እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች ታሰሩ | ኢትዮጵያ | DW | 25.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

እስክንድር ነጋና አንዷለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች ታሰሩ

በቅርቡ ከእስር የተፈቱት ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌን ጨምሮ 11 ሰዎች በዛሬው ዕለት መታሰራቸውን የዓይን እማኞች ገለጹ፡፡ ግለሰቦቹ የታሰሩት በተወሰኑ ወጣቶች አሰባሳቢነት በቅርቡ ከእስር ለተለቀቁ ሰዎች በተዘጋጀ የምስጋና መርኃ ግብር ላይ እየተሳተፉ ባለበት ወቅት መሆኑ ተነግሯል፡፡ 

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ፖለቲከኛ አንዱዓለም አራጌ፣ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ታስረዋል ከተባሉት መካከል ይገኙበታል። 11ቱ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች የተወሰዱት በተመስገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት ከተዘጋጀ የምሥጋና መርኃ-ግብር ላይ መሆኑን የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል ከሶስት ዓመት እስር በኋላ ባለፈው ጥቅምት ወር ከእስር የተለቀቀው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ይገኝበታል፡፡ የምስጋናው መርኃ ግብር ይካሄድ የነበረውም በአዲስ አበባ ጀሞ በሚገኘው የጋዜጠኛ ተመስገን ቤት እንደነበር ወንድሙ ታሪኩ ደሳለኝ ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል፡፡ 

“ዛሬ መጋቢት 16፣ 2010 ዓ.ም ለማመስገን እና ስጦታ ለመስጠት ጀሞ የሚገኘው የተመስገን ደሳለኝ ቤት ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይም ከሚመሰገኑት እና ስጦታ ከሚሰጣቸውሰዎች መካከል ተመስገን አንደኛው ነበር፡፡ ከዚያ አንዱአለም [አራጌ] አለ፡፡ [ክንፈሚካኤል ደበበ] አበበ ቀስቶ፣ ናትናኤል መኮንን፣ ማሙሸት አማረ፣ ኦልባና ሌሊሳ እና እማዋይሽ [አለሙ] እነዚህ ሰዎች የሚመሰገኑበት ነበር፡፡ ይህንን ፕሮግራም እያዘጋጀን ከዚያ መሃል ወታደሮች መጡና ያለንበትን የእኛን ቤት ከበቡት፡፡ የምንፈልገው እነርሱን እነርሱን ነው ተባለ፡፡ ረጅም ሰዓት ከበው ቁጭ አድርገዋቸው ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ የወታደር መኪና አምጥተው፣ ጭነዋቸው እዚህ ጀሞ የሚገኝ ሙዚቃ ቤት ሰፈር ውስጥ ፖሊስ መምሪያ እዚያ አስገብተዋቸዋል” ብሏል የዓይን እማኙ፡፡ 

ከመርኃ-ግብሩ አዘጋጆች መካከል አንዷ የሆኑት መዓዛ መሐመድ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ወደ ተመስገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት ያቀኑት የጸጥታ አስከባሪዎች ለምን ኮኮብ የሌለው ሰንደቅ ዓለማ ተጠቀማችሁ የሚል ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱት የጸጥታ አስከባሪዎች ሰንደቅ አላማውን ጎትተው ማውረዳቸውንም አክለው ተናግረዋል። በመርኃ-ግብሩ መጠናቀቂያ የደረሱት ፖሊሶች ለሰንደቅ አላማው አጠቃቀም እና ለመርኃ-ግብሩ ዝግጅት ተጠያቂ የሚሆን አንድ ሰው ይዘው ለመሔድ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም ታዳሚዎቹ በፈቃዳችን ተሰብስበናል በሚል አቋማቸውን ማሳወቃቸውን መዓዛ ተናግረዋል። ይኸንን ተከትሎ የጸጥታ ኃይሎች ተጨማሪ ኃይል ጠይቀው የመርኃ-ግብሩን ሶስት አዘጋጆች ጨምሮ 11 ሰዎች በአቅራቢያው ወደ ሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ መውሰዳቸውን አስረድተዋል። 

በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ለተወሰኑ ሰዓታት ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር የስልክ ግንኙነት ሲያደርጉ የነበረ ቢሆንም በስተመጨረሻ ግንኙነቱ መቋረጡን የአይን እማኞች ተናግረዋል። ቤተሰቦች ምግብ እና አልባሳት ለመስጠት ሞክረው መከልከላቸውንም ገልጸዋል። 

ዛሬ ለእስር ከታደረጉት ውስጥ ለአራት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በእስር ላይ ቆይቶ ባለፈው ጥር ወር የተፈታው ጦማሪ እና አራማጅ (አክቲቪስት) ዘላለም ወርቅአገኘሁ ይገኙበታል፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ስብስብ አባል የሆኑት በፍቃዱ ኃይሉ እና ማህሌት ፋንታሁንም ከታሳሪዎቹ መካከል እንደሚገኙበት ታሪኩ ገልጿል፡፡   

ተስፋለም ወልደየስ

እሸቴ በቀለ