እነ አህመዲን ጀበል የይቅርታ ደብዳቤ«አንፈርምም»አሉ | ኢትዮጵያ | DW | 10.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

እነ አህመዲን ጀበል የይቅርታ ደብዳቤ«አንፈርምም»አሉ

በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አራት አባላት የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ አንፈርምም አሉ። ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ፖለቲከኞቹ አንዱዓለም አራጌ እና ክንፈሚካኤል አበበ ለሁለተኛ ጊዜ "የግንቦት ሰባት አባል ነበርኩኝ" ብለው እንዲፈርሙ ቢጠየቁም አለመስማማታቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።

በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አራት አባላት የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ እንዲፈርሙ ተጠየቁ። ትናንት የካቲት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. አራቱ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች «ይቅርታ ስለመጠየቅ» የሚል ደብዳቤ እንደቀረበላቸው የኡስታዝ አህመዲን ወንድም አቶ መሐመድ አሚን ጀበል ተናግረዋል። በዛሬው ዕለት ወንድማቸውን ለመጠየቅ ወደ ማረሚያ ቤት አምርተው እንደነበር የገለጹት አቶ መሐመድ አሚን ደብዳቤው «በጥፋታችን መሰረት ተፈርዶብን እስር ላይ ስላለን ተጸጽተን ጥፋታችንን አምነን ይቅርታ ጠይቀናል፤ ፈርመናል» የሚል ይዘት እንዳለው አስረድተዋል።

ከሰባት እስከ 22 አመታት እስር ተበይኖባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት አራቱ የኮሚቴው አባላት፤ አሕመዲን ጀበል፣ ካሊድ ኢብራሒም፣ አሕመድ ሙስጠፋ እና መሐመድ አባተ፤ «ያጠፋነው ነገር የለም» በማለት ሳይፈርሙ ቀርተዋል። «ለ2006 ቀናት መንግሥት ያለ ጥፋታችን አስሮናል» ሲሉ ተቃውሟቸውን የገለጹት እነ አሕመዲን «የምንጠይቀውም ይቅርታ የለም» ማለታቸውን አቶ መሐመድ አሚን አስረድተዋል።

ከአራቱ የሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በተጨማሪ በሌሎች ጉዳዮች ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙ ሌሎች 55 ሰዎች የይቅርታ መጠየቂያ ደብዳቤ እንዲፈርሙ በማረሚያ ቤት አስተዳዳሪዎች እንደቀረበላቸው መስማታቸውንም መሐመድ አሚን ጀበል ተናግረዋል።

ተመሳሳይ ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም ፖለቲከኞቹ አቶ አንዱዓለም አራጌ እና አቶ ክንፈሚካኤል ደበበ (አበበ ቀስቶ)  ይገኙበታል። እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌ እና ክንፈሚካኤል ደበበ በኢትዮጵያ መንግሥት ሽብርተኛ ተብሎ የተፈረጀው የግንቦት ሰባት አባል ነበርኩኝ ብለው እንዲፈርሙ ሁለት ጊዜ መጠየቃቸውን የእስክንድር ነጋ ባለቤት ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት 746 እስረኞችን በይቅርታ እፈታለሁ ካለ በኋላ እነ እስክንድር ወደ ቢሮ መጠራታቸውን የገለጹት ወ/ሮ ሰርካለም «የግንቦት ሰባት አባል ነበርኩኝ» የሚል የይቅርታ ሰነድ እንዲፈርሙ መጠየቃቸውን ገልጸዋል። እስክንድር፣ አንዱዓለም እና ክንፈሚካኤል የቀረበውን ሰነድ አንፈርምም ማለታቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

"ለመጀመሪያ ጊዜ ጠይቀዋቸው እምቢ ካሏቸው በኋላ በድጋሚ በዛሬው ዕለት እንዳነጋገሯቸው ከዚያው አካባቢ ከምንጮች ማወቅ ችያለሁ" ያሉት ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲል ጥያቄውን በድጋሚ ውድቅ መደረጉን አክለው ገልጠዋል።  የኢትዮጵያ መንግሥት አቅርቦታል የተባለው ጥያቄ ለጋዜጠኞች መብት ከሚሟጋተው ሲፒጄ እና እና የፀሐፊያን ማኅበር ከሆነው ፔን ኢንተርናሽናል ትችት ገጥሞታል።

የኢትዮጵያ መንግሥት አቅርቦታል የተባለውን ጥያቄ «አሳዛኝ» ያሉት የሲፒጄ የፕሮግራም አስተባባሪ አንጌላ ኩይንታል «የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ እስክንድር ነጋን ይፍቱ» ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። አሜሪካዊው ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቀድሞዋ የአሜሪካ አምባሳደር ሳማንታ ፓወርም የኢትዮጵያ መንግሥት እስክንድርን እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።

እሸቴ በቀለ

ልደት አበበ