«እቴሜቴ» የኢትዮ ጀርመን የቤተሰብና የባህል ማኅበር | ባህል | DW | 28.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«እቴሜቴ» የኢትዮ ጀርመን የቤተሰብና የባህል ማኅበር

«እቴሜቴ ትምህርት ቤቴ፤ መግለጫዬ ናት የማንነቴ፤ ሀ ሁ ብዬ ጅማሪን፤ ዳሰስኩኝ የፊደል ገበታዬን፤ ለየሁኝ ሀ ና ለ ን፤ አወኩኝ ፊደሎቼን፤ ተናገርኩ ቋንቋዬን፤ ሀ ሁ አቡጊዳ አልኩ፤ አነበብኩ፤ እየቆጠርኩ፤ እየተኮላተፍኩ፤ ባትኖረኝ ኖሮ እቴሜቴ፤ የእዉቀት መገብያ ቤቴ፤ መች አዉቅ ነበር ቋንቋዬን፤ አኩሪ ባህል እንዳለኝን፤

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:35

«እቴሜቴ» የኢትዮ ጀርመን የቤተሰብና የባህል ማኅበር

አገኘሁኝ አምሳዮቼን፤ የአገሪን ልጆች ወገኖቼን፤ ተጫወትኩ ድብብቆሽ እቴሜቴ፤ ልጅነቴ ማርና ወተቴ፤ ተማርኩ አወኩ ባህል ወጌን፤ የማንነት መገለጫዬን፤ ስለዚህም ላመስግንሽ እቴሜቴ፤ የኢትዮጵያ ሃገሪ ምትክ ቤቴ።»በኮለኝ ከተማ የሚገኘዉ የኢትዮጵያዉያኑ ማኅበር «እቴሜቴ» የኢትዮ ጀርመን የቤተሰብና የባህል ማኅበር ዓመታዊ በዓል ላይ የዘጠኝ ዓመትዋ ህፃን አኒሳ ረዲ እቴሜቴ በሚል ርዕስ ያቀረበችዉ ሥነ- ግጥም ነበረ። አኒሳ አማርኛ መናገር መፃፍ ማንበብ የተማረችዉ በጀርመን ኮለኝ ከተማ በሚገኘዉ ኢትዮጵያዉያኑ በቋቋሙት በእቴሜቱቴ የአማርና ቋንቋ መረሃ-ግብር ላይ ነዉ። ባለፈዉ እሁድ ግንቦት 16 ዓመታዊ በዓሉን ያከበረዉ የኮለኙ «እቴሜቴ» የኢትዮ ጀርመን የቤተሰብና የባህል ማኅበር በተለይ ከወራቶች በፊት ማኅበሩ በጀርመን መንግሥት እዉቅናን አግኝቶ ሕጋዊ ሆንዋል። በዕለቱ ዝግጅታችን በኮለኝ ከተማ ስለሚገኘዉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበርና የቋንቋ ትምህርትና የባህል ማስተዋወቅያ መድረክ መሰናዶ ይዘናል።ከጎርጎረሳዊዉ 2011 ዓ,ም ጀምሮ አስር ህጻናትና ወደ ስምንት የሚሆኑ ቤተሰቦችን ይዞ ህጻናቱን የኢትዮጵያ ቋንቋ አማርኛን በማስተማር ባህልን በማሳወቅ የጀመረዉ ይህ ማኅበር ዛሪ ከአርባ በላይ ህጻናትና ወደ ሃያ ሰባት የሚሆኑ ቤተሰቦቻቸዉን በየሁለት ሳምንቱ በአንድ ጣርያ ያሰባስባል። ወላጆች በየአስራ አምስት ቀኑ የሚገናኙበት ይህ መድረክ «እቴሜቴ » የሚል ስያሜን ያገኘዉ የኢትዮጵያን ባህልና የአማርኛ ቋንቋን ከሚማሩት ከራሳቸዉ ከህጻናቱ መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ ይገልፃሉ ።

«በጎርጎረሳዉያኑ 2011 ላይ እኛ እራሳችን ቤተሰቦች ብቻ ተሰብስበን ካሪታስ የሚባል ድርጅት አለ በአቶ እስጢፋኖስ ሳሙኤል አማካኝነት ቤት ሰጥተዉን ከ 2011 ዓ,ም ጀምሮ ልጆችን አማርኛ ቋንቋን ማስተማር ጀመርን። አማርኛ ቋንቋን የማስተማር ባህል የማስተዋወቅ ሃሳቡ የተጀመረዉ በ 2011 ዓ,ም ነዉ። ልጆቹ ወደዛ ልጆቹን ቋንቋ ወደምናስተምርበት ቦታ ሲሄዱ ወደ እቴሜቴ ነዉ የምንሄደዉ እያሉ ነዉ የሚነግሩን። እናም በአጭሩ «እቴሜቴ» አማርና ቋንቋን ለማስተማር ልጆቻንን ለማሳወቅ የተቋቋመ ማኅበር ነዉ ሌላ ነገር የለዉም።»በጀርመን ሃገር በተለያዩ የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎቶች ዉስጥ የሰሩትና በአሁኑ ወቅት እዚሁ ጀርመን በቻይናዉ ህዋዌ የስልክ አገልግሎት መሥርያ ቤት ዉስጥ የምርምር ክፍል መሪ የሆኑት ዶክተር አብዱራዛቅ ሙደሲር ልጆቻቸዉ በእቴሜቴ የቋንቋና ባህል ትምህርት መድረክ ተካፋይ ናቸዉ።

«ይህ ማኅበር በኮለኝ ከተማና አካባቢዋ የሚገኙ አበሾች በተለይ ኢትዮጵያዉያን በብዛት ተሰባስበን ልጆቻችንን ቋንቋችንን የምናስተምርበት ባህላችንን የምናሳዉቅበት ነዉ። አስተማሪዎቹም ወላጆች ናቸዉ የማስተማር ልምድ ያላቸዉ፤ ፊደልን ማስቆጠር ሀ ሁን ልጆቹን ማንበብ መፃፍ እንዲችሉ ነዉ የሚያደርጉት። በወር ሁለት ጊዜ ነዉ የምንንገናኘዉ እሁድ እሁድ ግማሽ ቀን ልጆቹ ለሁለት ሰዓታት ያህል ትምህርት ሲማሩ ወላጆች ደሞ አብረዉ በመጨዋወት ሃሳብ በመቀያየር ጊዜን ያሳልፋሉ።»ባለፈዉ እሁድ በኮለኝ የሚገኘዉ የኢትዮጵያዉያን ማኅበር ዓመታዊ በዓሉን ሲያከብር ከ 150 እስከ 200 የሚሆኑ ሰዎች መገኘታቸዉን የማኅበሩ ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል ተስፋዬ ተናግረዋል። የማኅበሩ የፊናንስ ክፍል ተጠሪ አቶ ሳሙኤል ሙሉጌታ ይህ ባለፈዉ እሁድ ያከበርነዉ በዓል ከሌላዉ ጊዜ ለየት የሚያደርገዉ ማኅበሩ በጀርመን እዉቅናን በማግኘቱ መሆኑን ገልፀዋል።

«እዚህ ጋር ማኅበሩ እንደዚሁ በአንድ ሰዉ ተቋቋመ ማለት አይቻልም። ከ 20 እስከ 30 የሚሆኑ ወላጆች ያሉበት ስብስብ በሳምንት በሁለት ሳምንት በመገናኘት እንዲሁም ባሉት የባዕላት ጊዜ ሁሉ መገናኘት አብረን ራሳችንን ልጆቻችንን እና ባህላችንን በተመለከተ የተለያዩ ዝግጅቶችን እያደረግን ቆይተናል እና ይህ በዚህ ሳምንት ያደረግነዉ ዝግጅት ካለፉት ጊዜያቶች ለየት የሚያደርገዉ ልጆቹን ከቋንቋቸዉ በስተጀርባ የሃገራቸዉን ባህል የተማሩትን በመድረክ ለኛና የኛን ማኅበር ለሚወዱ ሰዎች ለማሳየት በአደረግነዉ ዝግጅት ለየት ባለ ሁኔታ ነዉ ያረቀብነዉ ነዉ ማለት ነዉ»

የዘጠኝ ዓመቱ ናሆም ሱራፊል ታደሰ የሚኖረዉ ተወልዶ ያደገዉም እዚሁ ጀርመን ነዉ። የኢትዮጵያዉያኑ ከአቋቋሙትና አማርኛ ከሚማርበት ከእቴሜቴ የባህልና የቋንቋ ትምህርት ቤት መቅረትን አይወደም። ናሆም ሱራፊል ታደሰ ማራቶን የምትል ትንሽ ጽሑፍ አለችኝ ብሎ በተኮላተፈ ጣፋጭ አንደበቱ አንብቦልናል።ማኅበሩ በአሁኑ ወቅት በርካታ የፊደል እንዲሁም የንባብ ተማሪዎች እንዳሉት የገለፁት የማኅበሩ የሂሳብ ክፍል ተጠሪ አቶ ሳሙኤል ሙሉጌታ በመቀጠል፤
«ይህን ትምህርት ማለት የሃገራችን ቋንቋ ፊደል መቁጠር ብሎም መጻፍ ማንበብ አማርኛን መናገርን ማስተማር ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ሲሳተፉ የነበሩ ልጆች እድምያቸዉ እየጨመረ በመሄዱ፤ ሁለተኛ ትምህርቱን ከመጀመርያዉ ጀምሮ በመከታተላቸዉ ያላቸዉ የትምህርት ብቃት የተሻለ ሆኖ ስላገኘነዉ በአንድ ክፍል መድበናቸዋል። በቅርቡ ይህን ማኅበር ይህን ትምህርት የተቀላቀሉትን ልጆች ደህሞ ከመጀመርያ ማለት አንደኛ ክፍል ዉስጥ መድበን በበቂ ትምህርቱን እንዲያገኙ በማድረግ ትምህርቱን በብቃት እንዲከታተሉ እያደረግን ነዉ። በአንድ ክፍል ዉስጥ ማለት በመጀመርያዉ ክፍል 2o ተማሪዎች ማለት ህጻናት ይገኛሉ። በሁለተኛዉ ክፍል የሚገኙት ማለት ይህን ትምህርት ከመጀመርያዉ ጀምሮ የሚከታተሉት ተማሪዎች ቁጥራቸዉ ትንሽ በዛ ይላል ቁጥራቸዉ ወደ 27 ይደርሳል ።»


አቶ ሳሙኤል ሙሉጌታ በመቀጠል ይህ ማኅበር በኮለኝና አካባቢዋ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያንን ልጆቻቸዉን ብቻ ሳይሆን የሚያሰባስበዉ የኢትዮጵያን ባህል ለማወቅ ጉጉት ያላቸዉን በርካታ ጀርመናዉያንን ጭምር መሆኑን ተናግረዋል።
« በምንኖርበት በዚህ አካባቢ ማኅበሩ ዓመታዊ በዓሉን እንደሚያከብር ቀድመን ሰፊ ማስታወቅያ በመሥራታችን በርካታ የጀርመን ሃገር ተወላጆችም ሆኑ ሌሎች አዉሮጳዉያን በዝግጅቱ ላይ ተካፋዮች ነበሩ፤ በአብዛኛዉ በተደረገዉ ባህላዊ ዝግጅት ሆነ የተለያዩ የሃገራችንን ባህል ሊያሳዩ የሚችሉ ሥራዎች በጣም በመደነቅ ነዉ የተመለከቱት ለኛ ለወደፊቱም የተሻለ መንገድ ልንሄድበት የምንችል እጅግ ጠቃሚ የሆነ አስተያየቶችን የሰነዘሩበትና ጥሩ ጊዜ ማሳለፋቸዉን ነዉ ከአስተያየታቸዉ ልንረዳ የቻልነዉ። »በፎርቹን ጋዜጣ ላይ ትፅፍ እንደነበር የነገረችን ጋዜጠኛ ሃና ወንድም ሸዋ ማሙዬ ልጆችዋ በዚሁ በእቴሜቴ ማኅበር ላይ የአማርኛ ቋንቋን ይማራሉ። በዚህ ማኅበር የናቶች የሴቶች ተሳትፎምን ያህል ነዉ።
የዛሬዎቹ የእቴሜቴ አማርኛ ቋንቋ ተማሪዎችና የኢትዮጵያን ባህል ቀሳሚዎች ነገ ከከፍተኛ ተቋማት በተለያዩ ሞያዎች ተመርቀዉ ሃገርን የሚገነቡ ዜጎች ናቸዉና ባህላቸዉን ቋንቋቸዉን ልናሳዉቃቸዉ የሚገባ ይመስለናል። በዚህ ረገድ የኮለኙ «እቴሜቱ የኢትዮ ጀርመን የቤተሰብና የባህል ማኅበር» እየሰራ ያለዉ ተግባር ይበል የሚያሰኝ ይመስለናል።ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ መማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic