እንግሊዝና የቁጠባ እቅዷ | ዓለም | DW | 21.10.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

እንግሊዝና የቁጠባ እቅዷ

የገንዘብ ሚኒስትሩ ጆርጅ ኦስቦርነ ይህን ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት ወዲህ ትልቁ የተባለውን የበጀት ቅነሳና የቁጠባ እቅድ ይፋ ሲያደርጉ ከተቃዋሚዎች የምክር ቤት አባላት ጠንካራ ነቀፌታ ገጥሟቸዋል።

default

የገንዘብ ሚኒስትሩ ጆርጅ ኦስቦርን

እቅዱ በሚቀጥሉት አራት ዓመታት በአጠቃላይ የ81 ቢሊዮን ፓውንድ የወጪ ቅነሳ እንዲደረግ ያለመ ነው። መሳይ መኮንን የዶቸቬሌ የእንግሊዘኛ ክፍል ባልደረባ ኦሊ ባራት ያጠናቀረውን እንዲህ ያቀርበዋል።

የወጪ ቁጠባ እቅዱ ብሪታኒያን በተሻለ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ለማስቀመጥ ነው ይላሉ የእንግሊዝ የገንዘብ ሚኒስትር ጆርጅ ኦስቦርነ። ለዓመታት ሲታሽ የከረመ፤ ቢሆንም በመጨረሻ ግን ተግባራዊ ሊሆን ጊዜው ደረሰም ብለዋል ሚኒስትሩ። እቅዱ ላይ ትላንት የብሪታኒያ ምክር ቤት የሞቀ ውይይትና ክርክር አድርጓል። ዋንኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ሌበር የህዝቡን የወደፊት ህይወት አደጋ ላይ የሚጥል ሲል ጠንከር ያለ ተቃውሞ አንስቷል። እቅዱ ተግባራዊ ሲሆን ግማሽ ሚሊዮን የሚደርስ ብሪታኒያዊ ስራውን ያጣል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ግን ሁነኛ ለውጥ የሚሳይ እቅድ እንደሆነ፤ ብሪታኒያን ከኢኮኖሚ ቀውስ ሊታደጋት እንደሚችል ይከራከራሉ።

ድምጽ

«ዛሬ ብሪታኒያ ከቀውስ አፋፍ ተመልሳለች። ላለፉት አስርተ ዓመታት ከእዳና ኪሳራ ጋር ተፋጠን ቆይተናል። ይህን አልፈን ለአራት ዓመት የሚሆን እቅድ በማቅረብ ዳግም ልምንገነባበት ቀን ነው ዛሬ። የህዝብ አገልግሎቶችና የሀገሪቱ አቅም አስተማማኝ በሆነና ለረጅም ጊዜ በሚቆይ ውጤት ላይ የሚስቀምጥ እቅድ ነው።»

በወጪ ቁጠባ እቅዱ መሰረት የመንግስት መስሪያ ቤቶች ይታጠፋሉ። ብሪታኒያ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የምታወጣው የዕርዳታ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ይደረጋል። በአንጻሩ ለብሄራዊ የጤና አገልግሎት የሚውለው ወጪ በመጠኑ ይጨምራል። ለትምህርቤቶች የሚወጣውም እንዲሁ። ሆኖም ከየመስራቤቱ የሚቀነሰው በጀት በአማካይ ሲሰላ 20 በመቶ ይደርሳል። የበጀት ቅነሳው የህዝብ አገልግሎቶችን የሚሽመደምድ ከመሆኑም በላይ ተጨማሪ 500 ሺህ ብሪታናውያን ስራ አጥ ይሆናሉ። የገንዘብ ሚኒስትሩ የሚሳዝን ግን የማይቀር ይሉታል።

ድምጽ

«ሀገሪቱ ገንዘብ በከፍተኛ ሁኔታ እያጠራት ባለችበት በዚህን ጊዜ የምንተወው አይሆንም»

እቅዱ የብሪታኒያን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን ክፉኛ የሚጎዳ ነው ተብሏል። መስሪያ ቤቱ የ24 በመቶ የበጀት ቅነሳ ይገጥመዋል። ሌላው በወጪ ቅነሳ እቅዱ የተካተተው የጡረታ መውጪያ እድሜ እንዲራዘም የሚያደርገው ሀሳብ ነው። ከተቀመጠለት ጊዜ ስድስት ዓመት ቀድሞ ተግባራዊ የሚሆነው የጡረታ እድሜን የማራዘም እቅድ በ2020 ጣሪያው ወደ 66 ዓመት ከፍ አንዲል ያደርጋል። በምክር ቤት የተቃዋሚው ወገን አባል አለን ጆንሰን ጥንቃቄ የጎደለው፤ የብሪታኒያን ህዝብ ለአዳጋ የሚያጋልጥ እቅድ ብለውታል።

ድምጽ

«ዛሬ የማይታዩ ቁጥሮችና ወረቀቶች የህዝቡን ዕድል እንዲወስኑ የተፈረደበት ቀን ነው። የህዘቡ የስራ ዋስትና፤ አገልግሎቶች እንዲሁም ስለወደፊት ያለው እይታ የተጋረደበት ቀን ነው።»

በስልጣን ላይ ያለው ጥምሩ መንግስት የወጪ ለቅነሳው ሰበብ ምክንያት ያደረገው የቀድሞውን የጎርደን ብራውንን መንግስት ነው። ተገቢ ያልሆኑ ወጪዎችን ሲስተናግድ የነበረ፤ ብሪታኒያን ለኪሳራ የዳረገ ፖሊሲ ሲያራምድ የቆየ በመሆኑ አፋጣኝ እርምጃ ካልተወሰደ ከማንወጣበት አደጋ ውስጥ መግባታችን የማይቀር ነው ሲል ጥምሩ መንግስት አስታውቋል። የእንግሊዝ ኢኮኖሚ አገግሞ ባለሀብቶች እምነት እንዲጥሉብል የሚደርግ እቅድ ነውም ብሎታል የቁጠባ እቅዱን።በብሪታኒያ የፖሊሲ ልውውጥ ማዕከል ከፍተኛ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር አንድሪው ሊልኮ ብሪታኒያ ካለባት የኪሳራ ክምር አንጻር እቅዱ አስፈላጊ ነው ይላሉ።

ድምጽ

«ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ የ10 በመቶ የበጀት ጉድለት መታየቱ ትልቅ አደጋ ነው። ስሜት በሚሰጥ መልኩ ለማስቀመጥ ያህል፤ በአውሮፓ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ከ3 በመቶ በላይ የበጀት ክፍተት ካለ፤ ሀገራቱ የተስማሙበት የውል ገደብ ስምምነቶች አሉ። ብሪታኒያ ከተገመተው 3 እጥፍ የበለጠ ጉድለት ውስጥ ኢኮኖሚዋ ይገኛል። ይህ እርምጃም ተወስዶ ከሚከሰተው ጥፋት መውጣት ይገባል።»

በሚቀጥሉት አራት ዓመታት ውስጥ ይቆጠባል ተብሎ የታቀደው የ81 ቢሊዮን ፓውንድ እቅድ የብሪታኒያን የበጀት ጉድለት በግማሽ ይሞላል ነው የተባለው። ጥምሩ መንግስት እቅዱ የብሪታኒያን ኢኮኖሚ ጤናማ ያደርገዋል ሲል ተስፋ አድርጓል። ተቃዋሚዎች ደግሞ ውጤቱ ተቃራኒው ይሆናል፤ ብሪታኒያንንም ወደ ኢኮኖሚ ቀውስ ዳግም ይከታታል ብለው እቅዱን እያጣጣሉት ነው።

መሳይ መኮንን
አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic