እየደመቁ የመጡት የልጃገረዶች እና ሴቶች በዓላት | ባህል | DW | 29.08.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

እየደመቁ የመጡት የልጃገረዶች እና ሴቶች በዓላት

የዘንድሮው የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና የመሳሰሉት በዓላት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በትግራይ፣ አማራ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እንደወትሮው ሁሉ በልጃገረዶች ጨዋታ ደምቀው እየተከበሩ ይገኛሉ። ባህላዊና ሃይማኖታዊ ገጽታ ያላቸው እነዚህ በዓላት ከማሕበራዊ እሴታቸው በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም እየፈጠሩ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:37

አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል በዓላት በድምቀት ተከብረዋል

ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም በሴቶች የሚከበሩት የአሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና ተመሳሳይ ይዘት ነገር ግን የተለያየ ስያሜ ያላቸው በዓላት ከጊዜ ወደ ጊዜ ትኩረት እየሳቡ እና እየደመቁ መምጣታቸው ይስተዋላል። ባህላዊ እና ሃይማኖታዊ ገጽታ ያላቸው እነዚህ በዓላት ከማሕበራዊ እሴታቸው በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም እየፈጠሩ ነው።

አሸንዳ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና ሌሎችም ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው በዓላት በተለይም በሴቶች ዘንድ የተለየ ትርጉም ይሰጣቸዋል። አሸንዳን የሚያከብሩ ሴቶች በዓሉ “የነፃነታችን ቀን ነው” ይሉታል። በአሸንዳ በዓል ሴቶች በባህላዊ መዋቢያ ደምቀው፣ ባህላዊ አልባሳት ለብሰው፣ ባህላዊ ዘፈኖችና እና ጭፈራዎች እያቀረቡ በጎዳናዎች ይታያሉ። ለአሸንዳ ዝግጅታቸውን አንድ ወር አስቀድመው የሚጀምሩ ሴቶች እንዳሉ የበዓሉ ተሳታፊዎች ይናገራሉ።

በመቐለ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል የሚያስተምሩት አቶ መብራህተን ገብረማርያም በአሸንዳ እና ከወርሐ ነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ በሚከበሩ ተመሳሳይ በዓላት ላይ ጥናት አካሄደዋል። መምህሩ “አሸንዳ ሃይማኖት የማይለይ፣ በአካባቢ የማይወሰን የብዙኃን ባህል ነው” ይላሉ። የበዓላቱ እሴቶች ማሕበራዊ ጠቀሜታቸው ከፍተኛ መሆኑንም ይገልጻሉ። 

ዘንድሮ የሻደይ፣ አሸንድዬ እና ሶለል በዓላት ከአማራ ክልል በተጨማሪ በአዲስ አበባም በድምቀት ተከብረዋል። በአከባበር ስነ ስርዓቱ ላይ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን ሴቶች እና ወጣቶች ባህላዊ ትርኢት አሳይተዋል። በመጪው እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ. ም. እንዲሁ በአዲስ አበባ የአሸንዳ በዓል የመዝጊያ ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ሙሉ ዝግጅቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ተስፋለም ወልደየስ  

Audios and videos on the topic