እንደወጡ የቀሩት የናይጄሪያ ልጆች | አፍሪቃ | DW | 11.07.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

እንደወጡ የቀሩት የናይጄሪያ ልጆች

በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ በቦርኖ ግዛት ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠዋል። አካባቢው በአክራሪው ደፈጣ ተዋጊ ቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን የሰርጎ ገብ ጥቃቶች የደህንነት ስጋት የነበረበት በመሆኑ የተዘጋው ትምህርት ቤት የተከፈተው ለማጠቃለያ ፈተና ነበር። ተማሪዎቹም ፈተናው እንዲያመልጣቸው አልፈለጉም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:48
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:48 ደቂቃ

እንደወጡ የቀሩት የናይጄሪያ ልጆች

ለትምህርት ፈተና የተቀመጡት ተማሪዎች ድንገት በቦኮ ሃራም የጭነት መኪናዎች ተጭነው ወደማያውቁት ጫካ ተወሰዱ። ይህ ከሆነ ከአመት በላይ አለፈው። ከ276ቱ እንስት ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት ከታጣቂ ቡድኑ ማምለጣቸው ቢነገርም አሁንም ስንት እንደቀሩ አይታወቅም። ከ200 በላይ ተማሪዎች እንደሆኑ ይገመታል።

የተማሪዎቹ መታገት በወላጆቻቸው፤ የቺቦክ ነዋሪዎች እና ናይጄሪያውያን ዘንድ መጀመሪያ ሐዘን፤ ቀጥሎ ደግሞ ቁጣ መቀስቀሱ አልቀረም። በሳምንቱ ‘ልጆቻችንን መልሳችሁ አምጡልን’ ("Bring back our girls") የተሰኘ ዘመቻ ተጀመረ። የዘመቻው ዋንኛ አላማ በቦኮ ሃራም የታገቱትን ተማሪዎች ማስታወስ እና የናይጄሪያ መንግስት ላይ ጫና ማሳደር ነበር። በማህበራዊ ድረ-ገጾች የተጀመረው ዘመቻ በናይጄሪያ ብቻ ሳይሆን በመላው ዓለም ደጋፊዎችን ለማፍራት ጊዜ አልወሰደበትም። ፓኪስታናዊቷ የሴቶች መብት አቀንቃኝ ማላላ ይሱፍ ዛይ እና የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማን የመሳሰሉ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ከዘመቻው ጎን ቆሙ። ይህ ሁሉ ሲሆን የተሰናባቹ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን መንግስት ይህ ነው የሚባል ርምጃ መውሰድ አልቻለም። የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን የዘመቻውን አስተባባሪዎች አግኝተው ለማነጋገር እንኳ አልፈቀዱም።

ከአንድ አመት በላይ ልጆቻችንን መልሱልን የሚል መፈክር አንግበው በቦኮ ሐራም ለታገቱ ታዳጊ ተማሪዎች ሲጮሁ የከረሙት የዘመቻው አስተባባሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ከአዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል። የዘመቻው አስተባባሪዎች የናይጄሪያ መንግስት የታገቱትን ከ200 በላይ ሴቶች ለማስለቀቅ የታየበትን ቸልተኝነትም ነቅፈዋል። የዘመቻው መሪ ኦቢ ኤዝክዌዚሊ የናይጄሪያ መንግስት የታገቱትን ተማሪዎች ለማስፈታት ጊዜው አሁን ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

«የተከበሩ ፕሬዝዳንት የመጀመሪያ ጥያቄያችን የታገቱት የቺቦክ ልጆች ተቀባይነት ሊኖረው ከሚችል ጊዜ በላይ በገዳዮች እጅ ቆይተዋል። አሁን መንግስታችን ልጆቻችንን መልሶ የሚያመጣበት ጊዜ ነው። ምንም ጊዜ የለም። የተከበሩ ፕሬዝዳንት የቺቦክ ሴቶች ልጆቻችንን በፍጥነት እንዲያስለቅቁልን እንጠይቃለን።»

የቦኮ ሃራም ታጣቂ ቡድን ከምዕራባውያን ጋር የሚደረጉ ፖለቲካዊም ይሁን ማህበራዊ ግንኙነቶችን ይቃወማል። ይህ ተቃውሞ ሱሪና ቲሸርት ከመልበስ ጀምሮ ምርጫን እና ዘመናዊ ትምህርትን ሁሉ ያጠቃልላል። ቡድኑ ናይጄሪያ በእስልምና ተከታይ ፕሬዝዳንት ብትመራም እንኳ በኢ-አማኒ እንደምትተዳደር ይቆጥራል። ቦኮ ሃራምን በጎርጎሪዮሣዊው 2002 የመሰረተው መሐመድ ይሱፍ ከሰባት አመታት በኋላ በፖሊስ ጣቢያ በነበረበት ተገድሏል። ታጣቂ ቡድን እስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሰርጎ ገብ ጥቃት ከጀመረ ሰባት አመታት ተቆጠሩ።

በ2009 ዓ.ም ቦኮ ሃራም በማይዱግሪ ከተማ የፖሊስ ጣቢያ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ በከተማዋ ጎዳናዎች ከጸጥታ ሃይሎች ጋር ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ አደረገ። በርካታ ደጋፊዎቹ እና የቡድኑ መስራች ተገደሉ። የናይጄሪያ መንግሥት ገና ከጅማሮው ቦኮ ሃራም አለቀለት ሲል አስታወቀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከአፍሪቃ በኢኮኖሚና የህዝብ ቁጥር ቀዳሚውን ደረጃ የያዘችው ናይጄሪያ እንደታመሰች ትገኛለች። የቦንብ ፍንዳታዎች፤ግድያ እና ዘረፋ የቡድኑ መለያዎች ናቸው። ቦኮ ሃራም የካሜሮን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤትን ጨምሮ ከ2ሺ በላይ ሴቶች ማገቱን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው ዘገባ ያትታል።

አዲሱ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የቦኮ ሐራም ግድያና ጥቃቶች አላባሩም። ይልቁንስ በኢራቅ እና ሶርያ የሚንቀሳቀሰውና ራሱን «እስላማዊ መንግስት» ብሎ ለሚጠራው የአይሲስ ታጣቂ ቡድን ታማኝነቱን የገለጠው ቦኮ ሐራም ለመጀመሪያ ጊዜ የናይጄሪያ ወታደርን በስለት ሲቀላ የሚታይበትን ቪዲዮ ይፋ አድርጓል።

ፕሬዝዳንት ሙሐመዱ ቡሐሪ የዘመቻው አስተባባሪዎች የቺቦክ ሴቶች ልጆች እንዳይረሱ ያደረጉትን ጥረት አድንቀው መንግሥታቸው ከጎረቤት አገሮች ጋር በመተባበር የሰርጎ ገብ ጥቃቱን ለማስቆም እየሠራ መሆኑን ተናግረዋል። ይሁንና አሁንም በቦኮ ሐራም እጅ የሚገኙትን ተማሪዎች ለማስለቀቅ በተለየ የሚደረግ ጥረት ስለመኖሩ የተናገሩት ነገር የለም።
ሐሳባቸውን የዘመቻው አስተባባሪዎች በኦቢ ኤዜክዌሲሊ በኩል ባስተላለፉት መልእክት ግን የናይጄሪያ መንግስት የቺቦክ ሴት ልጆችን ለማስለቀቅ የሚያደርገው ጥረት አሊያም የሚያሳየው ቸልተኝነት ከፍ ያለ ትርጉም እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

«የቺቦክ ሴት ልጆችን መታደግ መንግሥት ለእያንዳንዱ ናይጄሪያዊ ነፍስ ደህንነት እና ክብር ያለውን ዋጋ የሚያሳይበትና ጠንካራ መልእክት የሚያስተላልፍበት ይሆናል። በሁለተኛ ደረጃ እንደ ቺቦክ ማህበረሰብ ተከታታይና የተደራጀ የምላሽ አሰጣጥ እንዲኖር እንጠይቃለን። የቺቦክ ሴት ልጆች ወላጆች ልጆቻቸው በታገቱበት ያለፉት 450 ቀናት የተደራጀ ምላሽ አልተሰጣቸውም። »

የዘመቻው አስተባባሪዎች ከፕሬዝዳንቱ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የቦኮ ሐራም ታጣቂ ቡድን የያዛቸውን ከ200 በላይ የቺቦክ ሴት ልጆች ለመልቀቅ ከናይጄሪያ መንግስት ጋር መደራደር እንደሚፈልግ ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ታጣቂ ቡድኑ በበኩሉ በናይጄሪያ መንግሥት በእስር ላይ የሚገኙ ወታደራዊ መሪዎች እንዲለቀቁለት መጠየቁን ተዘግቧል። አሶሼትድ ፕሬስ ያነጋገራቸውና ቦኮ ሐራም ከናይጄሪያ መንግሥት ጋር በሚያደርገው ድርድር ተሳታፊ ናቸው የተባሉ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ጥያቄው ለቀድሞው ፕሬዝዳንት ጉድ ላክ ጆናታን ቀርቦ እንደነበር አስታውሰው ታጣቂ ቡድኑ የቺቦክ ልጃገረዶችን ሲለቅ በምትኩ በእስር ላይ የሚገኙ 16 አባላቱን እንዲፈቱለት ይፈልጋል ብለዋል።ላለፈው አንድ አመት በድርድሩ ተሳታፊ የነበሩ ፍሬድ ኢኖ የተባሉ ፖለቲከኛ በበኩላቸው ሌላ የእድል መስኮት ተከፈተ በማለት መልካም አጋጣሚ መምጣቱን ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

የናይጄሪያ መንግስት ከቦኮ ሐራም ታጣቂ ቡድን ጋር ተደጋጋሚ ድርድሮች ቢያካሂድም በደህንነት ተቋማቱ የተከፋፈለ አቋምና ጣልቃ ገብነት አንዳቸውም ፍሬ ማፍራት አልቻሉም። የቺቦክ ሴት ህጻናትን ለማስለቀቅ የሚደረገውን ጥረት የሚያስተባብሩትም ይሁኑ የቦኮ ሐራምን ርምጃዎች በጥንቃቄ የሚከታተሉ የጸጥታ ተንታኞች የናይጄሪያ መንግሥት የሳይንስ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ሳሉ የታገቱትን ልጃገረዶች ለማስለቀቅ ዘገምተኛ ነው ሲሉ ይተቻሉ። የዘመቻው አስተባባሪዎች የናይጄሪያን የፕሬዝዳንት መንበረ-ስልጣን ከተቆናጠጡ አምስተኛ ሳምንት ለሆናቸው ሙሐሙዱ ቡሐሪ ያቀረቡት ጥያቄም ይህንንው የሚያጎላ ነበር።

«የተከበሩ ፕሬዝዳንት በሰሜን ምስራቅ ናይጄሪያ የተከሰቱትን ጉዳዮች በተለይም ከቺቦክ የታገቱትን ሴት ተማሪዎች ጉዳይ የሚመረምር አንድ ኮሚቴ ሊቋቋም ይገባል። የፕሬዝዳንቱ እውነት አጣሪ ኮሚቴ በቺቦክ ሴት ልጆች ላይ ዘገባ ይፋ እንዲያደርግ እንጠይቃለን። ይህ ምሥጢሩን ባይፈታውም ልጆቹ ከታገቱ በኋላ የተፈጠሩ አለመግባባቶችንና ጭቅጭቆችን በማቅለል የቺቦክ ሴት ልጆችን ለመታደግ መንገድ ይከፍታል።»

በናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሄዶ ሌላ ፕሬዚዳንት ተተክቷል፤ ቦኮ ሃራም ግን ዛሬም ልጃገረዶቹን እንዳገተ ይገኛል። የእናቶች እና የመብት ተሟጋቾች ድምጽም «ልጆቻችንን መልሳችሁ አምጡልን» እያለ ደጋግሞ ያስተጋባል።

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic