ከሐሙስ እስከ ሰኞ በሲዳማ ምድር ምን ሆነ? | ኢትዮጵያ | DW | 22.07.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ከሐሙስ እስከ ሰኞ በሲዳማ ምድር ምን ሆነ?

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲዓን) ከሐምሌ11 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት አምስት ቀናት በተለያዩ አካባቢዎች ወደ 60 ገደማ ሰዎች መገደላቸውን አስታውቋል። የሲዳማ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ሰዎች መሞታቸውን ቢያረጋግጡም አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር ከመናገር ተቆጥበዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:40

የሲዳማ አርነት ንቅናቄ የሟቾችን ቁጥር 60 ገደማ አድርሶታል

ሰኞ በሐዋሳ ከተማ ትልቁ ሳምንታዊ ገበያ የሚቆምበት ዕለት ነው። እስከ ዕለተ አርብ ተዘግተው የቆዩት እና ሐዋሳን ከአጎራባች ከተሞች የሚያገናኙ መንገዶች በጸጥታ ኃይሎች እና በመከላከያ ሰራዊት ትብብር ተከፍተው አገልግሎት መሥጠት ጀምረዋል። የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት የሕዝብ መጓጓዣ ተሽከርካሪዎች፣ የመንግሥት እና ማኅበራዊ ተቋማት ወደ ሥራቸው ተመልሰዋል። አሮጌ ገበያ ተብሎ በሚጠራው የከተማዋ የመገበያያ ስፍራ በሥራ ላይ የሚገኙ አንድ ነጋዴ እንደሚሉት ለወትሮው ከከተማዋ አጎራባች አካባቢዎች ለንግድ ወደ ሐዋሳ ብቅ ከሚሉ ዜጎች አብዛኞቹ ቀርተዋል።

ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን አስራ አንደኛው የኢትዮጵያ ክልል ሊታወጅ በሲዳማ የለውጥ አራማጆች ቀነ ቀጠሮ የተያዘበት ዕለት ነበር። በዕለቱ የደቡብ ክልልንም፣ የሲዳማ ዞንን መቀመጫነት አዳብላ በያዘችው ሐዋሳ የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ ሌሎች የዞኑ አካባቢዎች ተዛምቷል። ሐዋሳን ጨምሮ በተለያዩ የዞኑ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች እና ግጭቶች የሰው ሕይወት ጠፍቷል።

የሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ዝናው ሳርሚሶ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በሐዋሳ ከተማ ብቻ አራት ሰዎች ሲሞቱ 21 ሰዎች ቆስለዋል። ከቆሰሉት ሰዎች መካከል አስራ ሁለቱ አሁን በሐዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ያስረዱት አቶ ዝናው አምስቱ ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል። ሕይወታቸው ያለፈ ሶስት ወንዶች እና አንዲት ሴት «በጥይት እና ጥይት በሚመስል ነገር» መመታታቸውን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል።

አቶ ዝናው እንዳሉት ሐዋሳን ከአጎራባች ወረዳዎች የሚያገናኙ መንገዶች ተዘግተው በመቆየታቸው ሳቢያ ሆስፒታላቸው ለተጨማሪ ሕክምና የተላኩ ቁስለኞችን ሳይቀበል ቆይቷል። አቶ ዝናው «አሁን መንገዶቹ ስለተከፈቱ ከበድ ያሉ በተለይም የአጥንት ሕክምና እና ሌሎች የተሻሉ እኛጋ ስለሆኑ ከዛሬ በኋላ ይመጣሉ የሚል እምነት አለን» ብለዋል። የሲዳማ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ደምሴ ባለፈው ሐሙስ የተቀሰቀሰው ኹከት አለታ ወንዶ፣ ይርጋለም፣ ሁላ እና አርበጎኔ በተባሉ አካባቢዎች መበርታቱን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ «በዋናነት አለታ እና ሁላ ዝርፊያ ነገርም አለ። በሰው ሕይወት እና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ጉዳቱ ከዚያ በላይ እንዳይሆን የጸጥታ ኃይሉ ጥረት አድርጓል» ብለውዋል።

የደቡብ ክልል መንግሥትም ሆነ የሲዳማ ዞን ባለሥልጣናት ካለፈው ሐሙስ ሐምሌ 11 እስከ ዛሬ ባሉት ቀናት የሞቱ እና የቆሰሉ ሰዎችን አጠቃላይ ቁጥር ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል። የማልጋ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሹባሌ ቡታ ባለፈው ቅዳሜ በጸጥታ ኃይሎች እና የሲዳማ ክልል እንዲታወጅ በሚፈልጉ ተቃዋሚዎች መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት ዎተራ ሬሳ በተባለ ቦታ በትንሹ 13 ሰዎች መገደላቸውን ለሬውተርስ ዜና ወኪል አረጋግጠው ነበር። ይህ የአስተዳዳሪው ማረጋገጫ የሐዋሳውን ጨምሮ የሟቾቹን ቁጥር ወደ 17 ከፍ ያደርገዋል።

በሲዳማ በተፈጠረው አለመረጋጋት በየቀኑ መረጃዎችን ሲያሰባስብ የቆየው ተቃዋሚው የሲዳማ አርነት ንቅናቄ (ሲአን) ፓርቲ በማልጋ ብቻ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 18 ደርሷል ባይ ነው። የሲአን ዋና ጸሀፊ አቶ ለገሰ ላንቃሞ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ይርጋለም፣ አለታ ወንዶ እና ለኩን ጨምሮ በተለያዩ የሲዳማ ዞን አካባቢዎች ወደ ስድሳ ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል። 

የሞቱ ሰዎች የቀብር ሥነ-ሥርዓት ለመካፈል ወደ ማልጋ የሔዱት አቶ ለገሰ «ይርጋለም አምስት፣ አለታ ወንዶ አንድ፣ ለኩ አምስት» ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል። ዋና ጸሐፊው የሞቱ ሰዎች ቁጥር «በአጠቃላይ ከአገረ ሰላሙ ጋር ወደ 60 እየተጠጋ ነው» ብለዋል።

ከኦሮሚያ ክልል የምትዋሰነው የሁላ ወረዳ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች መሞታቸው ከተሰማባቸው የሲዳማ ዞን ቦታዎች አንዷ ናት። በወረዳዋ የሚኖሩ ማንነታቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዐይን እማኝ እንደሚሉት ባለፈው አርብ 14 ሰዎች ከጸጥታ አስከባሪዎች በተተኮሰ ጥይት ሲገደሉ ተመልክተዋል።

የሁላ ወረዳው ነዋሪ እንደሚሉት የጸጥታ አስከባሪዎች አስቀድመው በአካባቢው የተሰማሩት ባለፈው ሐሙስ ምሽት ነበር። በበነጋታው የአካባቢው ነዋሪዎች በከተማዋ ከሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ አቅራቢያ ጥያቄዎቻቸውን ለማቅረብ ወደ ጸጥታ አስከባሪዎች ሲቀርቡ ተኩስ መከፈቱን የዐይን እማኙ አስረድተዋል።

የተቃዋሚው የሲአን ፓርቲ ዋና ጸሀፊ አቶ ለገሰ በሁላ ወረዳ እና በሌሎች አካባቢዎች ሰዎች "በጸጥታ አስከባሪዎች ተገድለዋል" ሲሉ የዓይን እማኙን ገለጻ ያጠናክራሉ። "በሲዳማ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች ሰው ያልተገደለባቸው ጥቂት ናቸው" የሚሉት አቶ ለገሰ "ሕፃናት ጭምር በክልሉ ልዩ ኃይል እና በመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገድለዋል" ብለዋል።

የሲዳማ ዞን ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮማንደር ደሳለኝ ሰዎች መሞታቸውን ቢያረጋግጡም አጠቃላይ የሟቾቹን ቁጥር ከመናገር ተቆጥበዋል። የፖሊስ አዛዡ ከሐምሌ 11 ጀምሮ የሲዳማ ዞንን ባመሰው ተቃውሞ እና ኹከት የተገደሉ እና የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር እንዲሁም የወደመውን ንብረት ግምት "ወደ ፊት ይፋ ይደረጋል" ብለዋል።

በሲዳማ ዞን ውስጥ ካሉ አካባቢዎች ከፍተኛ የንብረት ውድመት የደረሰባት የአለታ ወንዶ ከተማ መሆኗን ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በምትገኘው አለታ ወንዶ በዕለተ ሐሙስ የተቀሰቀሰው ውጥረት ዛሬ ረገብ ቢልም የአጎራባች አካባቢዎች ትኩሳት አሁንም እንዳልተለያት አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል። በከተማዋ በተቀሰቀሰው ግጭት እና ኹከት ከፍተኛ ዋጋ ያለው ንብረት በቃጠሎ መውደሙን እኚሁ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የአይን እማኝ ያስረዳሉ። እንደ ከተማዋ ነዋሪ ከሆነ በከተማይቱ የንብረት ውድመቱ እና ቃጠሎው ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት እስከ ምሽቱ አምስት ሰዓት ገደማ ድረስ የዘለቀ ነበር። ይህን ድርጊት ማስቆም ይችሉ የነበሩት የጸጥታ አስከባሪዎች ዘግይተው መድረሳቸውን ነዋሪው ያስረዳሉ።

ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በሲዳማ ዞን በተቀሰቀሰው አለመረጋጋት ጉዳት የገጠማቸውን አካባቢዎች ትላንት እሁድ ተዘዋውረው የተመለከቱት የደቡብ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በተለይ በአለታ ወንዶ የተመለከቱትን «ልብ የሚሰብር» ሲሉ ገልጸውታል። «ድርጊቱ ሊወገዝ ይገባል» ያሉት ርዕሰ-መስተዳድሩ «ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎችን በአጭር ጊዜ እናቋቁማለን» ሲሉ ለደቡብ ክልል ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የአለታ ወንዶው የአይን እማኝ ንብረታቸው በዕለተ-ሐሙስ ከተቃጠለባቸው ሌሎች ጎረቤቶቻቸው ጋር በአንድ ቅጥር ግቢ እንደሚኖሩ ይናገራሉ። የሲዳማ ክልል ሐምሌ 11 በይፋ እንዳይታወጅ መከልከሉን የተቃወሙ ወጣቶች ቁጣቸውን ለመግለጽ የፈጸሙትን ድርጊት የሲዳማ ብሔር አባላት ጭምር መቃወማቸውን ታዝበዋል። "ለጥያቄው ተገቢ ምላሽ በወቅቱ አልተሰጠም" ሲሉ የሚተቹት የአለታ ወንዶ ነዋሪ መጪው ጊዜ አብዝቶ ያሳስባቸዋል።

የሐዋሳው ነጋዴ እንደ አለታ ወንዶው ነዋሪ ሁሉ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት በሕዝቡ ዘንድ መንገሱን ይገልጻሉ። ነጋዴው መንግሥት ጥያቄውን ለመመለስ ዘገምተኛ ከመሆኑ ባሻገር የሕግ የበላይነትን ለማስከበር መዘግየቱን ይተቻሉ።

ሐዋሳ ከተማ ከተፈጠረው ኹከት በኋላ ከድርጊቱ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው የተባሉ 150 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ስኳሬ ሾዳ ለክልሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ ባለፈው ቅዳሜ ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ በተለይ አዲሱ መናኸሪያ፣ አቶቴ፣ አላሙራ እና ሎቄ ከተባሉ የከተማዋ አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ናቸው። ሌሎች በርካታ ተጠርጣሪዎች በከተማዋ በሚገኘው ታቦር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ታስረው እንደሚገኙም ተሰምቷል። ተጠርጣሪዎቹ የታሰሩበትን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር የተመለከቱ የዓይን እማኞች ቁጥራቸው እስከ 500 ሊደርስ እንደሚችል ግምታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ተስፋለም ወልደየስ

 

Audios and videos on the topic