እስራኤል፣ ዩጋንዳ እና የአፍሪቃውያን ስደተኞች እጣ | አፍሪቃ | DW | 14.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

እስራኤል፣ ዩጋንዳ እና የአፍሪቃውያን ስደተኞች እጣ

እስራኤል አፍሪቃውያን ስደተኞችን ወደ ዩጋንዳ ለመላክ  የጀመረችውን ጥረት አሁንም መቀጠሏን የመብት ተሟጋቾች እና የሕግ አውጪዎች አስታወቁ። እስራኤል ወደ ሀገሯ በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ በብዛት የኤርትራ እና የሱዳን የሆኑ 38,000 አፍሪቃውያን ስደተኞችን ለማስወጣት ትፈልጋለች።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:20

ዩጋንዳ ከእስራኤል የሚባረሩ አፍሪቃውያን ስደተኞችን ሳትቀበል አትቀርም ተባለ።

ባለፈው አሠርተ ዓመት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በግብፅ በኩል አድርገው እስራኤል የገቡት እነዚህ ስደተኞች በጊዚያዊ  ቪዛ ነው አሁን በዚያ የሚኖሩት። የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በስደተኞቹ ሰበብ ሀገራቸው ለገጠማት ውዝግብ ከተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት፣ ዩኤንኤችሲአር  ጋር በደረሰችው ስምምነት መፍትሔ ማግኘቷን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል። በስምምነቱ መሰረት፣ እስራኤል ከነዚህ ስደተኞች መካከል ግማሾቹን ወደ ምዕራባውያት ሀገራት ለማስፈር፣ የተቀሩት ደግሞ በዚያው በሀገሯ እንዲኖሩ ለመፍቀድ ነበር የተወሰነው።


« ጥሩ ስምምነት ነው። ይህን ስምምነት ከዩኤንኤችሲአር ኃላፊ ጋር በመድረሳችን በጣም ተደስቻለሁ። ችግሩን ለመቅረፍ ያስችለናል። የእስራኤልን ጥቅም በማስጠበቅ፣ ለደቡባዊ ቴል አቪብ እና ለአካባቢዋ ነዋሪዎች፣ እንዲሁም ፣ ወደ እስራኤል ለሚመጡት ሰዎች ችግር መልስ የሚሰጥ ጥሩ መፍትሔ ነው። »     

  የዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ ዊልያም ስፒንድለርም  ስምምነቱ  ለስደተኞቹ እና ለእስራኤል ራሷ ጥሩ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ ታስቦ እንደነበር ገልጸዋል።
«ስምምነቱ ጥሩ ነዉ ለነዚህ ሰወች መፍትሄ የሚሰጥና የእስራኤልን ፍላጎትም የሚያከብር ነዉ።ምክንያቱም ዓለም ዓቀፍ ግዴታዋን ለመወጣት ያስችላታል። ለዚህም የሌሎች ሀገራትን ድጋፍ ታገኛለች ።  ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብም  16 ሽህ የሚሆኑ ስደተኞችን በመቀበል ፣  መልሶ በማስፈር፣ የስራ ቪዛ በመስጠት፣ ቤተሰብን መልሶ በማገናኘት፣ በስፖንሰርሽፕ እና በሌሎች መንገዶች ከእስራኤል ጋር በመተባበር  ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። » 

ይሁንና፣ ኔታንያሁ በመንግሥታቸው ከተጣመረው የቀኝ ክንፍ  ቡድን ተቃውሞ ስለገጠማቸው ስምምነቱን ቀደም ሲል የተሰማውን መግለጫ ከሰጡ ከጥቂ ሰዓታት በኋላ ሰርዘዋል። በዚህም የመብት ተሟጋቾች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፣ ክትትል እና ውዝግብ በመሸሽ  በእስራኤል ይገኛሉ ያሏቸውን ስደተኞቹ እጣ ፈንታ ይበልጡን አወሳስበዋል። የእስራኤል መንግሥት ከተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት ጋር የደረሰውን ስምምነት ከሰረዘ በኋላ ከዩጋንዳ ጋር ስደተኞቹን እንድትቀበል የሚያስችል ስምምነት ለመድረስ አሁን ፊቱን ወደዚችው አፍሪቃዊት ሀገር በማዞር አንድ ልዑክ ወደዚያ መላኩን አስታውቋል። ቀደም ሲል  አፍሪቃውያን ስደተኞችን ለመውሰድ የገባችውን ቃል አጥፋለች ከምትላት ርዋንዳ ቀጥላ ሁለተኛዋ የእስራኤል ምርጫ የሆነችው ዩጋንዳ የእስራኤል ልዑክ ወደ ሀገሯ መሄዱን ሰሞኑን ስታስተባብል ከቆየች በኋላ ትናንት ለመጀመሪያ ጊዜ ስደተኞቹን በዚያ በማስፈሩ ጉዳይ ላይ ከእስራኤል ጋር ንግግር ላይ መሆኗን የዩጋንዳ የርዳታ፣ የአደጋ መከላከያ እና የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች ሚንስትር ሙሳ ኤክዌሩ  በይፋ  አስታውቀዋል። 

«የእስራኤል መንግሥት ዩጋንዳ  500 ኤርትራውያን እና ሱዳናውያን ስደተኞችን በሀገሯ እንዲሰፍሩ እንድትፈቅድ ጠይቋል። የዩጋንዳ መንግሥት እና እኔ የምመራው ሚንስቴር ይህንን ጥያቄ በአዎንታዊ መንገ።d3 ለመመለስ በማሰላሰል ላይ መሆናችንን በግልጽ ላስታውቅ እወዳለሁ። »

ሚንስትር ኤክዌሩ እንዳስረዱት፣ ተመላሾቹ ተገን ጠያቂዎች በዩጋንዳ የስደተኛነት አቋም ሊሰጣቸው ይችላል አይችልም የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ጠንካር ያለ ምርመራ ማለፍ ይኖርባቸዋል።  እስራኤል ከሀገሯ የምታባርራቸውን ስደተኞች ለመቀበል ፈቃደኛ ለሆኑ ሀገራት ገንዘብ ትከፍላለች በሚል የተሰማውን ዜና ግን ኤክዌሩ ሀሰት ስትል አስተባብለዋል።     
« እስካሁን ዩጋንዳ ውስጥ 1,4 ሚልዮን ስደተኞች አሉ። አንድም ሳንቲም አልተከፈልንም።   እንዲያውም፣ ካለን የተወሰነ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ስደተኞቹ ዩጋንዳን ሁለተኛ መኖሪያቸው እንዲያደርጉ እንሰራለን ። ስለዚህ ርምጃችን ከአንድም ክፍያ ጋር የተያያዘ አይደለም። የምናደርገው ከሰብዓዊነት በመነሳት ብቻ መሆኑ ግልጽ ነው። »

እንደ ዬክዌሩ ገለጻ፣ ስደተኞቹ ዩጋንዳ ሲደርሱ፣ በሀገሪቱ ላለው ዩኤንኤችሲአር ተላልፈው ይሰጣሉ ቢሉም፣ ዩኤንኤችሲአር ይመጣሉ ስለሚባሉት አፍሪቃውያን ስደተኞች የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ነው ያስታወቀው።


ከጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓም ወዲህ ወደ 4,000 የሚጠጉ ስደተኞች እስራኤል ባስተዋወቀችው መርሐ-ግብር ወደ ርዋንዳ እና ዩጋንዳ በፈቃደኝነት ተመልሰዋል። በመርሀግብሩ መሰረት፣ እያንዳንዱ ስደተኛ 3,500 ዶላር ተሰጥቷቸው እና የመጓጓዣ ወጪያቸው ተሸፍኖላቸዋል።  የሚሰጥ ሲሆን ይሸፍናል። ይሁንና፣ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን እንዲያባርሩ አሁንም ከቀኝ ክንፍ ቡድኖች ግፊት ተጠናክሮባቸዋል። 

ወደዩጋንዳና ርዋንዳ የተላኩ ስደተኞች በዚያ ይደረግላቸዋል የተባለውን ከለላ እንዳላገኙ ነው የመብት ተሟጋቾች የሚናገሩት። ወደ ዩጋንዳና ርዋንዳ ስለተመለሱ ስደተኞች እጣ ፈንታ እንዲያጣሩ ቡድኖች የላኩት የመባረር እጣ ያሰጋቸው ስደተኞች ርዳታ የሚያፈላልጉበት መስመር ህጋዊ ጽህፈት ቤት እና ሌሎች መሰል ድርጅቶች የስደተኞቹ ሁኔታ እጅግ አስከፊ መሆኑን ስደተኞች ርዳታ የሚያፈላልጉበት መስመር ህጋዊ ጽህፈት ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ ታል ሽታይነል ገልጸዋል።

«   ዩጋንዳ እና ርዋንዳ ለተመላሽ ስደተኞች አስተማማኝ የኑሮ ሁኔታ ለመስጠት የከእስራኤል ጋር የደረሱትን ስምምነት እንዳላሟሉ እናውቃለን። እንዲያውም፣ ባለን መረጃ መሰረት፣  ስደተኞቹ ዩጋንዳ እና ርዋንዳን ለቀው እንዲወጡ እና በሌሎች ሀገራት፣ በአውሮጳ ጭምር ስደት እንዲጠይቁ ተገደዋል። አንዳንዶች ወደ ሊቢያ እና እዚያ ወዳሉ የማሰቃያ ጣቢያዎች መድረሳቸው እና እጣ ፈንታቸው በጣም አሰቃቂ መሆኑን ሰምተናል። » 

እስራኤል ከዩኤንኤችሲአር ጋር የደረሰችውን ስምምነት ከሰረዘች በኋላ እንደገና ተግባራዊ የሆነው ስደተኞች በግዳጅ የማስወጣት እና የማይወጡትን ደግሞ በእስር የማቆየት እቅድ ግን በወቅቱ የመብት ተሟጋቾች በእስራኤል ላዕላይ ፍርድ ቤት ባቀረቡት ተቃውሞ የተነሳ ዓቢይ እክል ገጥሞታል። ላዕላዩ ፍርድ ቤት ተቃውሞ ያቀረቡት ወገኖች መከራከሪያ ሀሳባቸውን የሚያቀርቡበት ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸው በማዘዝ የእቅዱን ተግባራዊነት ለጊዜው አስቁሟል።

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic