እያደገ የመጣው የኢትዮጵያ ቡና የውጪ ገቢያ እና ተግዳሮቱ
ሰኞ፣ መስከረም 20 2017
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ቡና አምራች ከሆኑ የክልሉ አከባቢዎች አንዱ በሆነው በምዕራብ ኦሮሚያ ነቀምቴ ከተማ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት በትናንትው እለት የተካሄደው ይህ መድረክ ዋና ዓላማው በቡና አመራረት ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ የጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
ጥራታቸውን ሳይጠብቁ ወደ ውጪ የሚላኩ ቡናዎች ኢትዮጵያ ከዘርፉ ተገቢውን ገቢ እንዳታገኝ ማድረጉን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡ያም ሆኖ ግን ባለፈው 2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት አገሪቱ ከየትኛውም ጊዜ የተሸለውን 1.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱን ባለስልጣኑ ገልጿል፡፡በሚቀጥለው 2017 ዓ.ም. ደግሞ ያሉትን የቡና አላላክ ተግዳሮቶችን በመቅረፍ ቡናን በብዛትም ሆነ በጥራት ወደ ውጪ ገቢያ በመላክ ከ1.8 ቢሊየን ዶላር የላቀ ገቢ ለማግኘት ስለመወጠኑም ነው የተመላከተው፡፡
የቡና አመራረት ጥራትን ለማሻሻል..
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን ከኦሮሚያ ክልል መንግስት ጋር በጋራ በመሆን ቡና አምራች ከሆኑ የክልሉ አከባቢዎች አንዱ በሆነው በምዕራብ ኦሮሚያ ነቀምቴ ከተማ የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት በትናንትው እለት የተካሄደው ይህ መድረክ ዋና ዓላማው በቡና አመራረት ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ የጥራት ችግሮችን ለመቅረፍ መሆኑን የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አዱኛ ደበላ ለዶቼ ቬለ ገልፀዋል።
የዚህ ውይይት ዋና ኣለማ የነበረው በቡና አመራረትና ለውጪ ገበያ አዘገጃጀት ላይ የሚያጋጥሙ የጥራት ተግዳሮትን በመቅረፍ በ2017 ዓ.ም. የተሻለ ምርት ወደ ውጪ ለመላክ እንዲረዳ ታስቦ ነው፡፡
“ከገቢው አንጻርም ሆነ ከሚላክበት መጠን አንጻር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የኢትዮጵያ ቡና ከጥራት አንጻር እያጋጠመ ያለውን ፈተና በመቅረፍ ከዚህ በተሻለ መጠን መላክ እንዲቻል ነው ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይቱ የተደረገው” ብለዋልም፡፡
የቡና ምርት ተግዳሮት
ከመድረኩም ሆነ ከዚያ ውጪ በቡና አመራረትናአላላክ ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች የትኞቹ ናቸው በሚል ተለይተው ይሆን በሚል የተጠየቁት ዶ/ር አዱኛ፤ “ከእለት እለት የቡና አላላክ መጠን ከፍ እያደረግን መጥተናል፡፡ ነግር ግን የጥራት ደረጃቸው የወረዱ ቡናዎች የዓለማቀፍ ገቢያ ውስጥ ገብተው የተሻለ ገቢ እንዳናገኝ እያደረጉ ስለሆነ፤ ይሄ ደግሞ አርሶ አደሩ ከሚጠብቀው ተጠቃምነት አንጻር ዝቅተኛ ገቢ እንዲገኝ ያደርጋል፡፡ ያ የሚሆን ከሆነ ደግሞ የአርሶ አደሩ የማምረት ፍላጎት ስለሚወርድ በዋናነት የትኞቹ አከባቢዎች ከደረጃ በታች የሆነ ቡና ያመርታሉ የሚለው እንዲለይና ተጠባቂውን ገቢ የሚቀንሰውን ተግዳሮት ለመፍታት ነው በትኩረት እየሰራን የምንገኘው” ብለዋልም፡፡
ወደ ውጪ ገቢያ አላላክን የገጠመው ፈተና እና የታለፈበት መንገድ
ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ቡናን ወደ ውጪ ገቢያ ለመላክና ተፈላጊውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት ከአገሪቱ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ተግዳሮቶችም አጋጥመውት ነበር፡፡ በተለይም የኢትዮጵያ ቡና ላኪ ማህበራትንም ጭምር ከዚህ በፊት ባለፈው የምርት ዘመን በጉልህ ያሰጋው የቀይ ባህር አከባቢ አለመረጋጋት በመርከቦች እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው መናወጥ በጉልህ የሚነሳ ነው፡፡ በአውሮፓ ህብረት ከደን ጭፍጨፋ ጋር ተያይዞ ቡናን የሚያመርቱ አሉ በሚል የሚቀርበው ስጋትን ያጫረው ክስ ሌላው ፈተና ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር እንደሚሉት ግን ባለፈው ዓመት በቀይ ባህር ላይ የተነሳውን ስጋት በሌሎች አማራጮች በማለፍ ጉዳት እንዳያስከትል ብደረግም ከአውሮፓ ህብረት ደንብ ጋር የሚያያዝ ክስ ግን ገና ተግባራዊ የሚደረገው በሚቀትለው ታህሳስ ወር በመሆኑ ውጤቱ አለመታወቁን ገልጸዋል፡፡ “የአውሮፓ ህብረት ደንቡ ተግባራዊ የሚደረገው በ2024 ታህሳስ ወር ላይ እንደመሆኑ ውጤቱ ገና አልታየም” ያሉት ዋና ዳይረክተሩ በቀይ ባህር አከባቢ በየመኑ ሃውቲ አማጹያን መርከቦች ላይ ጥቃት መነጣጠሩን ተከትሎ የተፈጠረውን መስተጓጎል በተለይም የቡና እጥረት በተስተዋለበት ወደ አውሮፓ ገበያ ቡናን ለመጨመሪያ ጊዜ በአየር ካርጎ በመላክ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
በ2016 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ወደ 298 ሺኅ ቶን ቡና ከኢትዮጵያ ወደ ዓለም ገቢያ ተልኮ 1.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝታል፡፡ ይህም ከምን ጊዜውም የላቀ ገቢ ስለመሆኑ ነው የተመላከተው፡፡ ሆኖም አገሪቱ ካላት ቡናን የማምረትና በጥራት ለዓለም ገቢያ የማቅረብ አቅም አኳያ የሚቀሩ ስራዎች መኖራቸውን ያሳየም ነው ተብሏል፡፡ ባለፈው ሃምሌ እና ነኀሴ ወራት እንኳ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አኳያ ከ120 ሚሊየን ዶላር የላቀ ብልጫ ያለው ገቢ የተገኘበት መሆኑንም የኢትዮጵያ ቡና እና ሻይ ባለስልጣን መረጃ ያሳያል፡፡ በመሆኑም በሚቀጥለው የ2017 ዓ.ም. የምርት ዘመን ወደ ውጪ የሚላከውን የቡና መጠን ወደ 330 ሺህ ቶን በማሳደግ የገቢ መጠኑንም 1.8 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ለማድረስ ተወጥኗልም ነው የተባለው፡፡
ስዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ፀሐይ ጫኔ