1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኦቲዝምና የነርቭ ስርዓት ትስስር

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2016

በአሁኑ ጊዜ ለኦቲዝም የተጋለጡ ልጆች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን የአሜሪካው የበሽታዎች መቆጣጠሪያን መከታተያ ማዕከል ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ። የዓለም የጤና ድርጅት ከአንድ መቶ ልጆች ውስጥ ቢያንስ በአንዱ ላይ ኦቲዝም ሊያጋጥም እንደሚችል ይገልጻል።

https://p.dw.com/p/4f6Za
ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆችን ለማስተማሪያ የተዘጋጀ መርጃ
ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆችን ለማስተማሪያ የተዘጋጀ መርጃ ፎቶ ከማኅደርምስል Topcliffe Primary School/London Knowledge Lab

ኦቲዝምና የነርቭ ስርዓት ትስስር

 

 

ስለኦቲዝም የነርቭ ህክምና ባለሙያዎች ምን ይላሉ?

በዓለም አቀፍ ደረጃ ኦቲዝም ዘንድሮ በያዝነው ሚያዝያ ወር ሲታሰብ ለ17ኛ ጊዜ መሆኑ ነው። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ስለኦቲዝማ የአእምሮ እድገት ውሱንነት በየጊዜው ሲነገር እንሰማለን። ኦቲዝም የአንጎል እድገት ውስብስብ ችግሮች በቡድን የሚገለጹበት መሆኑን የሚያመለክቱ ማብራሪያዎች አሉ። በዚህ እክል ውስጥ ያሉ ልጆች ገና በለጋ ዕድሜያቸው የሚታወቁ ሲሆን ከአካባቢያቸው ተላምደውና ተዋህደው ለመኖር እንደሚያዳግታቸው ይገለጻል። የራሳቸው ዓለም አላቸው የሚባሉት የኦቲዝም ሰለባዎች በተግባብቦት ሂደት የሚያሳይዋቸው ሦስት ነገሮች እንዳሉ ነው ዶክተር ተሻገር የሚናገሩት። የቋንቋና ተግባቦት መገደብ፤ ትርጉም የሌለው እንቅስቃሴ እና ድምጽ ማውጣት የመሳሰሉ ያልተለመዱ ነገሮችን እንደሚያዘወትሩ አመልክተዋል።

እንዲህ ያሉት ምልክቶች ልጆቹ ላይ መታየት ከጀመረ በኋላ ሁለት እና ሦስት ዓመት ሲሆናቸው እየጨመረ የመሄድ ዕድሉ ከፍተኛ ሆኖ ያላቸው ዕድገትም እየተቆጠበ እንደሚሄድ ነው የነርቭ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያው ያመለከቱት። በዚህ መሀልም ዋነኛው መለያ ልጆቹ በአካባቢያቸው ካለው ሰው ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት የተረበሸ ነው የሚሉት። እንዲህ ላለው እክል መንስኤው ከነርቭ ስርዓት ጋር የተሳሰረ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። ዶክተር ተሻገርም ይህንኑ ነው ያረጋገጡት።ምዕናባዊ ኦቲዝም፤ የዲጅታል ዘመን ልጆች ስጋት

የተባለው የነርቭ መተሳሰር እንዲከሰት ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚባሉ ምክንያቶች አንዱ ከዘረመል ውርስ ጋር የሚገናኝ ሲሆን ከተፈጥሮ አካባቢ ጋር የተገናኘ ሊሆን እንደሚችልም የህክምና ባለሙያዎች ይገምታሉ። ሌላው መንስኤ ደግሞ በእርግዝና ጊዜ የሚያጋጥሙ የጤና ችግሮች፣ የሚወሰዱ መድኃኒቶች ሊሆኑ ይችላሉም ይላሉ። የአመጋገብ ችግር፣ ሲጋራና አልክሆል መጠጥ ማዘውተሩ በጽንስ ወቅት የሕጻኑ የአእምሮ እድገት ላይ የሚያሳርፈው ተጽዕኖ ሊኖር እንደሚችልም ይታሰባል።

ፎቶ ከማኅደር፤ የኦቲዝም መግለጫ አርማ
ኦቲዝም ይናገራልፎቶ ከማኅደር፤ የኦቲዝም መግለጫ አርማ

ኦቲዝም ሲገለጽ

ኦቲዚም በጥቅሉ ይገለጥ እንጂ የተለያየ ደረጃ ይዞ በልጆቹ ላይ እንደሚገለጥ ያመለከቱት የነርቭ ህክምና ባለሙያው፤ አንዳንዶቹ ላይ ቀለል ያለ፤ በአንዳንዶቹ ደግሞ ከፍተኛ የሚባል መገለጫዎች እንዳሉትም ነው ያስረዱት። ኦቲዝም ከአእምሮ የመረዳት አቅም አለመጎልበት ሁኔታ፤ የቋንቋ መገደብ፤ እንዲሁም በአካባቢያቸው ካሉ ሰዎች ጋር የመግባባት ውሱንነት እንደሚሳይ ደግመው የገለጹት ዶክተር ተሻገር፤ ከዚህ አልፎም የማይደረጉ ነገሮችን የማድረግና አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉ ነገሮችን ያለማወቅ አጋጣሚዎች እንደሚኖሩም አንስተዋል። ሌላኛዉ የድብርት ጽንፍለምሳሌ እሳትን መዳፈር፤ አብሯቸው ካለው ሰው ጥበቃ አምልጠው በመኪና መንገድ ላይ ድንገት የመሄድ፤ ነገር ስላለ ለአደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን አውቆ የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት።ጥንቃቄ የሚሻው የአእምሮ ጤንነት

የነርቭ ከፍተኛ ሀኪሙ ለወላጆች ያሳሰቡት ልጆቻቸውን ወደ ሕጻናት ሀኪም በተለይም የስነልቡና እና የነርቭ ሀኪም ዘንድ ወስዶ በጊዜ ማስመርመር ተቀዳሚ ተግባራቸው እንዲያደርጉ ነው። ከነርቭ መታወክ ጋር ተያይዞ የሚጥል በሽታ ሊኖር ስለሚችል ምርመራው ያንን አስቀድሞ ለማወቅ እና ተገቢውን እርዳታ ለማድረግ እንደሚረዳም አጽንኦት ሰጥተዋል። ችግራቸው በጊዜ የታወቀላቸው ልጆች ቋንቋቸውን በተለየ መልኩ እንዲማሩ፤ ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንዲችሉ፣ ከአካባቢያቸው ተላምደው ከሚያሳዩት የመገለል ስሜት ቀስ በቀስ እንዲወጡ ለማድረግ የቅርብ ክትትል እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል። ለሰጡን ማብራሪያ የነርቭ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያውን እናመሰግናለን።

 ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ