እቴጌ ጣይቱ ብጡል: ኢትዮጵያዊቷ ጀግና | አፍሪቃዊ ሥረ-መሠረት | DW | 06.05.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃዊ ሥረ-መሠረት

እቴጌ ጣይቱ ብጡል: ኢትዮጵያዊቷ ጀግና

የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያ ላይ ዐይናቸውን በጣሉበት ጊዜ እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከባለቤታቸው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጎን በመቆም በንጉሠ ነገሥቱ ላይ የተጀመሩ ሴራዎችን እና ጦርነቶችን የተቃወሙ ጀግና ሴት ናቸው። በአድዋ ጦርነት ከነበሩ የጦር አዛዦችም አንዷ ነበሩ።

እቴጌ ጣይቱ ብጡል ማን ነበሩ?
እቴጌ ጣይቱ ብጡል ከባለቤታቸው ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ ጎን በመሆን ኢትዮጵያን ለ24 ዓመታት ያስተዳደሩ ጀግና ሴት ነበሩ።  የጣልያን ቅኝ ገዥ ኃይሎችን በመዋጋት እና በነበራቸው የፖለቲካ ተሳትፎም ይታወሳሉ። ጣይቱ የኢትዮጵያን መዲና አዲስ አበባ ብለው የሰየሙም ሰው ናቸው።

ጣይቱ እቴጌ ጣይቱ ከመባላቸው በፊት ማን ነበሩ? 
ጣይቱ ከአባታቸው ከደጅአዝማች ብጡል እና ከእናታቸው ወይዘሮ ዮብ ዳር እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ 1832 ዓ ም ገደማ እንደተወለዱ ይነገራል። የታሪክ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ከጣና ሀይቅ ብዙም ሳይርቅ የሚገኘው ደብረ ታቦር ከተማ ነው የተወለዱት። እሳቸውም በ 10 አመታቸው ገደማ ለመጀመሪያ ጊዜ ተድረዋል። በወቅቱ  እንዲህ አይነት ጋብቻ የተለመደ ነበር። አራት ጊዜ አግብተው የፈቱት ጣይቱ በመጨረሻ የሸዋ ንጉስ ከነበሩት እና ኋላም ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከተባሉት ንጉሠ ነገሥት ጋር ትዳር መስርተዋል። ጣይቱ ከምኒልክ ጋር ትዳር ከመመስራታቸው በፊትም ጥሩ ሀብት እንደነበራቸው ይታመናል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:49

እቴጌ ጣይቱ ብጡል: ኢትዮጵያዊቷ ጀግና

እቴጌ ጣይቱ እንዴት ኃይል ያላቸው ሰው ሆኑ?
የጣይቱ ብጡል እና የአፄ ምኒልክ ጋብቻ ጠንካራ የፖለቲካ ጥምረት ፈጥሯል። ጥንዶቹም ንጉሠ ነገሥት እና እቴጌ ተብለው ሲሰየሙ ከተለያዩ የአካባቢው ገዢዎች ጋር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ጥምረት በመፍጠር አልያም ወታደራዊ አቅም በመጠቀም የበለጠ ግዛታቸውን አስፋፍተዋል።  
እቴጌ ጣይቱ የዳግማዊ አፄ ምኒልክ ባለቤት ብቻ አልነበሩም። በተለያዩ የፖለቲካ ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ወታደራዊ ውሳኔዎች ላይ ተዕፅኖ ፈጣሪ  ሴት ሆነው አልፈዋል። የታሪክ ምሁሮች እንደሚሉት ጣይቱ ከምኒልክ እኩል ውሳኔዎችን ይወስኑ እና በሳል ሴት እንደነበሩ ይነገራል። 
ጣይቱ ብጡል ዝነኛ የሆኑት በምንድን ነው? 
ጣይቱ ከጣሊያን ጋር ከተደረጉ ስምምነቶች መካከል ኢትዮጵያን  ቅኝ ተገዢ ሊያስደርጋት የሚችለውን የውጫሌውን ስምምነት ውል አንቀፅ 17 ውድቅ በማድረግ  ይታወቃሉ። መቀሌን ተቆጣጥረው የነበሩትንም የጣሊያን ወታደሮች ለማሸነፍ እንዲቻል ጣይቱ ባቀረቡት ሀሳብ ይታወቃሉ። በዚህም መሠረት ጣሊያኖች የሚጠቀሙበትን የውኃ ምንጭ በኃይል በመቆጣጠር ከመቀሌ እንዲወጡ ለማስደረግ ተችሏል። ጣይቱ ብጡል ጣሊያኖች በተሸነፉበት እና በድል በተጠናቀቀው የአድዋ ጦርነት በነበራቸው ሚናም ይታወቃሉ። እሳቸውም ኢትዮጵያን ቅኝ ግዛት ለማድረግ የሞከረውን የጣሊያን ጦር ለመዋጋት በስራቸው 5,000 እግረኛ እና 600 ፈረሰኞችን አሰልፈው ነበር።
ጣይቱ ብጡል በጊዜያቸው ከነበሩ ሴቶች የተለዩ ነበሩ?
ምንም እንኳን የጣይቱን ያህል ባይሆንም ኢትዮጵያ ብዙ ጠንካራ ሴቶች ነበሯት። ብዙዎች መሣሪያ አንስተው ባይዋጉም የመኳንንት ሚስቶችን ጨምሮ ብዙ ሴቶች የጎላ ሚና ተጫውተዋል። ምግብ በማብሰል ፣ በማፅዳት እና ለሰራዊቱ ጉልበት ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋፅዎ አበርክተዋል። ጣይቱ እንዳደረጉት አይነት ወታደራዊ ትዛዝ ማስተላለፍ ግን ለሴቶች ብዙም ያልተለመደ ነበር።  ጣይቱ  ማንበብ እና መፃፍ ይችሉ እንደነበር ይነገራል። ከዚህም ሌላ የሰንጠረሽ ጨዋታ (ቼዝ) መጫወት እንደሚወዱ እና በገና እንደሚደረድሩ እና ሙዚቃ እንደሚወዱ ይነገራል። 
ከምኒሊክ ሞት በኋላ ምን ተፈጠረ?
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ እጎአ 1909 ክፉኛ ሲታመሙ እቴጌ ጣይቱ አብዛኛውን ሀገሪቱን የመምራት ሚና ተጫውተዋል።  ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን ተቀናቃኞቻቸው ጣይቱ ስልጣን እንዲለቁ ግፊት አድርገውባቸዋል። አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት ይህ የሆነው እቴጌይቱ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛ ስልጣን በመቆጣጠራቸው ነው።
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ 1906 ዓ/ም ሲሞቱም ጣይቱ ከዋናው ቤተመንግስት እንዲወጡ ተገደዋል። እሳቸውም በ 1910 ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ስለ እቴጌ ጣይቱ ምን አይነት ማስረጃዎች ይገኛሉ?
ስለ እርሳቸው በፅሁፍ እና በምስል የሚያስረዱ ሰነዶች ይገኛሉ። በኢትዮጵያ ቤተ መንግሥት የነበሩ ሰዎች ፣ የውጭ ዲፕሎማቶች ፣ የጣሊያን የጦር እስረኞች እና ከራሳቸው ከጣይቱ የተላኩ ደብዳቤዎች ሳይቀሩ የጣይቱን ማንነት በዝርዝር ይገልፃሉ። 
ለንጉሠ ነገሥቱ እና ለእቴጌ ጣይቱ ይሠሩ የነበሩት የስዊዘርላንድ መሐንዲስ አልፍሬድ ኢልግ ጥንዶቹን በቤተ መንግሥቱ ስለነበራቸው ህይወት ግንዛቤ የሚያስጨብጡ ፎቶግራፎች በሰነድ አኑረዋል።

ቪድዮውን ይመልከቱ። 02:07

እቴጌ ጣይቱ ብጡል: ኢትዮጵያዊቷ ጀግና

ይህ ዘገባ አፍሪካዊ ሥረ-መሠረት በሚል ከጌርዳ ሔንክል ተቋም ጋር በመተባበር የሚቀርብ ዝግጅት ነው። የዘገባው ሳይንሳዊ ምክር የተገኘው ከፕሮፌሰር ጉዳዬ ኮናቴ፣ ሊሊ ማፌላ Ph.D እና ፕሩፌሰር ክሪስቶፈር ኦግቦግቦ ነው።