«እስከ ጊዜዉ በርቺ» አለማየሁ እሸቴ | ባህል | DW | 26.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

«እስከ ጊዜዉ በርቺ» አለማየሁ እሸቴ

«የዘፈኑን ዕድሜ ስነግራችሁ ሸመገለ እንዳትሉኝ እንጂ « ተማር ልጄ» የተዘፈነዉ የዛሬ ሰላሳ አምስት ዓመት ነዉ። ያዘለዉ መልክት እዉነተኛ አባት ለልጁ የሚሰጠዉ ምክር ነዉ። የሰዉ ልጅ ካልተማረ ዋጋ የለዉም። ስለሆነም አባቶች የሚሰጡንን ምክር በዚህ ዘፈን ለመጭዉ ትዉልድ የዘራሁት ነዉ ብዬ ነዉ የማምነዉ» አለማየሁ እሸቴ

ድምፃጻዊ አለማየሁ እሸቴ በጀርመናዉያን የሙዚቃ ባንድ በመታጀብ ቀደም ሲል ያዜማቸዉን ሙዚቃዎች በማቅረብ ለጀርመናዉያን መገናኛ ብዙኃን ማብራርያ ሲሰጥ ነበር ያደመጥነዉ። መቀመጫዉን በርሊን ላይ ያደረገዉ፤

«የሊስትሮ ማኅበር» የተሰኘዉ ድርጅት «እስከ ጊዜዉ በርቺ» የተሰኘዉን የድምፃዊ አለማየሁ እሸቴን ሙዚቃ መሪ ቃሉ በማድረግና በእንግሊዘኛ «STAY STRONG UNTILL A BRIGHT DAY COMES» የሚለዉን ትርጉም

በማስቀመጥ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴን ላበረከተዉ ሥራ እዉቅና ለመስጠት ለጥበቡ ክብር ለመሥጠት እንዲሁም ሙዚቃዎቹን በማስተዋወቅ አዳዲስ ሙዚቃዉንም ለሙዚቃ አፍቃሪዎች ጆሮ ለማድረስ በዝግጅት ላይ ይገኛል።

«ጥራጥሬም ቢሆን ቆልተን እየበላን ፤ ተመስገን እያልነው ዉሃን እየጠጣን፤ ስቀን ተሳስቀን ካልኖርን እኔና አንቺ ፤ ብዙ ቀን አያልፍም እስከጊዜው በርቺ»

የድምፃዊ አለማየሁ እሸቴን «እስከ ጊዜዉ በርቺ» የተሰኘዉን ሙዚቃ መሪ ቃሉ በበማድረግና በእንግሊዘኛ«STAY STRONG UNTILL A BRIGHT DAY COMES» የሚለዉን ትርጉም በማስቀመጥ ከአንጋፋዉ ሙዚቀኛ ጋር ሰፊ ዝግጅት የጀመረዉ የበርሊኑ የሊስትሮ ድርጅት ባሳለፍነዉ ሳምንት ቅዳሜ የተለያዩ የጀርመን ሚዲያዎችን ጋብዞ ዝግጅቱን አስተዋዉቋል። ዝግጅቱ ገና ለወራቶች የሚቀጥል ነዉ። ለአንጋፋዉ ከያኒ ለአለማየሁ እሸቴ ለሰራዉ ሥራ እዉቅና ክብር እንደሚሰጥም ነዉ የተነገረዉ። አዲስ ሙዚቃዉን በማዘጋጀት እንዲሁም ቃለ ምልልሶችን በመስጠት በርሊን ላይ በሥራ ተወጥሮ የሚገኘዉ፤ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴን በስልክ እንኳና ደህና መጣህ፣ በርሊን እንዴት ተቀበለህ? ነበር ያልነዉ፤

«እንደሌላዉ ጊዜ ተዘጋጅጄ የሙዚቃ ድግሴን ለማሳየት አይደለም የመጣሁት፤ ሊስትሮ ከኔ ጋር ፕሮግራም በመጀመሩና ሰዎቹ ቅርብ ወንድሞቼ ስለሆኑ ከማበረታታት አንፃር የሆነ ርምጃ ለማድረግ በሚል ነዉ። በዝግጅታችንም ጥሩ ጥሩ ነገርን እያደረግን ነዉ። እንደ እግዚአብሄር ፈቃድ ከመጭዉ ግንቦት ወር ጀምሮ የሙዚቃ ድግስ ይኖረናል»

«የሊስትሮ ሽልማት » በሚል ከጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ,ም ጀምሮ ክብሩንና ሽልማቱን የሚሰጠዉ የሊስትሮ ማኅበር የተሰኘዉ ድርጅት በበርሊን፤ዘንድሮ አንጋፋዉን ከያኒ አለማየሁ እሸቴን ለሽልማት እንደምያበቃ የማኅበሩ መስራችና ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሻንቆ ተናግረዋል።

« የሊስትሮ ማኅበር ዋና ዓላማና ሥራ እንዴት ነዉ ሰዉን ባለበት ሁኔታ ማበረታታት የምንችለዉ? የጎደለዉንና የሌለዉን ነገር ከመቁጠር ያለዉን ነገር ጠንካራ ጎኑን አንስተን የሞራል ድጋፍ መስጠት የምንችለዉ፤ ከሚለዉ ዓላማ ጋር የተያያዘ ነዉ። በዚህም ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴን መርጠናል። የመረጥንበት ምክንያት ሥራዉ ነዉ። የሱ ስራ የሱ ሙዚቃ እኔም እራሴ በህይወቴ ሲያግዘኝ ሲያበረታታኝ የኖረ ሥራ ነዉ። አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ዕድሜዉ 74 ዓመት ሆነ፤ በኛ በኢትዮጵያዉያን ልማድም ሰዉ ካልሞተ ቀደም ተብሎ የሚዘጋጅለት የምሥጋናና አንተ የሰራኸዉ ሥራ እኛን አግዞናል የሚል ነገር የሰፋ ስላልሆነ ነዉ። የአለማየሁ እሸቴን ሥራ አንስተን ያበረከተዉ አስተዋፅዖ ከፍተኛ ይህ የሊስትሮ ክብርና ምስጋና ይገባሃል ብለን አንድ ፕሮግራም ለማዘጋጀት ጋብዘነዋል። »

ለመጀመርያ ጊዜ በ1955 ዓ, ም በፖሊስ ሠራዊት ኦርኬስትራ የተቀጠረዉ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ በዝያን ጊዜ በብዛት የኤልቪስ ፕሪስሊን ሙዚቃዎች በአማርኛ ደግሞ የጥላሁን ገሰሰን ሙዚቃዎች ያዜም እንደነነር ይናገራል፤ ግን ቀደም ሲል አዲስ አበባ GCA ትምህርት ቤት ሳለ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝሙሮችን ያዜም ስለነበር ለዚህ ጉዞዉ ፈር ቀዳጅ እደሆኑት ይናገራል። አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ሙዚቃዎቹን ከአዲሱ ትዉልድ ጋር አስማምቶ የመሥራቱ ሚስጥር ጠንክሮ መሥራት መሆኑን ይገልፃል።

« ጥረት ነዉ፤ ለአንድ ነገር ጥረት እስካለ ድረስ ወኔሽ እስካልሞተ ድረስ አይወድቅም። በአጋጣሚ ደግሞ እግዚአብሄር ይመስገን ጤና ሰጥቶኛል»

የኢትዮጵያዉ ኤልቪስ በሚል መጠርያዉ የሚታወቀዉ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ይህን ሥም ይቀበለዉ ይሆን?

« ያ የልጅነት ነበር። ቋንቋዉም የልጅነት ነዉ፤ ወቅቱም የልጅነት ነበር። ኢትዮጵያዊዉ የዚያ የኩሩ ዜጋ የዛ የደሃ ልጅ ነኝ። ስለዚህ አለማየሁ እሸቱን እንጂ አለማየሁ ኤልቪስን አልቀበለዉም።

በርሊን ላይ የሚገኘዉ የሊስትሮ ማኅበር የተሰኘዉ ድርጅት ከጎርጎረሳዉያኑ 2006 ዓ,ም ጀምሮ ለ 19 ሰዎች ሽልማቱን እና ክብሩ አበርክቶአል ፤ ከነዚህ ሰዎች መካከል በጀርመን የኢትዮጵያ አንባሳደር ህሩይ አማኑኤልና የቀድሞዉ የጀርመን ፕሬዚዳንት ሆርስት ኮለር ተጠቃሽ ናቸዉ። ባለፈዉ ሳምንት ቅዳሜ ይህ ድርጅት በርካታ የጀርመን መገናኛ ብዙኃን ጋብዞ በሙዚቃ የተደገፈ ጋዜጣዊ መግለጫን ሰጥቶ ነበር ።

አዲስ አበባ ተወልዶ በህጻንነቱ ቀድሞ ወሎ ክፍለ ሃገር ወደ ሚባለዉ አካባቢ እንደነበር የሚናገረዉ አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ አባቱ ሙዚቀኛ መሆኑን እንዳልወደዱለት ይናገራል። ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ ከኩከ ሰብስቤ እንግዳዬነሽ በሚለዉ የቅብብሎሽ ሙዚቃዉ ቢታወቅም ቢወደድም ከሌላ ሙዚቀኛ በጋራ አብሮ የማዜም እጅግ ፍቅርም እንደሌለዉ ተናግሮአል።

ለሚስቱና ለልጆቹ ማቆላመጫ «ውዷ ባለቤቴ!» የምትል ዜማ የተጫወተዉ የሰባት ልጆች አባት ብሎም አያት የሆነዉ ተወዳጁ ኢትዮጵዊ አንጋፋ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴ እናቴ ከሚላት ባለቤቱ ጋር ጥሩ ጤና ረጅም እድሜ እንመኛለን። ጊዜ አይሽሪ የሆኑትን የአለማየሁ እሸቴን ሙዚቃዎች ለምዕራቡ ዓለም በማስተዋወቅ ከኢትያ በሙዚቃ ድልድይ የዘረጋዉን የሊስትሮ ማኅበር ድርጅት የጀመረዉ ሥራ የሚበረታታና ይበል የሚያሰኝ ይመስለናል። ለዝግጅቱ መሳካት አንጋፋዉ ሙዚቀኛ አለማየሁ እሸቴና የሊስትሮ ማኅበር ሰራተኞች ላደረጉልን ትብብር እናመሰግናለን። ሙሉዉን ቅንብር የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ።

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic