እክል የገጠመው የደቡብ ሱዳን ሰላም ድርድር | አፍሪቃ | DW | 13.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

እክል የገጠመው የደቡብ ሱዳን ሰላም ድርድር

የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ካለፉት ወራት ወዲህ ወደፊት መራመድ ተስኖታል። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ተፋላሚዎቹ ወገኖች ገላጋይ ሀሳብ ላይ እንዲደርሱ ለማስገደድ ፍላጎቱ እና አቅሙ የጎደለው ይመስላል።

በተፋላሚዎቹ የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና በዓማፅያኑ መካከል ካለፉት አስር ወራት ገደማ ወዲህ በምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን፣ ኢጋድ አደራዳሪነት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ባንዳንድ ልዩነቶች የተነሳ አሁንም ተቋርጦዋል። ውይይቱ ከስድስት ቀናት በኋላ የፊታችን ጥቅምት 16፣ 2014 ዓም እንደገና እንደሚጀመር የሚመለከታቸው ሁሉ አስታውቀዋል።

እንደሚታወቀው ፣ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ሀገሪቱን በፌደራዊ አወቃቀር ስልት የሚያስተዳድር መንግሥት ለመመሥረት ተስማምተዋል። በዚሁ መሠረት፣ ተቀናቃኞቹ ቡድኖች ውጊያውን እንዲያቆሙ እና አንድ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲያቋቁሙ እስካለፈው ሳምንት ድረስ ጊዜ ተሰጥቶዋቸው ነበር። ይኸው የጊዜ ገደብ ካልተከበረ፣ በደቡብ ሱዳን ሰላም እንዳይወርድ ባከላከለው ወገን ላይ ርምጃ እንደሚወስድ አደራዳሪው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ኢጋድ ዛቻ አሰምቶ ነበር። ሆኖም፣ የጊዜው ገደብም አልተከበረም፣ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ዩጋንዳ እና ሶማልያ የሚጠቃለሉበት ኢጋድ እንደዛተው ጠንካራ ማዕቀብ በመጣል ፈንታ እንደገና ጊዜውን እአአ እስከ ጥቅምት 16፣ 2014 ዓም ድረስ አራዝሞላቸዋል። ይህ፣ ተቀናቃኞቹ ወገኖች ልዩነታቸውን ለማስወገድ፣ በተለይም ፣ ወደፊት በሀገሪቱ እንዲቋቋም በተስማሙበት የሽግግሩ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ውስጥ አዲስ የሚፈጠረው አንድ ያማፅያኑ ተወካይ የሚይዘው የጠቅላይ ሚንስትርነት ቦታ ምን ያህል ሥልጣን ይኖረዋል በሚል ለተነሳው አካራካሪ ጥያቄ መልስ ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ እንዲያፈላልጉ ዕድሉን እንደሚሰጣቸው ኢጋድ ተስፋ አድርጓል።

የመጨረሻው የጊዜ ገደብ ያልተከበረበት ድርጊት ካላንዳች ርምጃ መታለፉ ለደቡብ ሱዳን እርቀ ሰላም ለማውረድ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር በሚመሩት መንግሥት እና በተቀናቃኛቸው ያማፅያኑ መሪ ሪየክ ማቸር መካከል የሚካሄደውን ድርድር እአአ ከግንቦት 2010 ዓም ወዲህ በኢትዮጵያ በማስተናገድ ላይ የሚገኙት የኢጋድ አባል ሀገራት ምን ያህል አቅም አልባ መሆናቸውን ያሳየ ነው። አደራዳሪው ኢጋድ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች ውጊያ አቁመው የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲያቋቁሙ ብዙ ጊዜ የመጨረሻ የጊዜ ገደብ ማሳርፉ እና ገደቡ በተደጋጋሚ ሳይከበር ሲቀር አዲስ ዕድል መስጠቱ የሚታወስ ነው። እና ይህ ሲታሰብ ከስድስት ቀናት በኋላ በባህር ዳር የሚቀጥለው ድርድር አዎንታዊ ውጤት የማስገኘቱ ተስፋ በጣም ንዑስ መሆኑን ውዝግብ በሚታይባቸው ሀገራት ሰላም እና ልማት እንዲዳብር የሚሰራው በምሕፃሩ ቢክ በመባል በሚታወቀው የቦኑ ዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ የደቡብ ሱዳን ጉዳዮች አስተባባሪ ቮልፍ ክርስቲያን ፔስ ለዶይቸ ቬለ በሰጡት አስተያየት አስታውቀዋል።

« በአሁኑ ጊዜ የሰላሙ ሂደት በርግጥ ተጀምሮዋል ብሎ መናገር አዳጋች ይመስለኛል። ገሀዱ፣ የፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር መንግሥት እና ሪየክ ማቸር የሚመሩት ያማፅያን ቡድን ተወካዮች በዓለም አቀፍ ሸምጋዮች አደራዳሪነት መደረግ አለበት የሚሉት የሰላም ውይይት በየትኛው መድረክ እንደሚካሄድ እና የትኞቹ ቅድመ ግዴታዎችም መሟላት እንዳለባቸው ብቻ ነው የተነጋገሩት፣ ስለዚህ ሀቀኛው የሰላም ድርድር ገና አልተጀመረም። »

በ2011 ዓም ነፃ መንግሥት ባቋቋመችው ደቡብ ሱዳን ውስጥ የርስ በርሱ ጦርነት የተጀመረው በ2013 ዓም መጨረሻ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር የቀድሞው ምክትላቸው ሪየክ ማቸርን መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ አሢረዋል በሚል በወቀሱበት እና ማቸርም ያኔ ወቀሳውን በማስተባበል፣ እንዲያውም፣ ኪር በሀገሪቱ አምባገነኑን አገዛዝ ለማቋቋም እየሰሩ ናቸውን ባሉበት ጊዜ ነበር። ከታህሳስ 2013 ዓም ወዲህ በቀጠለው ውዝግብ ከ1,000 የሚበልጡ ደቡብ ሱዳናውያን ሲገደሉ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። የመብት ተሟጋች ሁለቱም ተቀናቃኝ ወገኖች በሕዝባቸው ላይ ከባድ የጦር ወንጀል ፈጸመዋል በሚል ከሰዋል። እንደሚታየው፣ የኃይል ተግባር ሰለባ እንዳይሆኑ የሰጉ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳን ዜጎች አሁንም በተጨናነቁ የተመድ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። ይህም ቢሆን ግን ኢጋድ የወሰደው ርምጃ የለም፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በወቅቱ ለደቡብ ሱዳን ውዝግብ ያን ያህል ትኩረት እንዳልሰጠው ፔስ ገልጸዋል።

« ኢጋድ አቅም አልባ ድርጅት ነው። በተፋላሚዎቹ ወገኖች ላይ የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ሽያጭ ቢጥል ኖሮ አንድ ጠንካራ ምልክት ማስተላለፍ በቻለ ነበር። ግን ይህን አላደረገም። የጦር መሳሪያ ዝውውሩን የመቆጣጠር ተሞክሮም የለውም። እንደሚታየው፣ የደቡብ ሱዳን መንግሥት የጦር መሳሪያውን በዩጋንዳ፣ አልፎ አልፎም በኬንያ በኩል ያስገባል። ለነገሩ እነዚህ ሁለት ሀገራት ይህንኑ የጦር መሳሪያ አቅርቦት ማከላከል ነበረባቸው። ዓማፅያኑ የጦር መሳሪያቸውን ከየት እንደሚያገኙ በወቅቱ ግልጽ አይደለም። በዚያም ሆነ በዚህ ግን እስካሁ በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች ላይ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ማዕቀብ ለመጣል ሁነኛ ጥረት አልተደረገም። »

በሌሎች ተመሳሳይ ውዝግቦች በታዩባቸው አካባቢዎች ያረፈው ዓይነት የጦር መሳሪያ ማዕቀብ ይጣላል ብሎ ማሰብም፣ እንደ ፔስ አስተያየት፣ በወቅቱ አዳጋች ነው።

በተለይ ኬንያና ዩጋንዳ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን ይደግፋሉ የሚሉት ዓማፅያን ኢጋድ በደቡብ ሱዳን የሰላም ሂደት ገለልተኛ አይደለም የሚል ወቀሳ በመሰንዘር ፣ ድርድሩ ወደ ኬንያ እንዲዛወር መጠየቃቸው ተሰምቶዋል።

የሰላሙ ድርድር ጠቅላይ ሚንስትሩ በሚኖረው ሥልጣን እና ፕሬዚደንቱም የሀገሪቱ እና የመንግሥቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው ይቀጥላሉ አይቀጥሉም በሚሉት ጥያቄዎች ሰበብ የከሸፈበት ድርጊት ችግሩ የሥልጣን ሽኩቻ መሆኑን በግልጽ ማሳየቱን የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ጥናት ተቋም ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ኒሂያል ቲትማመር እንደሚከተለው አስረድተዋል።፣

« ተፋላሚዎቹ ወገኖች ለሕዝቡ ወሳኝ በሆኑት ዋነኞቹ የፖለቲካ ጥያቄዎች፣ ለምሳሌ፣ በሕገ መንግሥቱ፣ በፀጥታ ኃይሉ እና በአስተዳደራዊ አሰራሩ ላይ ማሻሻያ ይደረግ በሚሉት ጉዳዮች ላይ የተስማሙ ይመስላል። ስለዚህ ፕሬዚደንት ሳልቫ ኪር እና ተቀናቃኛቸው ሪየክ ማቸር ውዝግቡን ለማብቃት ሲሉ በወቅቱ በመካከላቸው ትልቁን ልዩነት ለፈጠረው የሥልጣን መጋራቱ ጉዳይ መፍትሔ ማግኘት ይኖርባቸዋል። »

በተለያዩት ጎሣዎች መካከል ያለው የጥላቻ እና የአለመተማመን መንፈሥ በጣም ስር የሰደደ በመሆኑ በሥልጣን ክፍፍሉ ሰበብ የተፈጠረው ውዝግብ በዓለም አቀፍ ሽምግልና ወይም ዲፕሎማሲያዊውን ግፊት በማሳረፍ ወይም ማዕቀብ በመጣል ማስወገድ እንደማይቻል ቲትማመር ገልጸዋል።

« ጥላቻን የማስፋፋቱ ፕሮፓጋንዳ በውዝግቡ የሚፋለሙት የተለያዩት ቡድኖች ከግለሰብ ጥቅም ይልቅ የሀገርን ጥቅም ማስቀደም የሚለውን ዋነኛውን ጉዳይ እንዲዘነጉት አድርጓቸዋል። »

ቲትማመር የውጭ ሸምጋዮች ይህንኑ ጥላቻ እና አለመተማመን በማጥፋቱ ረገድ ሊረዱ ይችላሉ ባይ ናቸው። በመሆኑም፣ ኢጋድ የጀመረው የማደራደሩ ሂደት የመተማመኑ መንፈሥ እንደገና ሊወርድ የሚችልበትን ጥረት ጎን ለጎን ማነቃቃት ይኖርበታል። እአአ በ90ኛዎቹ ዓመታት በተለያዩት የደቡብ ሱዳን ጎሣዎች መካከል ከተካሄደው ደም አፋሳሽ ውዝግብ በኋላ ውጤት ያስገኘ የእርቀ ሰላም መርሀግብር ተዘጋጅቶ እንደነበር ቲትማመር አስታውሰዋል።

አርያም ተክሌ
አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic