1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከምርኮ ከተለቀቁ በኋላ "ከህወሓት ተባብራችኋል" በሚል የተከሰሱ ወታደሮች እጣፈንታ ምንድነው?

Eshete Bekele
ዓርብ፣ ግንቦት 18 2015

በትግራይ ተማርከው ከነበሩ ወታደሮች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት ያለ ደመወዝ በአስቸጋሪ ሁኔታ በጦር ሰፈር ውስጥ እንደሚገኙ ተናገሩ። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ባለማዕረግ ወታደሮች በመከላከያ ሠራዊት "ከህወሓት ተባብራችኋል" የሚል ክስ ከተቀሩት ምርኮኞች መለየታቸውን ይገልጻሉ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳያቸውን እየተከታተለ ይገኛል።

https://p.dw.com/p/4RsHe
 Released Ethiopian National Defence Force ENDF Prisoners of War from Mekele center
ምስል DW

ከምርኮ ከተለቀቁ በኋላ "ከህወሓት ተባብራችኋል" በሚል የተከሰሱ ወታደሮች እጣፈንታ ምንድነው?

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተሳተፉት ወታደር ከሰባት ወራት ገደማ በፊት ከምርኮ እንደሚለቀቁ ሲነገራቸው "ትልቅ ደስታ" ተሰምቷቸው ነበር። ዜናውን የሰሙት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ በምርኮ ተይዘው ሳሉ ነው። "ጥቅምት 12 ቀን 2015 ስብሰባ ተጠራን እና ወደ አገራችሁ ትሔዳላችሁ ተባልን" የሚሉት ወታደር በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ከ1991 ጀምሮ ያገለገሉ እንደሆኑይናገራሉ።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ወታደር በሰኔ 2013 በትግራይ ክልል ጭላ ተብሎ በሚጠራ ቦታ በተደረገ ውጊያ ከተማረኩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ናቸው። እኚህ ወታደር ከመማረካቸው በፊት የጦርነቱን አስከፊ ገጽታ ኖረውታል። በምርኮ በቆዩባቸው ጊዜያትም ከባድ ፈተና እንዳሳለፉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በጥቅምት 2015 በመቐለ ከተደረገው ስብሰባ በኋላ በሺሕዎች ከሚቆጠሩ ባልደረቦቻቸው ጋር ተለቀቁ። ነገር ግን በወቅቱ ቤተሰቦቻቸው በሕይወት መኖራቸውን አያውቁም።   

"የእኔ ቤተሰብ ሞቷል ተብሎ መርዶ ተነግሯቸው ነበር። ድምጼን ከሰሙ በኋላ በጣም ነው የተደናገጡት፤ ሁሉም የመረበሽ ስሜት ነበራቸው። ከቤተሰብ ሁሉ አላምንም የሚል ስልክ የሚዘጋ ሰው ነበር" ሲሉ ከምርኮ ከተለቀቁ በኋላ የገጠማቸውን አስረድተዋል።

እኚህ ወታደር በጥቅምት 2015 በደቡብ አፍሪቃ ግጭት የማቆም ሥምምነት በኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ከመፈረሙ በፊት ከምርኮ ከተለቀቁ መካከል ናቸው።  "ከመቐለ ስንመጣ ባዶ እግራችንን ነን። ጫማም አልነበረንም፤ ልብስም የለንም። ደመወዝ ክፍያ የለም" ሲሉ እኚሁ ወታደር በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር ችግር ላይ እንደሚገኙ ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት ሰኔ 25 ቀን 21013 ወታደራዊ መለዮ የለበሱ ምርኮኛ ወታደሮች በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ በሰልፍ ሲሔዱ ታይቶ ነበር።
ከሁለት ዓመታት በፊት ሰኔ 25 ቀን 21013 ወታደራዊ መለዮ የለበሱ ምርኮኛ ወታደሮች በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቐለ በሰልፍ ሲሔዱ ታይቶ ነበር። ምስል Stringer/REUTERS

ከትግራይ ከተለቀቁት ወታደሮች መካከል ሦስት መቶ ገደማ የሚሆኑት ተለይተው በመከላከያ ሠራዊት የጦር ካምፕ እንዲቆዩ መደረጉን የተለያየ ማዕረግ ያላቸው ሦስት ወታደሮች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ወታደሮቹ አያያዛቸውን ከእስር ጋር ያመሳስሉታል። እንቅስቃሴያቸው በተወሰነ አካባቢ የተገታ ነው። ወታደሮቹ እንደሚሉት ከመከላከያ ደመወዝ አይከፈላቸውም። እንደ መደበኛ የሠራዊቱ አባላት ጥቅማ ጥቅምም አያገኙም።

"አባዬ የት ነህ ያለኸው? ለምንድነው የማትመጣው?" በቀላሉ የማይመለስ ጥያቄ

በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሌላ ሁለተኛ ወታደር "እስካሁን ድረስ ለሳሙና መግዣ እንኳን መሬታቸውን እየሸጡ፤ ዶሯቸውን እየሸጡ፤ እንቁላል እየተሸጠ፤ ብድር እየተበደሩ" ቤተሰቦቻቸው እንደሚያግዟቸው ይናገራሉ። "ልጆቻችን ትምህርታቸውን መማር በማይችሉበት ሁኔታ ላይ ሜዳ ወድቀው" እንደሚገኙ የሚናገሩት ወታደር "እንደምንም ተደብቀን በስልክ 'አለን' እንላለን። 'አለን በሕይወት ተርፈናል' እንላለን። 'ታዲያ ለምንድነው የማትመጡት? ልጆቻችን አባዬ የት ነህ ያለኸው? ለምንድነው የማትመጣው እያሉን በጣም በስነልቦና ተጎድተን ነው ያለንው" ሲሉ ያሉበት ሁናቴ አስረድተዋል።

ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ ሶስተኛ ወታደር ከመካከላቸው እስከ ኮሎኔል የሚደርስ ማዕረግ ያላቸው እንደሚገኙበት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "እዚህ ጋ ያለው ሠራዊት ከመሠረታዊ ወታደር አንስቶ እስከ ኮሎኔል ማዕረግ ያለው አለ። ሻለቃ አለ፤ መቶ አለቃዎች፤ ሀምሳ አለቃዎች አሉ። ትልቅ አቅም ያላቸው፤ ሠራዊቱን ማገልገል የሚችሉ፤ አሁን ሠራዊቱ ባለው ቁመና ላይ ለአገራቸው መጥቀም የሚችሉ ናቸው" ሲሉ ይናገራሉ።

ክሳቸው ምንድነው?

ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሦስት ባለ ማዕረግ ወታደሮች በመቐለ በምርኮ ተይዘው በነበረበት ወቅት ተመርጠው የማስተባበር ሥራ ሲያከናውኑ እንደነበር ይናገራሉ። በምርኮ "አንድ ዓመት ከስድስት ወር" መቆየታቸውን የገለጹት ሦስተኛው ወታደር "የህወሓት ካድሬዎች ኃላፊዎችን ከተማረከው ጦር መልምለው በግዴታ እንድንሰራ ያደርጉ ነበር። በዚያ አማካኝነት ነበር በሚመጣው በራሪ ጽሁፍ ላይ  ውይይት የሚደረገው" ሲሉ ተናግረዋል። ምግብ፣ አልባሳት እና ውኃ ለተማረኩ ወታደሮች ሲከፋፈል የማስተባበር ኃላፊነት እንደነበረባቸው ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በምርኮ በቆዩባቸው ጊዜያት "ትግራይ ላይ ወንጀል ፈጽማችኋል፤ የጅምላ ግድያ ፈጽማችኋል በሚል በህወሓት አመራሮች ግምገማ ይደረግ" እንደነበር የመጀመሪያው ወታደር አስረድተዋል።

ምርኮኞቹ ከትግራይ ከተለቀቁ በኋላ የተለያየ ማዕረግ ያላቸው ተለይተው "ህወሓትን እና የትግራይ ሠራዊትን" ትረዱ ነበር የሚል ክስ በመከላከያ ሠራዊት እንደቀረበባቸው ሦስቱ ወታደሮች ተናግረዋል። "እናንተ በዚያን ወቅት ለእነሱ ግምገማ ላይ ታግዟቸው ነበር፤ ምስክርም ነበራችሁ" የሚል ክስ እንደቀረበባቸው የመጀመሪያው ወታደር ይናገራሉ። "450 መቐለ ላይ ታስሮ የቀረ ሰው አለ" የሚሉት ወታደር "ያ 450ውም በእናንተ ምክንያት ነው ታስረው የቀሩት" ተብለው በመከላከያ ሠራዊት መወንጀላቸውን ገልጸዋል።

Äthiopien Bürgerkrieg, Reportage aus Abaala, an der Grenze zwischen Tigray und Afar
ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 በተደረገው ጦርነት የተሳተፉት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ የኤርትራ ሠራዊት፣ የትግራይ እና የአማራ ኃይሎች “የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል” እየተባሉ ይወነጀላሉ።ምስል Mariel Müller/John Irungu/DW

ወታደሮቹ የቀረበባቸውን ውንጀላ አስተባብለው መከራከራቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ ለሆኑት ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ስልክ ቢደውልም ምላሽ አላገኘም። ወታደሮቹ ግን የሠራዊቱ የሕግ ክፍል ጉዳዩን ተመልክቶ "የሚያስጠይቃችሁ ነገር የለም" የሚል ምላሽ እንደሰጠ ይናገራሉ።

"ሕግ አገልግሎቶች መጡና ጉዳዩን ጠየቁን። 'ምንም አይነት የሚያስከስሳችሁ ነገር የለም። በወንጀልም የሚያስጠይቃችሁ ነገር የለም' አሉና ጉዳዩን ውድቅ አደረጉት" የሚሉት የመጀመሪያው ወታደር "ከዚያ በኋላ ሰሚ አጣን" ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ ከጥቅምት 2013 እስከ ጥቅምት 2015 በተደረገው ጦርነት የተሳተፉ ኃይሎች “የጦር ወንጀሎች ፈጽመዋል” እየተባሉ ይወነጀላሉ። ጦርነቱ በተካሔደበት ወቅት እና በኋላም ይፋ የሆኑ ሪፖርቶች በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ብርቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ አጋልጠዋል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ሦስቱም ባለ ማዕረግ ወታደሮች የሰላማዊ ሰዎች ግድያም ሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አልፈጸምንም ሲሉ ራሳቸውን ይከላከላሉ።

"ምን አልባት እኔ ከታፈንኩ በኋላ በሁለተኛ እና በሶስተኛ ውጊያ ላይ ያ ነገር ተከስቶ ከሆነ እኔ ተማርኬ ስለነበር አላውቀውም" የሚሉት ሦስተኛ ወታደር "እኔ በነበርኩበት ወቅት ግን ጠንከር ያለ [ቁጥጥር] ነበር። ድንገት ያ ነገር ተሸርሽሮ ሊሆን ይችላል። እኔም እሰማለሁ። ትግራይ በነበርንበት ወቅት የህወሓት ካድሬዎች የፖለቲካ ትምህርት በሚሰጡን ሰዓት 'ትደፍሩ ነበረ፤ ትገድሉ ነበረ ይሉ' ነበር። ነገር ግን እኔ ሳስተባብረው የነበረው ጦር የማውቀው የለም" ሲሉ ተናግረዋል።

ብርቱ ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ባስከተለው ጦርነት አውደ ውጊያዎች ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የፌድራል መንግሥት እና የህወሓት ወታደራዊ እንዲሁም ሲቪል ባለሥልጣናት ባለፈው ሚያዝያ በአዲስ አበባ በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ላይ ተሸልመዋል። በደቡብ አፍሪቃው ግጭት የማቆም ሥምምነት መሠረት መንግሥት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎችን ወደ መደበኛ ሕይወታቸው የሚመልስ መርሐ-ግብር ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል። ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው ባለምዕረግ ወታደሮች የሥምምነቱ ትሩፋት እንዲደርሳቸው ይመኛሉ።

 Ethiopia I  “Enough With War - Let’s Celebrate Peace” in Addis Ababa
ብርቱ ሰብዓዊ እና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ባስከተለው ጦርነት አውደ ውጊያዎች ቀጥተኛ ተሳትፎ የነበራቸው የፌድራል መንግሥት እና የህወሓት ወታደራዊ እንዲሁም ሲቪል ባለሥልጣናት ባለፈው ሚያዝያ በአዲስ አበባ በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ላይ ተሸልመዋል።ምስል Office of Prime Minister of Ethiopia

"እኔ የምችለውን ያህል ታግያለሁ፤ ሦስት አራት ቦታ ቆስያለሁ፤ ይበቃኛል" የሚሉት ሁለተኛ ወታደር "ከመንግሥት በነጻነት የምንቀሳቀስበት ወረቀት ተሰጥቶኝ ቀሪ ሕይወቴን ወደ ቤተሰቦቼ ሔጄ ልጆቼን ማስተማር፣ አሮጊት እናቴን እና ሽማግሌ አባቴን መጦር ነው የምፈልገው" ሲሉ አስረድተዋል። መጻኢ እጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ የማያውቁት የመጀመሪያው ወታደርም "ወደ ወጣሁበት ቤቴ በክብር መመለስ ነው የምፈልገው" ሲሉ ምኞታቸውን ይገልጻሉ።

"እኔ ትምህርቴ፣ እውቀቴ ውትድርና ነው። ከውትድርና ውጪ ሌላ ሕይወት የለኝም" የሚሉት ሦስተኛው ወታደር "ይኸ ሁሉ ጠፍቷል" ሲሉ ስሜታቸውን በተስፋ መቁረጥ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። "ከዚህ ጠፍቼ ብሔድ ነገ ታንቄ መታሰሬ አይቀርም። ምክንያቱም የይለፍ ወረቀት የለኝም።" የሚሉት ወታደር "ነጻ ናችሁ" ተብለው እንዳሻቸው መንቀሳቀስ ይመኛሉ። "ነጻነት ከናፈቀን ሁለት ዓመት አለፈን። እዚያ ጠላት ናችሁ ስንባል፤ ስንደበደብ፣ ስንራብ ነበር። አሁን ወገን ብለን መጣን። ፍትኅ የለም" የሚሉት ከ16 ዓመታት በላይ በመከላከያ ሠራዊት አባልነት ያገለገሉ ወታደር በቀረ ሕይወታቸው ልጆች እና ቤተሰቦቻቸውን መርዳት እንደሚሹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ከምርኮኞቹ መካከል 320 የሚሆኑ ሰዎች ሱላ በተባለ ወታደራዊ የጦር ሰፈር እንደሚገኙ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። ለሁኔታው መፍትሔ ለማበጀት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ግንኙነት እያደረገ እንደሚገኝ የገለጸው ኮሚሽኑ ሁኔታውን በቅርበት መከታተል እንደሚቀጥል በጽሁፍ በሰጠው ምላሽ አስታውቋል። ዶይቼ ቬለ በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እና የመንግሥትን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ