እስከ አዲስ አበባ የዘለቀው የኦሮሞ ተቃውሞ | ኢትዮጵያ | DW | 06.08.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

እስከ አዲስ አበባ የዘለቀው የኦሮሞ ተቃውሞ

ከዚህ ቀደም በኦሮሚያ ከተሞች ብቻ ተወስኖ የነበረው የኦሮሞ ተቃውሞ በዛሬው ዕለት እስከ አዲስ አበባ የዘለቀ ሲሆን 50 ተቃዋሚዎች መገደላቸውን ኦሮሚያ ሚድያ ኔትወርክ ዘግቧል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:23

የኦሮሞ ተቃውሞ-የአይን እማኞች

አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ተቃውሞ ተካሂዷል።በባሌ ሮቤ፤አርሲ፤ሆለታ፤ወሊሶ፤ በሰሜን ሸዋ ጫንጮ፤በቦረና የሞያሌ ከተማ፤ምዕራብ ሸዋ፤ሻሸመኔ እና ቄለም ወለጋን በመሳሰሉ አካባቢዎች የተካሄዱ ሰልፎችን የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እና ቪዲዮዎች በማህበራዊ ድረ-ገጾች ተሰራጭተዋል። «ነዋሪዎች ከመኖሪያ ቤታቸው እንዳይወጡ ኃይለኛ ተኩስ ነበረ» የሚሉት የበዴሳ ከተማ ነዋሪ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ ወጣቶች እና ከገጠር የመጡ ሰዎች ተሰብብሰው ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የጸጥታ ኃይሎች ሰልፈኞችን ለመበተን በወሰዱት እርምጃ አንድ ተቃዋሚ በጥይት መገደላቸውንና በርካቶች መቁሰላቸውንም ጨምረው ገልጠዋል። «ህዝቡ እና ወታደሩ እኩል ነው» የሚሉት የበዴሳ ከተማ የአይን እማኝ «ያለ ምክንያት የታሰሩ የኦሮሞ ልጆች እና ሌሎችም ይፈቱ» «የኦሮሞ ገበሬዎች ያለ በቂ ምክንያት እና ያለ በቂ ክፍያ ከመሬታቸው እየተፈናቀሉ ስለሆነ ይቁም» የሚሉ መፈክሮች መደመጣቸውን ተናግረዋል።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ሙክታር ከድር ሐምሌ 28 ቀን 2008 ዓ.ም. በክልሉ የተጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ «ለብጥብጥ የተጠራ» እንደሆነ ገልጠው እውቅና የለውም ብለው ነበር። የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪውን ህጋዊ አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሐይለ ማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው በዕለተ-አርብ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግስት እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቀው ነበር።

በምስራቅ ሐረርጌ የቆቦ ከተማ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፉ የአይን እማኝ «ወደ 2000 የሚጠጉ ሰዎች» ለተቃውሞ አደባባይ መውጣታቸውንና ከጸጥታ ኃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም አምስት ሰዎች መቁሰላቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምሥራቅ ሸዋ በባቱ(ዝዋይ) ከተማ የሚገኙ ሌላ የአይን እማኝ በዝናባማው ዕለተ-ቅዳሜ ለተቃውሞ አደባባይ የወጡ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች መበተናቸውን አስረድተዋል። የአይን እማኙ ወደ 600 ተቃዋሚዎች በጸጥታ ኃይሎች መወሰዳቸውንና መደብደባቸውን አስረድተዋል። ተቃዋሚዎች የኦሮሞ ፖለቲካ መሪው አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎች እስረኞች እንዲፈቱ የወልቃይት እና ጠገዴ የማንነት ጥያቄም እንዲከበር መጠየቃቸውን የአይን እማኙ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

መቀመጫውን በዩናይትድ ስቴትስ ያደረገው ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ በዛሬው ዕለት ብቻ 50 ሰዎች መገደላቸውን ዘግቧል። የኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች እና ተቃውሞውን የሚከታተሉ ወገኖችም ሰላማዊ ሰልፈኞች በጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን፤መቁሰላቸውንና መታሰራቸውን እየገለጡ ነው።

በኦሮሞ ተቃውሞ አስተባባሪዎች የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ከአሁን ቀደሙ በተለየ አዲስ አበባ ደርሷል።ወደ መስቀል አደባባይ ያመሩት የተቃውሞ ሰልፈኞች በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ መሪዎች እና ዜጎች እንዲፈቱ ጠይቀዋል። ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ባይቻልም ከትናንትናው ዕለት ጀምሮ የኢንተርኔት አገልግሎት እጅጉን ደካማ መሆኑ ተሰምቷል። በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትን ለማነጋገር ያደረግንው ሙከራ አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

Audios and videos on the topic