ከሁለቱ አዛዉንቶች ማን ይሆን? | ዓለም | DW | 02.11.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

ከሁለቱ አዛዉንቶች ማን ይሆን?

#የአሜሪካ_ምርጫ_2020 ትራምፕ ከዓለም እያላተሙ ከዓለም ሁሉ ሊያስቀድሙ የፈከሩ፣ቃል የገቡ፣ሕዝብ ያሳደሙላት አሜሪካ በኮሮና ተሕዋሲ በተያዘና በሞተ ሰዉ ቁጥር በርግጥ ከዓለም ቀድማለች።ከዓለም የቀደመችበት በሽታና በሽታዉን ለመከላከል የሚወሰደዉ ርምጃም ወይም መርሕም ብዙዎች እንደሚሉት ለአሜሪካኖች ምርጫ ቀዳሚና ወሳኝ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:53

#የአሜሪካ_ምርጫ_2020 ሁለቱ አዛዉንቶች ማን ይዘልቅ ይሆን?


ያንድ ዘመን ዉልዶች ናቸዉ፤ በ3 ዓመት የሚበላለጡ አዛዉንቶች።ዉልደት፣የልጅነት ኑሮ ዕድገታቸዉ ግን ለነጩ አሜሪካዊ ልክ እንደ ራሷ እንደ አሜሪካ የደሐ-ሐብታም ማነፃፀሪያ አብነቶች፣ ደግሞ ተቃራኒ ግን እኩል ፖለቲከኛ ናቸዉ። ዶናልድ ጆን ትራምፕ እና ጆሴፍ ሮቢኔት ባይደን ጁኒየር። ጆ ባይደን ሲያጥር። እኩል ፖለቲከኛ የመሆናቸዉን ያክል እንደ አሜሪካ ልዩነት፣ እንደ ዉልደት፣ እድገት ኑሯቸዉ ርቀት፣ ስብዕና ባሕሪ፣ የፖለቲካ ፓርቲ፣ መርሕ፣አላማ፣ርዕያቸዉ ሁሉ ተፃራሪ ነው። ሁለቱም በነገዉ ምርጫ «አሸናፋለሁ» ባይ ናቸዉ። ትራምፕ ባለፈዉ ሳምንት።
«ፔንስሌቬንያን እናሸንፋለን። አለቀ፤ አለቀ።» ፔንስሌቬንያ የባይደን የትዉልድ ግዛት ናት። እና ባይደን በዚያዉ ሳምንት ግን ከሌላ ግዛት «ዶናልድ ትራምፕ ሻንጣዉን ሸክፎ ወደ መጣበት መሔጃዉ ጊዜ አሁን ነዉ» አሉ። ማን ያሸንፍ ይሆን? 
                                
እሱ፤ነሐሴ 1946 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኒዮርክ ዉስጥ ተወለደ።ከቤተሰቡ አምስት ልጆች አራተኛዉ ነዉ። ዶናልድ ተባለም። አዱኛ የሰገደችለት የቤት ገንቢና ሻጭ (ሪል ስቴት) ኩባንያ ባለቤት የሚሊየነር ልጅ ነዉ። The Trump Nation የተባለዉ መፅሐፍ ደራሲ ቲም ኦ ብሬይን  «የዶናልድን ዉልደት እድገት አይተሕ ማንነቱን ትረዳለሕ» ይላሉ።
«አስተዳደጉ እንደመካከለኛ መደብ ልጅ አይደለም። ቤተሰቡ ሾፌር ነበረዉ። ትምሕርት ቤት የሚሔደዉ በሊሞዚን ነዉ። ተቀጥሮ ወይም መደበኛ

ሥራ ሠርቶ አያዉቅም።»
ዶናልድ ሲወለድ ጆሴፍ የ3 ዓመት ከስምንት ወር ገደማ ልጅ ነበር። ከሁለት ታናሾቹ ቀድሞ ሕዳር 1942፣ ሴክራንተን ፔንስልቬኒያ ተወለደ። የትዉልድ ከተማዉ የአሜሪካ መካከለኛና አነስተኛ መደብ ማሕበረሰብ መኖሪያ አብነት ናት።
ጆሴፍ ከመወለዱ በፊት ቤተ-ሰቡ ጥሩ የሚኖር ደሕና ገቢ የነበረዉ ነበር። ሊወለድ አካባቢ ግን አባት ከሰሩ። ኑሮም መረረ። ጠንካራዉ አባት ለልጆቻቸዉ የሚመክሩ፣የሚያስተምሩ የሚያሳዩትም ወድቆ መነሳትን፣ አጥቶ ማግኘትን፣ ከስሮ መንሰርን ነበር። «አባቴ የወደቀዉ  መጥፎ ጊዜ ነበር። ሁል ጊዜ የሚነግረኝ ግን ስትወድቅ ተነስ እያለ ነበር።» አባት ወድቀዉ አልቀሩም። ተፍጨርጭረዉ ተነሱ። እንደ ድሮዉም ባይሆን የተሳካላቸዉ የአሮጌ መኪና ነጋዴ ሆኑ።
ጆሴፍ ድሕነትን ለማምለጥ፣

ዶናልድ ይበልጥ ለመንደላቀቅ በየፊናቸዉ ይዉተረተሩ ገቡ። ጆሴፍ በመጀመሪያና በሁለተኛ ደረጃ ተማሪነቱ በቀለሙ ደከም፣ በስፖርቱ በተለይም በአሜሪካኖቹ ፉትቦል ጠንከር ያለ ነበር። ከሁሉም በላይ የየክፍሉ «አለቃ» ሆኖ መሪነትን ገና በልጅነቱ ይለማመድ ያዘ።
ሲናገር አፉን ያዝ ወይም ቀርፈፍ ወይም ደንቀፍቀፍ ያደርገዉ ነበር። «መደነቃቀፉን ለማስወገድ ግጥምን እየሸመደደ፣ በቃሉ ግን ጮክ ብሎ መድገም እንደ ፍቱን ሕክምና ተጠቀመበት።ረዳዉ። የዶናልድ ችግር ግን ሌላ ነበር።
«ዶናልድ ችግር ፈጣሪ ብቻ አልነበረም። እብሪተኛም ነበር። እንደነገረኝ አስተማሪዎች አድርግ የሚሉትን ማድረግ ካልፈለገ «እቀጣቸዉ ነበር» ይላል።» አሉ ኦ ብሬይን። ወላጆቹ ዘየዱ። ሥርዓት እንዲማር ብለዉ ኒዮርክ ወታደራዊ አካዳሚ አስገቡት።
ለጆሴፍ ፉት ቦል፣ ለዶናልድ ደግሞ ቤዝ ቦል ነበር።«የቤዝ ቦል ተጫዋች መሆን ነበር የምፈልገዉ።ጎበዝ ተጨዋች ነበርኩ።»
ጆሴፍ በ1965 በታሪክና በፖለቲካ ሳይንስ፣ ዶናልድ  ደግሞ በ1988 በኤኮኖሚክስ  ተመረቁ።ከእንግዲሕ አንቱ ናቸዉ።ባይደን ካገቡ በኋላ፣ በመጀመሪያዉ ዲግሪ ላይ ሌላ የሕግ ዲግሪ አከሉበት። ትራምፕም በንግዱ እንጂ ወደ ትምሕርቱ ተመልሰዉ አልገቡም።ያገቡትም ከባይደን 10 ዓመት ያክል ዘግይተዉ ነዉ። 
ብቻ ሁለቱም ረጅሙን የሕይወት ጎዳና ያዘግሙበት ገቡ።ባይደን ላጭር ጊዜ በጥብቅና ከሰሩ በኋላ በዴሞክራቲክ ፓርቲ በኩል ፖለቲካዉን ተቀየጡ።1969።በዚያዉ ዓመት በደልዌር ክፍለ-ግዛት የኒዉ ካስል ወረዳ ምክር ቤት አባል ሆነዉ ተመረጡ።
ትራምፕ ግን ከአባታቸዉ ኩባንያ ስራ አስኪያጅነት ወደ ራሳቸዉ ኩባንያ መስራችነት፣ ከሚሊዮነርነት ወደ ቢሊየነርነት ይመነደጉ፣

ዶላር እየሰበሰቡ ዶላር ይረጩ ያዙ።ባይደን ዘንድሮ ለትልቂቱ ሐገር ትልቅ ሥልጣን ለመወዳደር የበቁት ከወረዳ ምክር ቤት አባልነት እስከ ሴናተርነት፣ ከሴናተርነት እስከ ምክርትል ፕሬዝደንትነት ፖለቲካዉን ከግማሽ ምዕተ-ዓመታት በላይ ከቀዙፉ-ከዋኙበት በኋላ ነዉ።
ትራምፕ ግን ከጥቂት አመታት በላይ ዋይት ሐዉስ ለመግባት ገንዘብ፣ገንዘብ የሚያገዝፈዉ ስም፣ በቴሌቪዥን መስኮት ደጋግሞ መታየት በቂያቸዉ ነበር።እርግ ነዉ «በ1980ዎቹ ፕሬዝደንት እሆናለሁ ይሉ ነበር » የሚሉ ጓደኞች አሏቸዉ።ይሁንና ፌዝና ቁምነገሩን ለይተዉ የማይናገሩት  ነጋዴ አሉት የተባለዉን ካጀታቸዉ ይሁን ካንገት በዉል የሚያዉቅ የለም።
የሚታወቀዉ ለፖለቲካ ፍላጎት እንዳላቸዉ በይፋ የታየበት የ1999ኙ አጋጣሚ ነበር።ያኔ ትራምፕ ከሪፐብሊካን ፓርቲ ደጋፊነት ሪፎርም ፓርቲ ወደተባለዉ ደጋፊነት ቀየሩ።
ባመቱ ግን «የምትገባን አሜሪካ» ያሉትን መፅሐፍ አሳተሙ።መፅሐፉ ምጣኔ ሐብቱን ከመንግስት ጫና ነፃ (ሊብራል) ማድረግ፣ ፖለቲካዊን ግን ጠጠር ያለ ወግ አጥባቂ መርሕ እንዲከተል ማድረግ የሚል ይዘት ነበረዉ።
በ2012ቱ ተመልሰዉ የሪፐብሊካን ፓርቲን ተቀየጡ።የያኔዉን ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማን አሜሪካ ዉስጥ አልተወለዱም በማለት በሐሰት ስም ማጥፋት የጀመሩትም ያኔ ነበር።ዉንጀላዉ ዉሸት ቢሆንም ስድብ፣ማንጓጠጥ፣ማበሻቀጣቸዉ የብዙ ቀኝ አክራሪ አሜሪካዉያንን ጆር መሳቡ አልቀረም።
በ2016 ከዝነኛዉ የዴሞክራቶች ፕሬዝደንት ከቢል ክሊንተን ባለቤት፣ ከኦባማ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትርና ከመጀመሪያዋ አሜሪካዊት ሴት ዕጩ ፕሬዝደንት ከሒላሪ ክሊንተን ጋር ተወዳደሩ።የመርሐቸዉ ማጠንጠኛ ቅድሚያ ለአሜሪካ ወይም አሜሪካ ትቅደም ነበር።
«ዛሬ እዚሕ የተሰበሰብነዉ በሁሉም ከተማ፣ በሁሉም የዉጪ ርዕሠ ከተሞች፣ በሁሉም የስልጣን ደረጃ ሊሰማ የሚገባ መርሕ ለማወጅ ነዉ።ከዛሬ ጀምሮ ሐገራችንን የሚመራዉ አዲስ ርዕይ ነዉ።ከእንግዲሕ መርሐችን አ

ሜሪካ ትቅደም የሚለዉ ብቻ ነዉ።አሜሪካ ትቅደም።»
አሸነፉም።ቢሊዮነር፣ ቅምጥል፣ ቀኝ አክራሪ፣ ያሻቸዉን የሚናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ለሁለተኛ ዘመነ-ሥልጣን ለመመረጥ ከፖለቲካና ታሪክ አዋቂዉ፣ ከለዘብተኛዉ፣ አንጋፋ ፖለቲከኛ ከቀድሞዉ ምክትል ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ጋር «እየተናነቁ» ነዉ።
ሁለቱ ፖለቲከኞች እና ፓርቲዎቻቸዉ በብዙ ነገር ይለያያሉ።ብዙዎች እንደሚሉት የመራጩን ሕዝብ ፍላጎት በቀጥታ የሚነኩት ግን የጤና መርሕ፣ ምጣኔ ሐብቱ፣ ዘረኝነት እና ፀንስ ማስወረድ ከቀዳሚዎቹ አራቱ ጉዳዮች ናቸዉ።ግን ማን እንደ ኮሮና።አምና ይሕን ጊዜ ምንም የማይታወቀዉ የኮሮና ተሕዋሲ ስርጭትና ስርጭቱን ለመግታት ዕጩዎቹ የሚከተሉትን መርሕ የሚስተካከል በርግጥ የለም።
ትራምፕ ከዓለም እያላተሙ ከዓለም ሁሉ ሊያስቀድሙ የፈከሩ፣ቃል የገቡ፣ሕዝብ ያሳደሙላት አሜሪካ በኮሮና ተሕዋሲ በተያዘና በሞተ ሰዉ ቁጥር በርግጥ ከዓለም ቀድማለች።ከዓለም የቀደመችበት በሽታና በሽታዉን ለመከላከል የሚወሰደዉ ርምጃም ወይም መርሕም ብዙዎች እንደሚሉት ለአሜሪካኖች ምርጫ ቀዳሚና ወሳኝ ነዉ። የኮሎንቢያ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር አሽዊን ቫሳን እንደሚሉት በነገዉ ምርጫ የኮሮና ተሕዋሲን ያክል ትኩረት የሚስብ መርሕ ሊኖር አይችልም።
«በአሜሪካ መራጮች አዕምሮ ዉስጥ የኮሮና ተሕዋሲ ቀዳሚና ማዕከላዊዉን ሥፍራ ይዟል።ምክንያቱም የሕዝብ ጤና ቀዉስ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሐብቱ፣ በሥራ፣ በትምሕርት፣ በትራንስፖርት እና በሁሉም የሕብረተሰባችን ክፍል ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል።ይሕ ተፅዕኖ በድምፁ ጫና ያሳድራል።»
እስከ ዛሬ ከ92 ሚሊዮን የሚበልጥ አሜሪካዊ ድምፁን ሰጥቷል።እስካሁን በተሰባሰበዉ የቅድመ ምርጫ አስተያየት የዶሞክራቶቹ ዕጩ ጆ ባይደን ከፕሬዝደንት ትራምዕ የተሻለ ድጋፍ እንዳላቸዉ ይጠቁማል። ወሳኙ ግን ነገ የሚሰጠዉ ድምፅ ነዉ።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሠ


 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች