ኦጋዴን: የነዳጅ ፍለጋው እና የጸጥታው ሁኔታ | ኢትዮጵያ | DW | 25.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

ኦጋዴን: የነዳጅ ፍለጋው እና የጸጥታው ሁኔታ

በኦጋዴን አካባቢ የሚካሄደውን የነዳጅ ዘይት ቁፋሮ ኣጥብቆ እንደሚቃወም ኣማጺው የኦጋዴን ነጻ ኣውጪ ግንባር በምህጻሩ « ኦ ኤን ኤል ኤፍ » ኣስታወቀ። ኣንድ ኣንጋፋ የግንባሩ መሪ ለ« አይ ፒ ኤስ » የዜና አገልግሎት እንደገለጹት በኦጋዴን የሚገኘው የነዳጅ ዘይት ከለማ የኢትዮጵያን መንግስት ባለጸጋ ያደርገዋል።

የኦጋዴንን ህዝብ ደግሞ በድህነት እና ጭቆና ስር ያቆየናል ብሏል። ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ለጊዜው በሚስጢር ቢያዝም፤ በኣሁኑ ጊዜ፤ በኦጋዴን አካባቢ የማይናቅ የነዳጅ ዘይት መጠን ለመገኘቱ በቂ መረጃዎች ኣሉ።

ኢትዮጵያ ለነዳጅ ዘይት ፍለጋ የኦጋዴን በረኃን ማሰስ ከጀመረች ዓስርተ ዓመታት ተቆጥሯል። ኣለ ተብሎ ተስፋ ባያጭርም የለም ተብሎም ግን ተስፋ ኣላስቆረጠም። እናም ፍለጋው በተለይም ኣሁን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል። ሌላው ችግር የክልሉ ምናልባትም ከሶማሊያው ቀውስ ጋርም በተያያዘ በአካባቢው ኣስተማማኝ ሰላም የመታጣቱ ግዳይ ነው። በአካባቢው የተገኘው የተፈጥሮ ጋዝም ሆነ እየተፈለገ ያለው የነዳጅ ዘይት ይላሉ የኣማጺው የኦጋዴን ነጻ ኣውጪ ግንባር « ኦ ኤን ኤል ኤፍ » መስራች አብዱረህማን መሓዲ ኢንተር ፕረስ ሰርቪስ (« አይ ፒ ኤስ ») ለተሰኘው የዜና አገልግሎት ሲናገሩ ኢትዮጵያን ሀብታም ሊያደርጋት ይችላል። ነገር ግን እኛን በድህነት እና በጭቆና ውስጥ ያቆየናል። ለዚህም ነው በአካባቢው የሚካሄደውን የማዕድን ልማት ኣጥብቀን የምንቃወመው ሲሉም ያስረዳሉ። በ 2007 ዓም ለምሳሌ እአኣ ማለት ነው የ « ኦ ኤን ኤል ኤፍ » ሸማቂዎች ዘጠኝ ቻይናውያንን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመንግስት ወታደሮችን ከፈጁ በኃላ የነዳጅ ቁፋሮ ጣቢያውንም ማጋየታቸው የሚታወስ ሲሆን ከዚያ ወዲህ በኦጋዴን የሚሰማሩ የቻይና የነዳጅ ቁፋሮ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን ወታደሮች የደንብ ልብስ እየለበሱ ለመሳሰል መገደዳቸው ኣይዘነጋም።

ኣማጺው የኦጋዴን ነጻ ኣውጪ ግንባር ኦጋዴኒያ እያለ በሚጠራው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የራስን እድል በራስ የመወሰን መብትን ለማስከበር እንደሚታገል መግለጹ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ የኤርትራ መንግስትን ጨምሮ በሶማሊያ ኃይሎች የውጪ ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ኣሸባሪ ቡድን ነው ሲል እንቅስቃሴውን በወታደራዊ ጡንቻ ሲመክት ቆይቷል። በዚህ ሁሉ መካከል ታዲያ በአካባቢው የልማት ስራዎች ከመሰናከላቸውም በላይ የመብት ተሟጋቾች እንደሚሉት ሰብዓዊ መብቶች ተጥሷል። ሌላው ቀርቶ የኣስቸኩዋይ ጊዜ እርዳታዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ እየተቻለ ኣይደለም ተብሏል።

በኦጋዴን አካባቢ የሚገኘው የማዕድን ኃብት ለኣገሪቱ በተለይም ለራሱ ለኦዴን ክልል ይበልጥ ጠቃሚ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ መንግስት ቃ/ኣቀባይ፤ የማስታወቂያ ሚኒስትር ዲዔታው አቶ ሺመልስ ከማል ለ« አይ ፒ ኤስ » እንዳስረዱት በክልሉ ይፈጸማል የተባለውን የመብት ጥሰት እና ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ ያደረገ ነው የተባለለትን ወታደራዊ ጥቃት ኣስተባብሏል።

በኦጋዴን ይገኛል የተባለውን የነዳጅ ዘይት ኣስመልክቶ ከመንግስት በኩል እስከኣሁን በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም በኬኒያ ናይሮቢ የቀውስ ኣስወጋጅ ግብረ ኃይል ተንታኝ የሆኑት ሚ/ር አብዲ ረሺድ ለዶቸቬሌ እንዳስረዱት ነዳጅ በኦጋዴን አካባቢ ለመገኘቱ በርካታ መረጃዎች ኣሉ።

«እስከሚገባኝ ድረስ ያ የኢትዮጵያ ክልል ጥሩ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ውጤት እንዳለው የሚያመለክቱ በቂ መረጃዎች ኣሉ። ምናልባትም ለገበያ በቂ የሆነ መጠንም ኣለው። ነገር ግን አብዛኞቹ በዚያ የፍለጋ ስራ ለይ የተሰማሩ ኩባኒያዎች፤ ኣየህ፤ ይህንን የንግድ ሚስጢር ይጠብቃሉ።»

Somalia Kämpfe in Mogadishu Hawiye-Clan

የሰብኣዊ መብት ይዞታው ግን ገና ኣለመሻሻሉን የጠቀሱት ተንታኙ የኢትዮጵያ መንግስት ከኦጋዴን ነጻ ኣውጪ ግንባር ጋር የጀመረው ድርድር በራሱ የዚህ ኣመላካች ነው ይላሉ።

«እንደሚታወቀው የአዲስ አበባው መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከ« ኦ ኤን ኤል ኤፍ » ጋር የሰላም ንግግር ጀምሯል። እንደማስበው የኢትሾጵያ መንግስት እና « ኦ ኤን ኤል ኤፍ »ን ኣሁን ወደ እርቅ እንዲያዘነብሉ ከሚያደርጉዋችው ምክኒያቶች ኣንዱ ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ነው። ሰላም ከሰፈነ የኢትዮጵያ መንግስትም ይጠቀማል። የኦጋዴን ህዝብም ተጠቃሚ ይሆናል። ስለዚህ የኣሁኑ የድርድር አዝማሚያ ሰላማዊ ኦጋዴን የሁለቱም ወገኖች ፍላጎት ነው ከሚል ስሌት የመነጨ ነው ብዬ ኣስባለሁ።»

በኢትዮጵያ ከኦሮሚያ ቀጥሎ በቆዳ ስፋቱ 2ኛው ትልቁ አካባቢ የሆነው የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል በረኃማነት ቢያጠቃውም በተፈጥሮ ኃብት ይዞታው ግን የበለጸገ መሆኑ ይታወቃል።

ጃፈር ዓሊ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic