እስራኤል ፍልስጤሞች፤ ንግግርም-ኩርፊያም የለም | ዓለም | DW | 06.06.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

እስራኤል ፍልስጤሞች፤ ንግግርም-ኩርፊያም የለም

ላለፉት 25 ዓመታት የፍልስጤም እስራኤል ጉዳይ ለሌላ አላስነካም ያለችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ፈረንሳይን የመሰለ ተፎካካሪ ሥለመጣባት ነዉ።የፍልስጤም ባለሥልጣናት ለእስራኤል ሁለንተናዊ ድጋፍ የምትሰጠዉ ዩናይትድ ስቴትስ ገለልተኛ ሸምጋይ አይደለችም እያሉ እንዳጉረመረሙ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 13:05

እስራኤል ፍልስጤሞች፤ ንግግርም-ኩርፊያም የለም

የዓለም ኃያል-ሐብታም መንግሥታት ከአፍቃኒስታን እስከ ኢራቅ፤ ከሊቢያ እስከ ሶሪያ በቀጥታም በእጅ አዙርም የከፈቱት ዘመቻ ሐገር ከማጥፋት፤ ሕዝብ ከመፍጀት-ማሰደድ፤ሽብርን ከማስፋፋት ባለፍ አሸናፊም-ተሸናፊም እንደሌለ ሲረዱት ከተረሳዉ-የፍልስጤም-እስራኤሎች ዶሴያቸዉ ላይ አዋራ ያራግፉ ገቡ።የአዉሮጳ-አሜሪካ ሐያል፤ የአረብ-እስያ ሐብታም መንግሥታት ተወካዮች ባለፈዉ አርብ ፓሪስ-ፈረንሳይ ዉስጥ ባደረጉት ስብሰባ ሥለተዳፈነዉ የፍልስጤም-እስራኤሎች ድርድር መነጋገራቸዉ ተስፋ-በቀቢፀ ተስፋ ለሚጣፋበት ምድር በርግጥ ሌላ ተስፋ ነዉ።የተሰብሳቢ-ተወያዮቹን መልዕክት ባለጉዳዮች አለመቀበላቸዉ እንጂ ቀቢፀ-ተስፋዉ። የዛሬው ዝግጅት የተዘነጋነዉን የፍልስጤም እስራኤሎችን ማብቂያ የለሽ ጠብ-ድርድር ይቃኛል።

የቀድሞዉ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር በ2007 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ኳርቴት የተሰኘዉ ሥብስብ ልዩ መልዕክተኛ ሆነዉ ሲሾሙ የፍልስጤም እስራኤሎችን ጠብ-ግጭት ለማስወገድ ትልቅ ተስፋ-ዝግጅትም አለኝ ብለዉ ነበር።ሁለቱን ወገኖች «ሁለት መንግሥት» በሚለዉ አዲስ ሥልት ለማግባባትም «እድሉም፤ አጋጣሚዉም» ሠፊ ነዉ ብለዉ ነበር።«እንደሚመስለኝ እድል አለዉ የሚለዉ ስሜት አሁን ጠንካራ ነዉ።ይሁንና ባሁኑ ወቅት በጣም አስፈላጊዉ ነገር ማዳመጥ፤መረዳትና መገንዘብ ናቸዉ።»

የቀድሞ የሶቭየት ሕብረት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንድሬይ ግሮሚኮ በ1947 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር) ሐሳቡን ሲያቀርቡ የእስከዚያ ዘመኑን የአይሁድ ስቃይ፤ሰቆቃ፤ሞት-ስደትን ለማስቆም አስበዉ ነበር።እስከዚያ ዘመን ድረስ ፍልስጤም ይባል የነበረዉ ግዛት ለሁለት ተገምሶ ባንደኛዉ ገሚስ አይሁድ፤ በሌላዉ አረቦች መንግሥት ይመስርቱ የሚለዉ የግሮሚኮ ሐሳብ የአይሁድ ምኞት፤ የዋሽንግተኖች ዕቅድ፤ የለንደኖች ሥልት ሆኖ ሕዳር 1947 በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጉባኤ ሲፀድቅ የተፈጠረዉ ትልቅ ስሕተት፤

አይሁድ ፍልስጤምን እንዳጫረሰ፤ ዓለምን እንዳስደነገጠ፤ የሐያላን መንግሥታትን ፖለቲከኛ ዲፕሎማቶችን እንዳመላለሰ አለ።69 ዓመቱ።

ቶኒ ብሌር የአራቶች ልዩ መልዕክተኛ ሆነዉ ሲሾሙ-ያሉትን ሲሉ እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ያልቻሉ ወይም ያልፈለጉትን እንደ ልዩ መልዕክተኛ ገቢር ማድረግ-መቻላቸዉን የጠረጠሩ ብዙ ነበሩ።በጣም ብዙዎቹ ግን ብሌር ከግሮሚኮ እስከ ኤድዋርድ ሸቨርድናንዜ፤ ከጆርጅ ማርሻል እስከ ሔንሪ ኪሲንጀር፤ ከዎረን ክርስቶፈር እስከ ማድሊን ኦልብራይት፤ ከኡ ታንት እስከ ኮፊ አናን የነበሩና ያሉ ፖለቲከኛ ዲፕሎማቶች እስከ ብሌር ዘመን ካደረጉት የተለየ እንደማያደርጉ እርግጠኛ ነበሩ።

የእርግጠኞቹ ግምት ዉል አልሳተም።ብሌር የፍልስጤም እስራኤሎችን ፍላጎት ለማዳመጥ፤ ለመረዳትና ለመገንዘብ ከመቶ ጊዜ በላይ አካባቢዉን ተመላለሱበት።የአይሁድ፤ የአረብ፤የአዉሮጳ፤ የአሜሪካ መሪ-ዲፕሎማቶችን አነጋገሩ።የአረብ ሐገራት በሕዝባዊ አመፅ መናወጥ ሲጀምሩ በ2010 ብሌር የሰጡት አስተያየት የተልዕኳቸዉን ዉጤት ጠቃሚ ነበር።

«የአረብ ሕዝባዊ አመፅ እየተጠናከረ ሲመጣ፤ እነዚሕ ሐገራት ቱኒዚያ፤ ግብፅ፤ ሊቢያ እና ሶሪያ ተስፋቸዉ ምን ሊሆን ይችላል።እንዲያዉ ዜጎቹ መንግሥቶቻቸዉን በትክክል የመምረጥ ሙሉ መብት እንኳ ቢቀር ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ፤ የመገናኛ ዘዴዎች ነፃነት፤ ክፍት ገበያ ማግኘት ወደሚችሉበት ደረጃ መሸጋገር ይችሉ ይሆን? አብዛኛዉ ሕዝብ ይሕን ማድረግ ይፈልግ ይሆናል።ጥያቄዉ ግን እኛ እንረዳቸዋለን ወይ ነዉ።ርዳታችን ወታደራዊ አይደለም ያንን አላማቸዉን ከግብ ማድረስ የሚችል ድጋፍ እንሰጣቸዋለን ወይ ነዉ።»

ብሌር እኛ ሲሉ ሐያሉን ዓለም በጣሙን ምዕራቡን ዓለም ማለታቸዉ እንደሆነ ግልፅ ነዉ።ለግልፁ ጥያቄ ከፓሪስ፤ለንደን፤ ዋሽግተኝ የተሰጠዉ መልስ ሊቢያ ላይ ጦር ማዝመት፤ግብፅ ላይ በሕዝብ የተመረጠ መሪን ማስገልበጥ፤ ሶሪያ ላይ አማፂያንን ማስታጠቅ ሆነ።

2014 ሌላ ጦርነት።ተጨማሪ እልቂት።ለዲሞክራሲ፤ ለነፃነት፤ ለፍትሕ ያለመዉ ሕዝብ ጥያቄ ግብፅን በመፈንቅለ መንግሥት፤የሊቢያ እና ሶሪያን በጦርነት ማተረማሱ አልበቃ ያለ ይመስል እስራኤልና ሐማስ የተሰኘዉ ደፈጣ የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አዲስ ዉጊያ ገጠሙ።«እንደሚመስለኝ የአጭር ጊዜም ቢሆን መረጋጋትና ፀጥታ ለማስፈን በጣም ባጣዳፊ የሆነ ስምምነት ያስፈልገናል።ይሁንና ለዚሕ ግጭትና ዉጊያ መሠረት ለሆነዉ ለረጅም ጊዜዉ ጠብ ሁነኛ መፍትሔ ካልተበጀ ያሁኑ ዉጊያ ማስወገዱ ብቻ ብዙም አይጠቅምም።የረጅም ጊዜዉ ካልተወገደ የአጭር ጊዜዉ ሠላም ዳር አይዘልቅም።»

የረጅም ጊዜ ሰላም አይደለም።ተስፋዉም የለም።የብሌር፤ በዉጤም ዩናይትድ ስቴትስ፤ ሩሲያ፤ የተባበሩት መንግሥታት እና የአዉሮጳ ሕብረትን ያቀፈዉ አራትዮሽ የተሰኘዉ ስብስብ ሙከራም እንደገና ከሸፈ።ብሌርም በስድስተኛ ዓመቱ ሥልጣናቸዉን ለቀቁ።

ባለፈዉ አርብ

ፓሪስ ፈረንሳይ ዉስጥ ከተሰበሰቡት አብዛኞቹ ያዉ አራቶች የተሰኘዉ በዩናይትድ ስቴትስ የሚመራዉ ስብሰብ አባላት ተወካዮች ናቸዉ።አረቦችም አሉበት።ተሰብሳቢ ተወያዮቹ ፍልስጤም ይባል የነበረዉ ግዛት ለሁለት ከተገመሰበት ከ1947 ጀምሮ ሠላም ለማዉረድ በመፈለግ እና ባለመፈለግ መካከል ግራ ቀኝ ከሚላጋዉ አስተሳሰብ የተለየ ሐሳብ የሚያቀርቡ አይደሉም።

አዲስ ሐሳብ ቀርቶ ከሁለት ዓመት በፊት ጨርሶ የተቋረጠዉ የእስራኤልና የፍልስጤም ድርድር የሚቀጥልበትን ጊዜ እንኳን በግልፅ አልተነገረም።የእስራኤልና የፍልስጤም ተወካዮችም በስብሰባዉ ላይ አልተካፈሉም።እንዲያዉም የጠቅላይ ሚንስትር ቢንያም ኔታንያሁ መንግሥት ስብሰባ-ዉይይቱን አጥብቆ ተቃዉሞታል።

በጀርመን የቀድሞዉ የእስራኤል አምባሳደር አቪ ፕሪሞር ግን ስብሰባዉ መደረጉ ተገቢ ነዉ ይላሉ።«ባሁኑ ሰዓት እስራኤልና ፍልስጤሞችን ለማግባባት የጋራ ሽማግሌ የለም።እና የሆነ ወገን ሐላፊነቱን መዉሰድ አለበት።መካከለኛዉ ምሥራቅን ለድርድር የሚያዘጋጅ ማለት በቀጥታም ባይሆን ግፊት የሚያደርግ ወገን ያስፈልጋል።ፍልስጤሞች በእስራኤል መንግሥት ላይ ጫና ለማድረግ ምንም አቅም የሌላቸዉ መሆኑ ግልፅ ነዉ።የእስራኤል መንግሥት ደግሞ ለመደራደርም ሆነ ሰጥቶ ለመቀበል አይፈልግም።ሥለዚሕ ሐላፊነቱን መዉሰድ ያለበት ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ መሆን አለበት።ማለት አዉሮጳ እና አሜሪካ መሆን አለባቸዉ።ዉይይቱም በመጀመሪያ እስራኤልና የፍልስጤም ተወካዮች በሌሉበት መደረግ አለበት።»

ስብሰባዉን የጠራችና ያዘጋጀችዉ ፈረንሳይ ናት።ፕሬዝደንት ፍራንሷ ኦሎንድ ለተሰብሳቢዎቹ ባደረጉት ንግግር እየተጠናከረ የመጣዉ የአሸባሪዎች ጥቃት እና የሽብርተኝነት ስሜትን ለመግታት የመካከለኛዉ ምሥራቅን ድርድር መጀመር አስፈላጊ ነዉ።የፓሪሱ ስብሰባ የተደረገዉም ሁለቱ ወገኖች የሚደርሱበት የሠላም ስምምነት ፅኑ እንደሚሆን ዓለም አቀፍ ዋስትና ለመስጠት ስለሚረዳ ነዉ።

ኦሎንድ ገና ከድርድር በኋላ ሥለሚደርስበት ስምምነት ያወራሉ።የእስራኤል ደግሞ ድርድር፤ ሥምምነት፤ ገቢራዊነቱን አይደለም ገና ሥለድርድር የተነጋገረዉን የፓሪሱን ስብሰባ ራሱን ተቃዉማዋለች።የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳሉት የፓሪሱ ስብሰባ በመጀመሪያዉ የዓለም ጦርነት ማብቂያ (በ1916) መካከለኛዉ ምሥራቅን ለመቀራመት ብሪታንያ እና ፈረንሳይ ካደረጉት ስምምነት የተለየ አይደለም።

ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በበኩላቸዉ መንግሥታቸዉ ከፍልስጤሞች ጋር በቀጥታ መደራደር እንደሚፈልግ አስታዉቀዉ የፓሪሱን ስብሰባ ዋጋ ቢስ አድርገዉታል።ኔታንያሁ ቀጥታ ድርድር የሚሉት እስራኤል በሐይል በያዘችዉ የፍልስጤም ግዛት የአይሁድ ሠፈራ መንደር ማስገንባቷን እንደቀጠለች ነዉ።ዲፕሎማት ፕሪሞር ግን

የኔታንያሁን መግለጫ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ይሉታል።«ይሕ ያዉ የፕሪፓጋንዳዉ አካል ነዉ።(ኔታንያሁ) ከፍልስጤሞች ጋር መደራደር አይፈልግም።ከፍልስጤሞች ጋር መነጋገር ነዉ-የሚፈልገዉ።ይሕን ደግሞ አድርጎታል።የሚፈልገዉ ከፍልስጤሞች ጋር መደረዳር፤ የጋራ መፍትሔ ወይም ማካካሻ መፈለግ ሳይሆን ፍልስጤሞችን ይሕን አድርጉ-አታድርጉ ማለት ነዉ።»

ለወትሮዉ የፍልስጤምና የእስራኤል ጉዳይ ለሌሎች አላስነካም የምትለዉ ዩናይትድ ስቴትስ «አትንኩብኝ» ዓይነት አቋሟን በፓሪሱ ስብሰባ ላይ አላንፀባረቀችም።እንዲያዉም በዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ ተወክላለች።ይሁንና ኬሪ የስብሰባዉ የአቋም መግለጫ ሲነበብ ጭንቅላታቸዉን ሽቅብ ቁልቁል ከመነቅነቅ ሌላ መግለጫዉ እዉን እንዲሆን ልዕለ-ሐያል ሐገራቸዉ መፈለግ-አለመፈለጓን አላረጋገጡም።

መግለጫዉ እስራኤል በ1967ቱ ጦርነት በሐይል ከያዘቻቸዉ የፍልስጤም ግዛቶች ሙሉ በሙሉ ለቅቃ እንድትወጣ ይጠይቃል።እስራኤላዉያን በ1967ቱ ጦርነት እየሩሳሌምን በሐይል የያዙበትን 39ኛ ዓመት ትናንት እየሩሳሌም ዉስጥ በሠልፍ፤ትርዒት፤ በድል አድራጊነት ስሜት አከበሩ።እየሩሳሌም በተለይ አሮጌዉ ክፍሏ እስራኤል በሐይል ከያዘቻቸዉ የፍልስጤም ግዛቶች አንዱ ነዉ።

ፍልስጤሞች ባንፃሩ ፈረንሳዮች የተዳፈነዉን ድርድር ለማንቀሳቀስ መወሰናቸዉን በደስታ ተቀብለዉታል።የደስታዉ ምክንያት ሁለት ነዉ።ባንድ በኩል-ላለፉት 25 ዓመታት የፍልስጤም እስራኤል ጉዳይ ለሌላ አላስነካም ያለችዉ ዩናይትድ ስቴትስ ፈረንሳይን የመሰለ ተፎካካሪ ሥለመጣባት ነዉ።የፍልስጤም ባለሥልጣናት ለእስራኤል ሁለንተናዊ ድጋፍ የምትሰጠዉ ዩናይትድ ስቴትስ ገለልተኛ ሸምጋይ አይደለችም እያሉ እንዳጉረመረሙ ነዉ።

ለዘመነ-ዘመናት የሚያልሙት ነፃነት በሐያላኑ ዘንድ መንፀባረቁ-ሁለት። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ እየሩሳሌምን፤ ጋዛንና ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻን የሚያስተዳድር ላለዉ ለፍልስጤም መንግሥት እዉቅና ሰጥቷል።እዉቅናዉ ገቢር ይሆናል ወይ ነዉ-ብሎ ጥያቄ ግን እስካሁንም፤አሁንም መልስ አላገኘም።ካሁን በኋላስ?

ነጋሽ መሐመድ

ሒሩት መለሠ

Audios and videos on the topic