዝቅ ብለዋል። ምክንያቱም የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነርን ጨምሮ ሌሎች በስደተኞች ዙርያ የሚሰሩ ድርጅቶች በመሳተፋቸዉ ነዉ። አሁን ሁለት የስደተኞች መጠለያ ነዉ ያለዉ። አንዱ በኬንያ ሞያሌ የሚገኘዉ የሶማሬ ካምፕ ሲሆን በዚህ መጠለያም 777 ግለሰቦች ተጠልለዉ ይገኛሉ። ሁለተኛዉ በሶሎሎ ዉስጥ የሚገኘዉ የዳምባላ ፋቻና መጠልያ ሲሆን በዚህ መጠለያም 1,819 ግለሰቦች ይገኛሉ። እነዚህ ግለሰቦች በመጠለያዉ የተመዘገቡ ስሆኑ ቀሪዎቹ ወደ 5000 የሚሆኑት ደግሞ ምዝገባን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።»

ባላፈዉ ሳምንት ሰኞ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የክተር አብይ አህመድ መሾምን ተከትሎ ብዙ ሰዎች ወደ አገራቸዉ እንደተመለሱም ዋና ስራ አስካያጇ ታላሶ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። ታላሶ ቹቻ: «ጠቅላይ ሚንስትሩ የመሾማቸዉ መግለጫን ተከትሎ ወደ መጠለያ የሚመጡት ስደተኞች ቁጥር በጣም ቀንሰዋል። ከባለፈዉ ሳምንት ጀምሮ 11 አባወራዎችን ብቻ ነዉ የተቀበልነዉ። ቁጥራቸዉ ከቀን ወደ ቀን እየቀነሰ ይገኛል። በአከባብያቸዉ ሁኔታዉ ቀስ በቀስ ወደ ነበረበት እየተመለሰ ነዉ።»

ወደ ኬንያ ገቡ ከተባሉት 10, 500 ተፈናቃዮች ዉስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት ሴቶችና ሕጻናት መሆናቸዉን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ባወጣዉ ዘገባ አስታውቋል። ወደ 1500ዎቹ  ከአምስት ዓመት እድሜ በታች መሆናቸው እና 600 ነፍሰ ጡር እናቶች እንደሆኑ ተገልጿል። የአካል ጉዳተኞች እና አረጋውያን ከተሰደዱት መካከል ይገኙበታል።

መርጋ ዮናስ

ሂሩት መለሰ  
 

Audios and videos on the topic