እስክንድር ነጋና ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ 11 ሰዎች ተፈቱ | ኢትዮጵያ | DW | 05.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

እስክንድር ነጋና ተመስገን ደሳለኝን ጨምሮ 11 ሰዎች ተፈቱ

ኮኮብ የሌለው ሰንደቅ አላማ ተጠቅማችኋል በሚል ሰበብ እስር ላይ የሰነበቱት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ተፈቱ። ዛሬ ከተፈቱት መካከል ጦማሪዎቹ ዘላለም ወርቅ አገኘሁ፣ ማኅሌት ፋንታሁን፤ በፍቃዱ ኃይሉ እና ፖለቲከኞቹ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ ወይዘሪት ወይንሸት ሞላ ይገኙበታል።

ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ጦማሪንን ጨምሮ ለአስር ቀናት ገደማ እስር ላይ የሰነበቱ አስራ አንድ ግለሰቦች ተፈቱ። ጋዜጠኞቹ እስክንድር ነጋ እና ተመስገን ደሳለን ጦማሪያኑ ማኅሌት ፋንታሁን፣ በፍቃዱ ኃይሉ፣ ዘላለም ወርቅአገኘሁን ጨምሮ አስራ አንዱ ግለሰቦች በቀበሌ መታወቂያ ከእስር መለቀቃቸውን ጋዜጠኛ በላይ ማናየ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጧል። 
ዛሬ መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ.ም ማምሻውን ከእስር ከተፈቱት መካከል ፖለቲከኞቹ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ አቶ ይድነቃቸው አዲስ እና ወይዘሪት ወይንሸት ሞላ ይገኙበታል። ጋዜጠኛ በላይ እንዳለው ከአስራ አንዱ ግለሰቦች መካከል አንዳቸውም ክስ አልተመሰረተባቸውም። 

እነ እስክንድር ነጋ መጋቢት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. የታሰሩት በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት ከተዘጋጀ የምሥጋና መርኃ-ግብር መገባደጃ ላይ በጸጥታ ኃይሎች ተወስደው ነበር። በዕለቱ በቦታው የነበሩ የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ወደ ተመስገን ደሳለኝ መኖሪያ ቤት ያቀኑት የጸጥታ ኅይሎች ኮኮብ የሌለው ሰንደቅ አላማ ተጠቅማችኋል በሚል አስራ አንዱን ሰዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወስደው አስረዋቸዋል። 

የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለት አመታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ካወጀ በኋላ 1107 ሰዎች መታሰራቸውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር የሚመረምረው ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ታደሰ ሆርዶፋ ባለፈው ሳምንት አስታውቀው ነበር። በትናንትናው ዕለት በባሕርዳር ከተማ በእስር ላይ የነበሩ 19 ሰዎች መፈታታቸው አይዘነጋም።
እሸቴ በቀለ