ኦሳማ ቢን ላደንና አልቃይዳ | ዓለም | DW | 05.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኦሳማ ቢን ላደንና አልቃይዳ

ኦሳማ ቢን ላደን እስከተገደለበት እና አልቃይዳም ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ በሚጠራው ቡድን ቦታውን እስከተቀማበት ጊዜ ድረስ ለዩናይትድ ስቴትስ ቁጥር አንድ ጠላት ነበር ፤ ለዓለማችን ደግሞ የአሸባሪነት መገለጫ ።ኦስማ ቢን ላደን ከተገደለ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ አምስት አመት ሆነው ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:31
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:31 ደቂቃ

ኦሳማ ቢን ላደን እና አልቃይዳ

ኦሳማ ቢን ላደን ከመጀመሪያው አንስቶ የአሸባሪው ቡድን የአልቃይዳ መሪ ነበር ። ድርጅቱን አልቃይዳ ሲል የሰየመውም ሆነ አፍጋኒስታን የበሩ ተዋጊዎችንም በገንዘብ ይደግፍ የነበረውም እርሱ ነው ። ኦስማ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የወጣው በ1980 ዎቹ አፍጋኒስታን ከነበረው የሶቭየት ህብረት ጦር ጋር ጦርነት በተካሄደበት ወቅት ነው ። ያኔ የአረብ ተዋጊዎች አፍጋኒስታን የሚገኙ በእምነት አንድ የሆኑ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ህብረት ፈጠሩ ። ለብዙ ጊዜያት ልል ሆኖ የቆየው ይህ የጂሃዲስቶች ህብረት በኦሳማ ቢን ላደንና በሁለተኛው ሰው በአይማን አል ዛውሃሪ በጎርጎሮሳዊው 1997 ዓለምን ስጋት እና ሽብር ውስጥ ወደከተተው ወደ «አልቃይዳ» ተቀየረ ። ከዚያም የአልቃይዳ ማሰልጠኛ ካሞፖች ተገንብተው ቢን ላደን በሙስሊሙ አለም የምዕራባውያንን ተጽእኖ ለመታገል የሚያካሂደው ትግል የጂሃዲስቶች ትግል ሆነ ። ድርጅቱ ከተቋቋመ ከ4ዓመታት በኋላ ቢን ላደን ጥንካሬውን ለዓለም ያሳየበትን እጅግ አደገኛ የሽብር ጥቃቶች በጎርጎሮሳዊው መስከረም 11 2001 አም በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጣለ ። ከዚያም አሸባሪዎችን ለመቅጣት የአሜሪካን የአፀፋ ጥቃት ተከተለ ።በዚያው አመት አሜሪካን አልቃይዳንና ታሊባንን ለመውጋት ጦርዋን አፍጋኒስታን አዘመች ። ቢን ላደንና ተዋጊዎቹም ወደ ሰሜን ፓኪስታን አፈገፈጉ ። የአልቃይዳ ሚሊሽያዎችም በአንዳንድ የአፍጋኒስታንና የፓኪስታን ክፍሎች ጠንካራ ይዞታቸውን አጡ ። ከዚያ በኋላም ቢን ላደን

Bin Laden und El Zawahiri in El Kaida Camp

አብዛኛውን የድርጅቱን ሥራና በየቦታው ለተበታተኑት ጂሃዲስት ቡድናት የሚተላለፈውን መልዕክት ለምክትሉ ለዛዋሀሪ ትቶ ተሰወረ ። አል ቃይዳ በኢራቅ ውስጥ ተጠናክሮ መንቀሳቀስ የጀመረው ደግሞ አሜሪካን በ2003 ዓም ኢራቅን ከወረረች በኋላ ነው ። አፍጋኒስታን ውስጥ ለብዙ አመታት የተዋጋው አቡ ሙሳብ አል ዛርካዊ ከተባባሪዎቹ ጋራ ኢራቅ ውስጥ ያለውን በጣም ጨካኙን ቅርንጫፍ ድርጅት መሪነት ያዘ ። የቢን ላደን ትግል ከምዕራባውያኑና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ነበረ ። ሺአዎችን እንደሚጠላ ይነገርለት የነበረው ዛርካዊ በሺአ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ያደርስ ስለነበረ ይህን እንዲያስተካክል ቢጠየቅም ውጤት አልተገኘም ። በበርሊኑ የሳeineስና የፖለቲካ ጉዳዮች ጥንate ተቋም የሽብር ጉዳዮች አዋቂ ጊዶ ሽታይንበርግ እንደሚሉት በዚህ የተነሳ ዛርካዊ እና ቢን ላደን ይጋጩ ነበር ። ለዚህም እንደ አብነት ያነሱት በአንድ ወቅት ከአልቃይዳ አመራር ለዛርካዊ የተፃፈውን ደብዳቤ ነው ።
«ዝዋሃሪ ፣ ዛራካዊ ስልታዊ ለውጥ እንዲያደርግ የሞከረበትን ዝነኛ ደብዳቤ በጎርጎሮሳዊው 2005 ዓም ጽፎለት ነበር ይሄ ደብዳቤ ምንም ያመጣው ነገር የለም ። ይህም የኢራቁ አልቃይዳ በራሱ ፍላጎት የሚንቀሳቀስ መሆኑን ነው የሚያሳየው ።
አቡ ሙሳ ዛርካዊ በ2006 ዓም በአሜሪካኖች ጥቃት ተገደለ ። የኢራቁ አልቃይዳ ከዛርካዊ ሞት በኋላ ቢዳከምም ፈፅሞ አልጠፋም ። ከአምስት ዓመት በኋላም የአልቃይዳው መሪ ኦስማ ቢን ላደን በተደበቁበት ፓኪስታን ውስጥ በጎርጎሮሳዊው

ግንቦት 2 2011 ዓም በዩናይትድ ስቴትስ ተገደሉ ።ይህንንም የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ለህዝባቸውና ለዓለም ይፋ አደረጉ ።
« ዛሬ ለአሜሪካን ህዝብ እና ለዓለም ዩናይትድ ስቴትስ የአልቃይዳ መሪና በሺህዎች ለሚቆጠሩ ወንዶች ሴቶችና ህፃናት ግድያ ተጠያቂ የሆነው ኦሳማ ቢንላደን የተገደለበትን ዘመቻ ማካሄዷን አሳውቃለሁ ። »
የዛሬ አምስት ዓመት የተገደለው ኦሳማ ቢን ላደን ምንም እንኳን መንፈሳዊ መሪ ነኝ ብሎ ባይናገርም ሽታይንበርግ እንዳሉት በተከታዮቹ ዘንድ ሃይማኖትና ፖለቲካን አጣምረው እንደያዙት ጥንታዊ መሪዎች ከፍተኛ ተቀባይነት ክብርና ግርማ ሞገስ ነበረው ። እሱን የተካው ዛዋሃሪ ግን በቀጣዮቹ አመታት ጂሃዲስቶችን እንደ ቢንላደን ማነሳሳት አልቻለበትም ። እንደ ሽታይንበርግ ይህም ከአውሮጳና ከመላው ዓለም የተሰባሰቡት የአልቃይዳ ወጣት ተዋጊዎች ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራውን ቡድን የተቀላቀሉበት አንዱ ምክንያት ነው ። በአሁኑ ጊዜ ከአልቃይዳ ይልቅ በዓለማችን በአሸባሪነት ትልቁን ቦታ የያዘው ራሱን እስላማዊ መንግስት ብሎ የሚጠራው ይኸው ቡድን ነው ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic