እግር ኳስ፣ ቴኒስ፥ ቡጢና ሌሎች ዘገባዎች | ስፖርት | DW | 01.12.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

እግር ኳስ፣ ቴኒስ፥ ቡጢና ሌሎች ዘገባዎች

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ቸልሲ ፈጣን ግስጋሴው ገታ ብሏል፥ የአምናው ባለዋንጫ ማንቸስተር ሲቲ እግር በእግር መከተሉን አላቋረጠም። በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ኃያሉ ባየር ሙንሽን እንደልማዱ ሊጋው ከመጠናቀቁ ቀደም ብሎ ዋንጫውን ለመጨበጥ ተቃርቧል፤ የቀድሞው ብርቱ ተፎካካሪ ቦሩስያ ዶርትሙንድ አቅም አንሶት በወራጅ ቃጣናው ጠርዝ ላይ እያጣጣረ ነው።

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ የእግር ኳስ ፍልሚያ በሳምንቱ ማሳረጊያ የቸልሲ ነጥብ መጣል ለዋነኛ ተፎካካሪው ማንቸስተር ሲቲ ያልታሰበ ሲሳይ ነው የሆነለት። ከትናንት በስትያ ቸልሲ ከሰንደርላንድ ጋር ገጥሞ ያለምንም ግብ በመለያየት ነጥብ ተጋርቷል። 27 ነጥቦችን የሰበሰው ማንቸስተር ሲቲ ግን ትናንት ሳውዝሀምፕተንን 3 ለባዶ ለመሸኘት ተሳክቶለታል። በእዚህም መሠረት ማንቸስተር ሲቲ በደረጃ ሠንጠረዡ አንደኛ ከሆነው ቸልሲ ጋር የሚለይበትን ነጥብ ለማቀራረብ ችሏል። ቸልሲ በ33 ነጥብ አንደኛ፥ ማንቸስተር ሲቲ በ27 ነጥቦች ኹለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። የቸልሲን ፈጣን ግስጋሴ የተገዳደረው ሳውዝሀምፕተን በ26 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ከሊቨርፑል ጋር ተመሳሳይ ነጥብ ያለው ኤቨርተን ትናንት በቶትንሐም ሆትስፐር 2 ለ1 ተረትቷል። ባለ 17 ነጥቡ ሊቨርፑል ከትናንት በስትያ ስቶክ ሲቲን 1 ለ ዜሮ አሸንፎ የቁልቁለት ጉዞውን ለጊዜውም ቢሆን ገታ ማድረግ ችሏል። በደረጃ ሠንጠረዡ አራተኛ ተርታ የተሰለፈው ማንቸስተር ዩናይትድ ሁል ሲቲን 3 ለ ምንም ፀጥ አድርጓል። ከትናንት በስትያ ዌስት ሀም ዩናይትድ ኒውካስልን፣ አርሰናል ዌስት ብሮሚችን 1 ለባዶ አሸንፈዋል። አርሰናል በ20 ነጥብ 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፥ ዌስት ሀም ዩናይትድ በ21 ነጥብ አምስተኛ፣ ቶትንሀም ሆትስፐር በ20 ነጥብ 7ኛ፣ ከክሪስታል ፓልስ ጋር አንድ እኩል የተለያየው ስዋንሲ ሲቲ እና ኒውካስል እኩል 19 ነጥቦችን ይዘው 8ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ፤ መከረኛው ሊቨርፑል ከኤቨርተን ጋር በተመሳሳይ 17 ነጥብ ይዞ 11ኛ ደረጃ ላይ ይቃትታል። ከትናንት በስትያ ኩዊንስ ፓርክ ሌስተር ሲቲን 3 ለ2 ሲረታ፥በርንሌይ ከአስቶን ቪላ ጋር አንድ እኩል ተለያይተዋል።
የባየር ሙንሽኑ ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየር

የባየር ሙንሽኑ ግብ ጠባቂ ማኑኤል ኖየር

የፕሪሚየር ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነቱን የማንቸስተር ሲቲው ሰርጂዮ አጉዌሮ በ12 ግቦች በቀዳሚነት እየመራ ነው። በቅዳሜው ጨዋታ በዘንድሮ የውድድር ዘመን 5ኛ ቢጫ ካርድ የተሰጠው የቸልሲው ዲዬጎ ኮስታ በ11 ግቦች ይከተላል። ዲዬጎ ስታምፎርድ ብሪጅ ሜዳ በሚካሄደው የረቡዕ ግጥሚያ መሰለፍ አይችልም። የዲዬጎን ከአንድ ጨዋታ መታገድ በተመለከተ የቸልሲው አሠልጣኝ ጆሴ ሞሪንሆ ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «ስለተጎዱ አለያም ከጨዋታ ስለታገዱ ተጨዋቾች አናለቅስም፥ ረፍት ወስዶ ለቅዳሜው የኒውካስል ግጥሚያ ታድሶ መምጣት ይችላል» ብለዋል። አያይዘውም፥ ለረቡዕ ጨዋታ ሬሚን ወይንም ዲዲየር ድሮግባን እንደሚያሰልፉ ተናግረዋል። የአርሰናሉ አሌክሲስ ሳንቼዝ በ8 ከመረብ ያረፉ ኳሶች በሦስተኛ ኮከብ ግብ አግቢነት እየተከተለ ነው።
በጀርመን ቡንደስ ሊጋ ዘንድሮ እንደ ቦሩስያ ዶርትሙንድ የተንኮታኮተ የእግር ኳስ ቡድን የለም። ዶርትሙንድ ትናንት ከአይንትርራኅት ፍራንክፉርት ጋር ተጋጥሞ እጅ ሰጥቷል። የቀድሞው ብርታቱ የከዳው ዶርትሙንድ 2 ለ ዜሮ በመረታት በጀርመን ቡንደስሊጋ ታሪክ ከ29 ዓመታት ወዲህ በወራጅ ቃጣናው ስር ለመገኘት ተገዷል። እጎአ በ1985 ዓም የውድድር ዘመን በ16ኛነት ለማጠናቀቅ ተገዶ የነበረው ዶርትሙንድ ዘንድሮ የመጨሻው ጠርዝ፤ 18ኛ ላይ ተንበርክኮ ትንንሾቹ አዲስ ገቢዎች እነ ፓዴርቦርንን ተንጠራርቶ ለማየት ተገዷል። የዶርትሙንድ የትናንት ሽንፈትን ከመቀበል ውጪ ምንም ማድረግ ያልቻሉት የቡድኑ አሠልጣኝ ዩየርገን ክሎፕ በሐዘን ድባብ ተውጠው እንዲህ ብለዋል።
ተደጋጋሚ ሽንፈት የገጠመው ቦሩስያ ዶርትሙንድ

ተደጋጋሚ ሽንፈት የገጠመው ቦሩስያ ዶርትሙንድ

«በዛሬው ጨዋታ ያለንበትን ሁናቴ ቀይረን ማሻሻል ፈልገን ነበር፥ እንችልም ነበር። ያ አልተሳካልንም። ተቃራኒው ነው የሆነው። እንዲያም ሆኖ እንቀጥላለን።»
ዎልፍስቡርግ ቦሩስያ ሞይየንሽንግላድባኅን 1 ለ0 ተሸንፏል። ከትናንት በስትያ በተከናወኑ ግጥሚያዎች ባየር ሌቨርኩሰን ኮሎኝን 5 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶታል። ሻልካ ማይንትስን 4 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት ረትቷል። ቬርደር ብሬመን ፓዴርቦርንን 4 ለ ምንም ሸኝቷል። ሆፈንሃይም ሐኖቨርን 4 ለ3አውስቡርግ ሐምቡርግን 3 ለ1 እንዲሁም ባየር ሙንሽን ሔርታ ቤርሊንን 1 ለባዶ አሸንፈዋል።
በደረጃ ሠንጠረዡ ኃያሉ ባየር ሙንሽን በ33 ነጥቦች በብቸኝነት ተኮፍሷል። ዎልፍስቡርግ በ26 ነጥብ ይከተለዋል። ባየርን ሙንሸን ባለፈው ዓመት የውድድር ዘመን 13ኛ ጨዋታውን ካከናወነ በኋላ በኹለተኛነት ከሚከተለው ቡድን ጋር የነበረው የነጥብ ልዩነት 4 ነበር፥ ዘንድሮ ልዩነቱን ወደ 7 ከፍ አድርጎታል። በፔፕ ጉዋርዲዮላ የሚመራው ባየርን ሙንሽን ከእዚህ በተጨማሪ ባለፈው ማክሰኞች በእንግሊዙ ማንቸስተር ሲቲ 3 ለ2 ቢረታም በሻምፒዮንስ ሊግ የምድቡ ቀዳሚ ሆኖ ለማለፍ ችሏል። የማክሰኞው ሽንፈት ባየርን በእዚህ የውድድር ዘመን የገጠመው የመጀመሪያው ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል።
ባየር ሙንሽን እና ማንቸስተር

ባየር ሙንሽን እና ማንቸስተር

ባየር ሌቨርኩሰን በ23 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። አውስቡርግ በ21 ነጥብ አራተኛ፣ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ እና ሻልካ በተመሳሳይ 20 ነጥቦች ሆኖም በግብ ክፍያ ልዩነት 5ኛ እና 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ቦሩስያ ዶርትሙንድ በ11 ነጥብ የደረጃ ሠንጠረዡ መጨረሻ ጠርዝ 18ኛ ላይ ተወስኗል።
በቡንደስሊጋው በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የአይንትራኅት ፍራንክፉርቱ አሌክሳንደር ማየር በ1ኛነት ይመራል፥ እስካሁን 8 ግቦች አስቆጥሯል። የባየር ሌቨርኩሰኑ ካሪም ቤላሪብ፣ የባየር ሙንሽኑ ማሪዮ ጎዬትሰ የማይንትሱ ሺንጂ ኦካሳኪ እና የሻልካው ክላስ ያን ሁንቴላር በተመሳሳይ 7 ግቦችን በማስቆጠር አሌክሳንደር ማየርን ይከተሉታል።
የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያ

የአውሮጳ ሊግ ግጥሚያ

በስፔን ላሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያ ትናንት ሴቪላ ግራናዳን 5 ለ1 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል። አትሌቲኮ ማድሪድ ዴፖርቲቮ ኮሩናን 2 ለዜሮ እንዲሁም ባርሴሎና ቫሌንሺያን 1 ለባዶ ረትተዋል። ቪላሪያል ኮርዶባን 2 ለባዶ ሸኝቷል። ከትናት በስትያ ሪያል ማድሪድ ማላጋን፣ ኤስፓኞላ ሌቫንቴን እንዲሁም አትሌቲክ ክለብ ጌታፌን 2 ለ1 አሸንፈዋል። ሴልታቪጎ በአይበር 1 ለዜሮ ተሸንፏል።
በእዚህም መሠረት፣ ሪያል ማድሪድ በ33 ነጥብ ቀዳሚነቱን ይዟል። ዋነኛ ተፎካካሪው ባርሴሎና በኹለት ነጥብ ዝቅ ብሎ ይከተለዋል። አትሌቲኮ ማድሪድ 29 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በስፔን ላሊጋ የሪያል ማድሪዱ ክሪስቲያኖ ሮናልዶ 20 ኳሶችን ከመረብ በማሳረፍ ኃያል ግብ አዳኝነቱን አስመስክሯል። የባርሴሎናው ኔይማር ከሮናልዶ በግማሽ ዝቅ ብሎ 11 ግቦችን በማስቆጠር ኹለተኛ፣ ሌላኛው የባርሴሎና ፈርጥ ሊዮኔል ሜሲ በ10 ግቦች ሦስተኛ በመሆን ይከታተላሉ።
በጣሊያኑ ሴ ሪ ኣ የጁቬንቱሱ ካርሎስ ቴቬዝ በ9 ግቦች ኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ነው። የናፖሊው ጆሴ ካሌጂዮን በ8 እንዲሁም የኤስ ሚላኑ ጄሬሚ ሜኔዝ፣ የኢንተር ሚላኑ ማውሮ ኢካርዲ፣ የናፖሊው ጎንዛሎ ሒጉዋይን እንዲሁም የኡዲኔዜው አንቶኒዮ ዲ ናታሌ እያንዳንዳቸው 7 ግቦችን በማስቆጠር ይከተላሉ።
ሴሪ ኣውን ጁቬንቱስ በ34 ነጥቦች ይመራል። ሮማ በ31 ነጥብ ይከተላል። ጄኖዋ እና ናፖሊ በ23 እና 22 ነጥቦች ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ትናንት ኢንተርሚላን በሮማ 4 ለ2 ተሸንፏል። ጁቬንቱስ ቶሪኖን እንዲሁም ፓሌርሞ ፓርማን 2 ለ1፣ ኤስ ሚላን ኡዲኒዜን 2 ለ0 አሸንፈዋል። ኤምፖሊ እና አትላንታ ያለምንም ግብ ተለያይተዋል። ጄኖዋ ሴሴናን 3 ለባዶ ረትቷል። ፊዮሬንቲና ካጊሊያሪን ያሸነፈበት የ4 ለባዶ ድል ታላቅ ሆኖ ተመዝግቧል።
የመኪና ሽቅድምድም
የፎርሙላ አንድ የመኪና ሽቅድምድም አሽከርካሪ ማርክ ቬበር ብራዚል ሳዎፖሎ ውስጥ ትናንት የመኪና አደጋ ገጠመው። የዓለም ፅናት የመኪና ሽቅድምድም የቀድሞ ባለድሉ አውስትራሊያዊው የፖርሼ አሽከርካሪ ማርክ ቬበር ትናንት አደጋ የደረሰበት ትከንፍ የነበረችው መኪናው ማቴዎ ክሬሶኒ ከሚያሽከረክራት ፌራሪ ጋር ተላትማ ነው። ከግጭቱ በኋላ ማርክ ቬበር የሚያሽከረክራት ፖርሼ በእሳት መያያዟም ተጠቅሷል። የ38 ዓመቱ ማርክ እና ጣሊያናዊው ማቴዎ ወደ ሀኪም ቤት የተወሰዱ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የሚገኙበት ሁናቴ አስጊ እንዳልሆነ ተጠቅሷል። ማርክ ከመኪና ሽቅድምድም ውድድር አምና ራሱን ማግለሉ ይታወቃል።#b
ቡጢ
በከባድ ሚዛን የቡጢ ፍልሚያ ታይሰን ፉሪ ዴሪክ ቺሶራን በ10ኛው ዙር ላይ ማሸነፉ ተገለጠ። የ26 ዓመቱ እንግሊዛዊ ታይሰን ፉሪ የሰነዘራቸው ከባድ ቡጢዎች የሀገሩ ልጅ ኪሶራ 11ኛው ዙር ፍልሚያ ከመድረሱ በፊት እጅ እንዲሰጥ አስገድዶታል። ዴሬክ ቺሶራን የረታው ታይሰን ፉሪ የእንግሊዝ እና የአውሮጳ የከባድ ሚዛን ቡጢ ባለድል ሆኗል። አሁን ታይሰን ፉሪ ወደፊት የሚጠብቀው ሦስት የተለያዩ ዓለም አቀፍ የከባድ ሚዛን የቡጢ ቀበቶዎችን የሰበሰበው ዩክሬናዊ ቭላድሚር ክሊችኮ ነው። ቭላድሚር ክሊችኮን ላለፉት ዐስር ዓመታት የሚረታው አልተገኘም።
የሜዳ ቴኒስ
በሴቶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር እጅግ ስትጠበቅ የነበረችው አሜሪካዊቷ ሴሬና ዊሊያምስ ትናንት የማኒላዋ ማቬሪክ ኪርስተንን 6 ለ3 በሆነ ልዩነት አሸንፋለች። በቡድን ጨዋታዋ ግን 1 ሚሊዮን ዶላር ለመሸለም የሲንጋፖር፣ ኒው ዴልሂ እና ዱባይ ግጥሚያዎች ይቀሯታል። በወንዶች የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ደግሞ የዓለማችን ቁጥር ኹለት ኃያል የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሮጀር ፌዴሬርን ያሸነፈው ፈረንሳዊው ጋዬል ሞንፊል በመጪው የጎርጎሪዮሳዊው አዲስ ዓመት ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ እንደሚቀርብ ከወዲሁ ቁርጠኝነቱን ገልጧል። ማኒላ ውስጥ ባደረገው ተከታታይ ጨዋታ ዓርብ ዕለት ሌይቶን ሔዊትን ቅዳሜ ደግሞ አንዲ ሙራይን ለማሸነፍ ችሏል።
የፎርሙላ አንድ ፌራሪ መኪና

የፎርሙላ አንድ ፌራሪ መኪና

የሊቨርፑሉ አሠልጣኝ ብሬንዳ ሮጀርስ የ34 ዓመቱ ሽቴፋን ዤራርድ በቡድኑ ሊቆየይ እንደሚችል ዛሬ ገለጡ። ቀደም ሲል ሽቴፋን ጄራርድ ምናልባትም ወደ አሜሪካን የእግር ኳስ ቡድኖች ሊያቀና ይችል ይሆናል ተብሎ ነበር። የቀድሞው የእንግሊዝ አማካይ ከሊቨርፑል ጋር የገባው ውል የዘንድሮው የውድድር ዘመን እስኪያበቃ የሚፀና ሲሆን፣ ከአንድ ወር በኋላ በሚገባው የጎርጎሪዮሳዊው አዲስ ዓመት ግን ወደ ፈለገው ቡድን መቀየር እንደሚችል አሠልጣኙ አስታውቀዋል።
የአትሌቲኮ ማድሪዱ ዋና አስተዳዳሪ አንጄል ጊል ማሪን በዲፖርቲቮ ደጋፊ ሞት እጃቸው ያለበትን ሰዎች በእግር ኳሱ ዓለም ቦታ የሌላቸው የማይረቡ ሲሉ ዘለፉ። ከወንዝ ውስጥ ተጎትቶ ሐኪም ቤት በልብ ድካም የሞተው የ43 ዓመቱ የዴፖርቲቮ ደጋፊ ጭንቅላቱ ላይ አደጋ እንደደረሰበት በምርመራ መረጋገጡም ተገልጧል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic