እስራኤል የምታፈርሰው የፍልስጤማውያን ንብረት | ዓለም | DW | 07.03.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

እስራኤል የምታፈርሰው የፍልስጤማውያን ንብረት

የእስራኤል እና ፍልስጤማውያን ግጭትን በሚመለከት የአውሮፓ ህብረት ያወግዛል፣ የተባበሩት መንግሥታት በተደጋጋሚ ያስጠነቅቃል። እንደዛም ሆኖ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ የእስራኤል ጦር መስተዳድር ፍልስጤማውያን የሚኖሩበት አካባቢ ከመቼውም በላይ በርካታ ቤቶች፣ ጎጆዎች እና የውኃ ማጠራቀሚያዎችን አፍርሷል።

እስራኤል በኋይል በያዘችው በምዕራባዊ ዮርዳኖስ የአቡ ንዋር ቀበሌ ይገኛል። ይህ ፍልስጤማውያን የሚኖሩበት ክልል C የተባለ አባባቢ ሲሆን ሙሉ በሙሉም በእስራኤል አስተዳደር ስር ይገኛል። በዚህ አካባቢም ፍልስጤማውያን መገንባት ከፈለጉ ከእስራኤል ጦር መስተዳደር ፍቃድ ያስፈልጋቸዋል። መስተዳደሩ ግን ወሳኝ ለሆኑ መሰረተ ልማቶች እንኳን ፍቃድ አይሰጥም። ይልቁንስ ያለ ፍቃድ የተገነቡ ቤቶች እና ትምህርት ቤቶችን ያፈርሳል። ይህ ደግሞ 2016 ከገባ በኋላ ይበልጥ ተጠናክሯል ይላሉ። ዴቪድ ካርደን፤« በየካቲት ወር 2016 ለምሳሌ 200 መሰረተ ልማቶች ፈርሰዋል። መመዝገብ ከጀመርንበት ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ በአንድ ወር ጊዜ እንደዚህ ከፍተኛ ቁጥር ፈረሳ ሲካሄድ ይህ የመጀመሪያው ነው።»
ካርደን በእስራኤል ቁጥጥር ስር የሚገኙ አካባቢዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ርዳታ ክፍል ኃላፊ ናቸው። ካርደን በእስራኤል በኩል የሚሰጠውን ምላሽ ያውቃሉ፤ የዛኑ ያህል በአቡ ኑዋር የሚኖሩት 113 ቤተሰቦች እና ህፃናት በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይረዳሉ። ጀባል አል ባባ የሚባለው ተራራ ጫፍ የሚኖሩትም ሰዎች ሁኔታ ከአቡ ኑዋር የተሻለ አይደለም። አታራ ማዛራ የዚህ አካባቢ ነዋሪ ናቸው። ዶሮ ያረባሉ። የዶሮ ቤታቸው የቫቲካን መሬት ላይ ስለሰፈረ መፍረስ አያሰጋውም፤ ይሁንና ምንም ያህል ሳይርቅ የሚገኘው የመኖሪያ ጎጆዋቸው በእስራኤል መስተዳድር ስር ይገኛል ፤ እንዲፈርስ ትዕዛዝም ተላልፎበታል። አታራ ማዛራ ጎረቤት የሚገኘው ህንፃ እንዴት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት በእስራኤል ጦር እንደፈረሰ ያስታውሳሉ። « ህንፃው የአውሮፓ ህብረት የርዳታ ፕሮጀክት እንደነበር ሰዎቹ አይተዋል። የሚውለበለበው የአውሮፓ ህብረት ሰንደቅ ዓላማ ከዚያ ያተርፋቸው መስሏቸው ነበር። ነገር ግን የእስራኤልን ትራክተሮች ቤቶቻችንን እና ሰንደቅ ዓላማውን አወደሙት። »


ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ ምዕራብ ዮርዳኖስ ውስጥ የሚኖሩ 400 ፍልስጤማውያን ቤት አልባ ሆነዋል። በእስራኤል ጦር መስተዳድር ከሚፈርሱት 40 ከመቶው ድንኳን እና ጎጆ ቤቶች ናቸው። እንደ ተባበሩት መንግሥታት መረጃ ከፈረሱት 36 ከመቶ የሚሆኑት የነዋሪዎቹ መተዳደሪያ የሆኑት እንደ የከብት በረቶች፣ የውኃ ማጠራቀሚያዎች እና የመሳሰሉት ናቸው። የእስራኤል መስተዳድር በድርጊቱ አግባብነት ያምናል። ፍፁም ፍቃድ ማግኘት የተሰናቸው ፍልስጤሚያውያን ደግሞ ሁኔታውን ያወግዛሉ።« በተደጋጋሚ ፍቃድ ለማግኘት ሞክረናል። ነገር ግን እስራኤል ምንም ፍቃድ አትሰጥም። ይጫኑናል። መገንባት የምችልበት ድንጋይ አለኝ፤ ይሄው እዚህ ተቀምጧል።»
እያሉ አታራ ማዛራ ከጎጆዋቸው ፊት ለፊት የተከመረውን የብሎኬት ድንጋይ ይጠቁማሉ። እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከ 2010- 2014 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ፍልስጤማውያን የግንባታ ፍቃድ ለማግኘት 2000 የሚጠጉ ማመልከቻዎች አስገብተዋል። ከነዚህ ማመልከቻዎች ውስጥ ተቀባይነት ያገኙት ግን 33 ብቻ እንደሆኑ ዴቪድ ካርደን ከመንግሥታቱ መዝገብ እያነበቡ ያስረዳሉ« የአለም አቀፉ ማህበረሰብ እስራኤል የምዕራብ ዮርዳኖስ ክልል C ተቆጣጣሪ እንደሆነች እውቅና ሰጥቷል። ዋና ስራቸው የፍልስጤም ሲቪል ማህበረሰብን ደህንነት ማሟላት እና መሰረታዊ ፍላጎቶችን ማሟላት መሆን ነበረበት። ያ ማለት አንድ መሠረተ ልማት ሲወድም የሰብዓዊ መብት አንድ ህግ እንደተጣሰ ሊቆጠር ይገባል።
ቶርስትን ታይሽማን /ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic