ኦሮሚያ፣ የ“ኢኮኖሚ አብዮት” | ኢትዮጵያ | DW | 10.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

ኦሮሚያ፣ የ“ኢኮኖሚ አብዮት”

የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት ሰሞኑን ደጋግመዉ የሚናገሩት አንድ ሐረግ አለ። የ«ኦሮሞ ኢኮኖሚ አብዮት» የሚል፡፡ የኢኮኖሚ አብዮቱ ኢላማ ያደረገው በክልሉ በነበረው ህዝባዊ አመጽ ተሳትፎ የነበራቸውን ወጣቶች ነው፡፡ ለወጣቶቹ ሥራ ለመፍጠር በመንግስትና በግል ትብብር ሊመሰረቱ የታቀዱ ድርጅቶችን በበላይነት የሚመራ ምክር ቤት መቋቋሙ ተነግሯል፡፡ 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:24

ዕቅዱ የህዝቡን ጥያቄዎች ያልመለሰ ነው በሚል ተተችቷል

የምክር ቤቱ ሃያ አምስት አባላት በቅርቡ ሥለ መተዳደሪያ ሕጉ ተወያይተዋል፡፡ ሊመሰረቱ ከታሰቡ ድርጅቶች የሁለቱን የአክሲዮን ድርሻዎች ለገበያ የሚቀርቡባቸውን ቀናትም ወስነዋል፡፡ ከድርጅቶቹ አንዱ ኦዳ የተቀናጀ ትራንስፖርት አክሲዮን ማህበር ነው።  ማኅበሩን የሚያደራጅ ስምንት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተሰይሟል፡፡ የኦሮሚያ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታከለ ኡማ የኮሚቴዉ አባል ናቸዉ። 

“እንደምናውቀው ሀገራችን ውስጥ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ከፍተኛ ነው፡፡ ኢኮኖሚው እያደገ ነው፡፡ የኢኮኖሚውን ዕድገት እና የህብረተሰብ ትስስሩን ሊያፋጥን የሚችል ደግሞ ዘመናዊ ትራንስፖርት ያስፈልጋል ከማለት እና በሀገራችን ውስጥ  በተለይ ደግሞ በትራንስፖርት ዙሪያ ያለውን ፍላጎትና አቅርቦቱን ለማመጣጠን ነው ዋናው አላማ፡፡ ይሄ ሲደረግ ደግሞ በመንግሥትና በግል ባለሀብት አንድ ላይ በመቀናጀት ነው፡፡ በተለይ የኦሮሞ አርሶ አደር፣ ትንንሽ ሃብቶችን እያፈሩ ያሉ ወጣቶች አሉ፡፡ እነርሱንም በማቀናጀት አንድ ላይ የሚሰራ ሂደት ነው ማለት ነው” ይላሉ የቢሮ ኃላፊው፡፡  

የሚቋቋመው ድርጅት 400 ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮችን እና ባለሀብቶችን በባለአክሲዮንነት ለማሳተፍ አቅዷል፡፡ የባለአክሲዮኖቹ ቁጥር ወደፊት ወደ አንድ ሚሊዮን ሊያድግ እንደሚችል አቶ ታከለ ይናገራሉ፡፡ ድርጅቱ በበርካታ ዘርፎች እንደሚሰማራ የሚገልጹት የቢሮ ኃላፊው ዋናው ትኩረቱ ግን የህዝብ ማጓጓዣ አገልግሎት መስጠት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ 

“የህዝብ ትራንስፖርቱ እንግዲህ ዘመናዊ የሆነ ትንንሽ ትራንስፖርቶችን የሚደግፍ ደግሞ ደረጃውም ከፍ ያለ ነው፡፡ ሁለተኛ የደረቅ ትራንስፖርትም አለው፡፡ ደረቅ ትራንስፖርት ስንል ትናንሽ ትራንስፖርቶች ሳይሆን በተለይ ከአዲስ አበባ ራቅ ባለ ቦታ የእርሻ ምርቶችን ወደዋናው ገበያ የሚያመጣ ነው፡፡ የፍሳሽ ትራንስፖርትም አለ፡፡ እንግዲህ እነዚህን ሁሉ ስናስገባ ነዳጅ ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ባለአክሲዮኖቹ እና አርሶ አደሩም የሚሳተፉበት የነዳጅ ማደያ ይኖራል፡፡ ትልልቅ ማደያዎች ሆነው በእያንዳንዱ ከተማ እና ወረዳ ላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን ወደ ሥራ ሊያስገባ በሚችል ሁኔታ እየተሰራ ያለ ነው፡፡ የመኪና መገጣጣሚያዎችን ደግሞ እዚያው ድርጅቱ ቀስ በቀስ እየገጣጠመ እንግዲህ ከመገጣጠምም አልፎ ወደ ማምረት ለመግባት ነው” ሲሉ የድርጅቱን ትልም ይዘረዝራሉ፡፡  

ይህን የትራንስፖርት ድርጅት ጨምሮ በ“ኦሮሞ ኢኮኖሚ አብዮት” የመጀመሪያ ምዕራፍ ወደ ተግባር ሊገቡ የተዘጋጁ ድርጅቶች የተሰማሩባቸው ዘርፎች በግል ባለሀብቶች ሊሸፈኑ የሚችሉ ናቸው፡፡ ይህ የክልሉ አካሄድ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሚከተለው “የነጻ ገበያ መርሆ ጋር አይጋጭም?” ለሚለው ጥያቄ አቶ ታከለ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ 

“ቀጥታ መንግሥት እየገባ አይደለም፡፡ መንግሥት እየገባ ያለው በምንድነው? ለትርፍ የተቋቋሙ ኢንተርፕራይዞች አሉ፡፡ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልላችን ውስጥ ወደ 11 የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞች ለትርፋቸው የተቋቋሙ አሉ፡፡ ኢንተርፕራይዞች ትርፋማ ናቸው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ባለሀብቱን መደገፍ አለበት፡፡ እንደዚህ ትልልቅ አክሲዮኖች በትንንሽ ባለሀብቶች ለማይሰሩና ትልቅ ብር ስለሚፈልጉ መንግሥት ባለሀብቱን አደራጅቶ፣ አቀናጅቶ ወደዚህኛው ቢዝነስ ማስገባት አለበት፡፡ መንግስት በኢንተርፕራይዝ በኩል ገብቶ እንዲያግዛቸው ነው እንጂ መንግሥት የግሉን ባለሀብት እንዳይወዳደሩ እንዳይሰሩ ለማድረግ አይደለም፡፡ ይልቁንስ ለግል ባለሀብት መደላደል ለመፍጠር ነው የታቀደው” ሲሉ የክልላቸውን እቅድ ተከላክለዋል፡፡ 

የኦሮሚያ ክልል መንግሥትን ዕቅድ አስመልክተው በፌስ ቡክ አድራሻችን አስተያየታቸውን የሰጡ አብዛኞቹ ተከታታዮቻችን “የህዝቡን ዋንኛ ጥያቄዎች ያልመለሰ ነው” ሲሉ ተችተውታል፡፡ ስማቸውን ያልጠቀሱ  አድማጫችን አስተያየታቸውን በድምጽ አጋርተውናል፡፡ 

“የኦሮሚያ መንግሥት በክልሉ ተነስቶ ለነበረው አመጽ ምክንያት የሆኑቱን ቅሬታዎች ለመፍታት ጥረት አደርጋለሁ ማለቱ መልካም ነው፡፡ ለቅሬታዎቹ መላ ከመምታቱ በፊት ግን ቅሬታዎቹንና ችግሮቹን በትክክል ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩን ማወቅ የመፍትሄው ግማሽ ነው፡፡ እንደ ክልሉ መንግሥት ዋናው ችግር የወጣቶች ሥራ አጥነት ነው፡፡ በእኔ እምነት ሥራ አጥነት እንደችግር ቢኖርም ዋናው ቅሬታ እርሱ አይመስለኝም፡፡ የተነሳው ጥያቄ ሥራ ስጡን ሳይሆን ባርነት ይብቃን የሚል ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁ ችግር ‘የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሳትፎ የለንም፣ ተገልለናል’ የሚል ነው፡፡ መፍትሄ ማግኘት ያለበትም ይሄ ይመስለኛል፡፡” 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ
 

Audios and videos on the topic