ኦስሎ፤ የሰላም ኖቤል ሽልማት ለቱኒዚያ | ዓለም | DW | 09.10.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኦስሎ፤ የሰላም ኖቤል ሽልማት ለቱኒዚያ

የዘንድሮዉ የሰላም ኖቤል ሽልማት ቱኒዚያ ዉስጥ ከጃዝሚን ሕዝባዊ አብዮት ማግስት ሀገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድትሸጋገር አብቅቷል ለተባለዉ ለአራት የቱኒዚያ ሲቪክ ማኅበራት ጥምረት ተሰጠ።

የኖቤል ተሸላሚዎችን የሚመርጠዉ መድረክ ለብሔራዊ የዉይይት ጥምረቱ የተሰጠዉ የሰላም ኖቤል ሽልማት የቱኒዚያን ሕዝብ እንደሚያበረታታ እና ሌሎችንም በተለይ በመካከለኛዉ ምሥራቅ የሚገኙ ዴሞክራሲ ለቸገራቸዉ ሃገራት ማነቃቂያ ይሆናል ብሏል። አምስት አባላት ያሉት የኖቤል የሰላም ሽልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር ኩልማን ፋይቭ የኮሚቴዉን ዉሳኔ እንዲህ ነበር ይፋ ያደረጉት፤

Norwegen Kaci Kullmann Five Bekanntgabe der Friedensnobelpreisträger 2015

የኖቤል ሰላም ሽልማት ኮሚቴዉ ሊቀመንበር

«የኖርዌይ የኖቤል ኮሚቴ የ2015ን የኖቤል የሰላም ሽልማት ከጃስሚን አብዮት ማግስት ቱኒዚያ ዉስጥ ዴሞክራሲያዊ አብዝሃዊነት እንዲገነባ ላደረገዉ ወሳኝ አስተዋፅኦ ለቱኒዚያዉ የአራት ብሔራዊ የዉይይት ጥምረት እንዲሰጥ ወስኗል። ጥምረቱ የዛሬ ሶስት ዓመት በበጋ ወራት በፖለቲካዊ ግድያዎችና በተንሰራፋዉ ማኅበራዊ አለመረጋጋት ምክንያት የዴሞክራሲዉ ሂደት የመንኮታኮት አደጋ በገጠመዉ ወቅት ነበር። ሀገሪቱ ወደእርስበርስ ጦርነት ልትገባ አፋፍ ላይ ደርሳ በነበረበት ወቅት ሰላማዊ የፖለቲካ ሂደትን በአማራጭነት መሥርቷል። በዓመታት ዉስጥም ቱኒዚያ የፆታ፣ የፖለቲካ አስተሳሰብም ሆነ ሃይማኖት ሳይገድበዉ የሁሉንም መሠረታዊ መብቶች የሚያከብር ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት ያለዉ መንግሥት እንዲመሠረትም አስተዋፅኦ አድርጓል።»

Tunesien Houcine Abassi Gewerkschafter einer der Friedensnobelpreisträger

ከዘንድሮዉ የቱኒዚያ ተሸላሚዎች አንዱ

ሽልማቱ አስቀድሞ ሊሰጣቸዉ ይችል ይሆናል በሚል በከፍተኛ ደረጃ የተገመቱና የተጠበቁ እያሉ ለቱኒዚያዉ የብሔራዊ የዉይይት ጥምረት መሰጠቱ ድንገተኛ ነበር። የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴዉ ከአረቡ ዓለም አብዮት ጋር በተገናኘ ሽልማቱን ሲሰጥ ጥምረቱ ሁለተኛ መሆኑ ነዉ። በጎርጎሪዮሳዊዉ 2011,ም የመናዊቱ ጋዜጠኛ ታዋኮል ካርመን የየመንን አገዛዝ በመታገል ላበረከተችዉ አስተዋፅኦ ሽልማቱን ከላይቤሪያ መሪ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ እና ከላይቤሪያዊቱ የሰላም ተሟጋች ለይማህ ጎቤዌ ጋር ተጋርታለች። ሽልማቱ የወርቅ ሜዳልያ፣ ዲፕሎማ እና 950ሺ የአሜሪካን ዶላር ሲሆን የዘንድሮዎቹ ተሸላሚዎች የፊታችን ኅዳር 30ቀን ኦስሎ ተገኝተዉ ይቀበላሉ።

SL/HM