ኦባማና የውጭ ጉዳይ የፖለቲካ መርኀቸው | ዓለም | DW | 24.03.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኦባማና የውጭ ጉዳይ የፖለቲካ መርኀቸው

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ዖባማ፤ ዛሬ ኔድርላንድ እንደገቡ በሰጡት መግለጫ ፣ አውሮፓውያንን ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ በክሪሚያ በወሰደችው እርምጃ ሳቢያ ዋጋ የሚያስከፍላትን የማዕቀብ ርምጃ በመተባበር ወስደናል አሉ። ሰፊ የጦር ኃይል አንቀሳቅሶ

ለጦርነት መዘጋጀት ሳይሆን፤ በአብራሪ የለ,ሽ የጦር አኤሮፕላኖችና በማዕቀብ መመካት ሆኗል ፤ ዖባማ ለዩናይትድ ስቴትስ የቀየሱት አዲሱ የውጭ አመራር ዘይቤ፣ በወታደራዊ ስልት ቀላሉን መንገድ ነው የመረጡት። የዩክሬይኑ ውዝግብ ይህን ስልት የሚፈትን ይሆናል። የፑቲን የጦር እንቅሥቃሴ ሁሉንም ጥላ ጋርዶበታል። በሃርቫርድ ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ባለሙያ ኒኮላስ በርንስ እንደሚሉት፣ ፑቲን ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ አውሮፓን እጅግ ያሠጉ ሰው ናቸው። ያሁኑ ውዝግብ ፣ በዖባማ የውጭ አመራር ዘይቤ ላይ ታላቁን ፈተና ደቅኗልም ብለዋል።

እ ጎ አ በ 1989 ዓ ም የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት ከፈረሰች በኋላ ፤ የአውሮፓው ሕብረትና የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ድርጅት ወደ ምሥራቅ ሲስፋፋ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን ፤ ወደ ዩክሬይን ሲጠጋ ግን ሩሲያ ፣ በቃ! ያለች ነው የመሰለው። ፕሬዚዳንት ዖባማ ስለገጠሟቸው ዐበይት ተግዳሮቶች በርንስ እንዲህ ይላሉ---

«እንደሚመስለኝ ፕሬዚዳንት ዖባማ፣ ሁለታ ታላላቅ ተግዳሮቶች ተደቅነውባቸዋል።አንደኛው ፤ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን፣ በክሪሚያና ዩክሬይን ለፈጸሙት ጠብ ጫሪነትና አውሮፓ ውስጥ በከፊል የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን አንዳንድ ከፋፋይ ሁኔታዎች እንዲከሠቱ በማድረጋቸው፤ ከጀርመንና አንዳንድ ሃገራት ጋር በማበር አንድ ዓይነት ምላሽ መስጠት የሚለው ሲሆን ፣ ሌላው እስያ ውስጥ በደቡብና በምሥራቅ ቻይና ባህር የቻይና መስፋፋት የደቀነው ሥጋት ነው። »

እናም፤ እ ጎ አ ከ 2005 እስከ 2008 በፕሬዚዳንት ደብልዩ ቡሽ የአስተዳደር ዘመን ፣ ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት የፖለቲካ ልሂቅ ፣የዩናይትድ ስቴትስ አመራር አንድ ዓይነት እርምጃ የሚወስድበት ጊዜው አሁን ነው ይላሉ--

«ለአሜሪካ አመራር ፣ ጊዜው አሁን ነው። በአውሮፓና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ያለውን ግንኙነት በ«ኔቶ» በኩል ማቀራረቢያ ው ጊዜ አሁን ነው። እንደሚመስለኝ ዩናይትድ ስቴትስ ይህን በአመራር ልትወጣው ትችላለች። ይህን ከፕሬዚዳንታችን ማየት እንሻለን።»

ዖባማ፤ የክሪሚያው ሕዝበ ውሳኔ ሲካሄድ ፤ በፑቲን ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ አልወሰዱም ተብለው በሴናተር ጆን ማክ ኬይን በተደጋጋሚ መወቀሳቸው የሚታወስ ነው። ይሁን እንጂ፤ የኑክልየር ጦር ባለቤት በሆነችውን ሩሲያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ፈጽሞ የማይታሰብ እጅግ አደገኛ ሁኔታ ነው ሲሉ በርንስ ያስጠነቅቃሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፤ ዩክሬይን የ «ኔቶ» አባል ሃገርም አይደለችም።

«መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልና ፕሬዚዳንትዖባማ፣ የሚሰጠው ምላሽ በ3 ደረጃ የሚከናወን ሊሆን ይገባዋል ማለታቸው አስተዋይነትን ነው የሚጠቁመው። በመጀመሪያ የዩክሬይንን መንግሥት መርዳት ይኖርብናል። ሁለተኛ ለ«ኔቶ» ተጓዳኞች ፣ ለምሳሌ ለፖላንድ፣ ኢስቶኒያ ላትቪያና ሊትዋንያ --ለዩክሬይን ለሚቀርቡ አገሮች የፀጥታ ደኅንነት ዋስትና እንደምንሰጥ ማረጋገጥ ይኖርብናል። ሦስተኛ፣ አውሮፓና ዩናይትድ ስቴትስ፣ ፕሬዚዳንት ፑቲን ለወሰዱት ሕገ-ወጥ ርምጃ የሚመጥነውን የገንዘብ መጠን መጥቀስ ይኖርባቸዋል። ይህም ሲሆን ነው የማዕቀቡ እርምጃ ትርጉም የሚኖረው።»

ፕሬዚዳንት ዖባማ፤ የቀድሞውን የሊቢያውን መሪ ሙአመር ጋዳፊን በኃይል ከሥልጣን እንዲወገዱ ካበቁ በኋላ አገሪቱ በዴሞክራሲ ራሷን እንድትገነባ አላደረጉም ተብለው ይወቀሳሉ። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አምና፣ የበሺር አል አሰድን መንግሥት ፣ ህዝብ በመርዘኛ ጋዝ በማጥቃቱ ሳቢያ ለመደብደብ ከተዘጋጀ በኋላ፤ ዖባማ ሐሳባቸውን መለወጣቸው የሚታወስ ነው። በዚህም ሪፓብሊካውያኑ ከባድ ስህተት ነው የተሳሳቱት በማለት ይወቅሷቸዋል። ፑቲን ፣ ዖባማ ዝተው ተግባራዊ አለማድረጋቸውን፤ ፣ ባለፉት 5 ዓመታትም አካሄዳቸውን በመከታተል ጠንቅቀው ለማወቅ ችለዋል ያሉት፤ ወግ አጥባቂው የኮንግረስ አባል ቻርለስ ዴንት እንዲህ ብለዋል።

«ከኢራን ጋር ባደረግነው የኑክልየር መርኀ ግብር ድርድር፣ በጥሞና ተከታትለውናል። ዩናይትድ ስቴትስ፤ በተናጠል፤ የሚሳይል መከላከያ አውታሯን ከቼክ ሪፓብሊክና ከፖላንድ ማንሳቷን ፑቲን ዐይተዋል። ስለሆነም ዩናይትድ ስቴትስ፤ በዓለም ዙሪያ ከነበራት ኀላፊነት በማፈግፈግ ላይ እንደሆነች የተገነዘቡት የሩሲያው መሪ በተወሰነ ደረጃ ክፍቱን ቦታ መሙላት እንደሚችሉ ተሰምቷቸዋል። »

ዲፕሎማቱ ኒኮላስ በርንስም፤ አገራቸው ከሶሪያ ማፈግፈጓን የተሳሳተ ምልክት ሰጪ ነው ባይ ናቸው።

«የሆነ ካርታ ላይ መሥመር አሰመርን፤ ሶሪያ ከዚህ መሥመር ማለፍ የለባትም ብለን፤ ካለፈች ቅጣት እንደምታገኝ አስጠነቀቅን፤ ግን ቅጣት አላገኘችም። እንደሚመስለኝ እዚህ ላይ ስህተት ተሠርቷል።ነገር ግን ዩናይትድ ስቴትስ ለስለስ አላች ወይም ተሞኘች የሚለውአባባልም ሆነ ተጽእኖዋን ለማሳረፍ አልደረፈረችም የሚለው አነጋገር ሚዛናዊ አይደለም። »

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic