እስልምና በጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 28.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

እስልምና በጀርመን

በጀርመን ሀገር የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ልክ እንደ ክርስቲያኖችና እና ይሁዲዎች እኩል እውቅና እንዲያገኙ ከብዙ ዓመታት ወዲህ ትግል አካሂደዋል። ይኸው ትግላቸው አሁን የተሳካ ውጤት አስኝቶላቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:53
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:53 ደቂቃ

እስልምና በጀርመን

ጀርመን ሀገር ውስጥ ወደ አራት ሚልዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች ይኖራሉ። የሀይማኖት ነፃነታቸውየተጠበቀላቸው ሲሆን፣ ብሎም መስጊዶችን በነፃ መገንባት እና የሙስሊም በዓላትን አንዳችም ገደብ ሳያርፍባቸው ማክበር ይችላሉ። በብዙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የእስልምና እምነት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት፣ በአምስት የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችም ውስጥ ኢማም ለመሆን ለሚፈልጉ ሰዎች ሥልጠና ይሰጣል። ይህም ሙስሊሞችን በጀርመን ህብረተሰብ ውስጥ ለማዋኃድ በተጀመረው ስራ ላይ ትልቅ መሻሻል መመዝገቡን ያረጋግጣል። ያም ቢሆን ግን፣ በጀርመን የእስልምና እምነት ተከታዮች ከክርስቲያኖች እና ከይሁዲዎች እኩል እንደማይታዩ ከሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ፣ «ኤስ ፔ ዴ» ጋ ቅርበት ያለው የፍሪድሪሽ ኤበርት ተቋም ከጥቂት ጊዜ በፊት ያወጣው ጥናት ውጤት አረጋግጦዋል። ጥናቱን ካካሄዱት መካከል አንዷ የሆኑት የእስልምና እምነት ተመራማሪ ራይም ሽፒልሀውስ እንደሚገምቱት፣ እስልምና ከክርስትና እና ከይሁዳዊነት ጋ በአንድ ደረጃ መታየት እስኪጀምር ድረስ ገና ብዙ መሰራት ይኖርበታል።

« እኛ በተጨባጭ እንደተመለከትነው እውቅና ማግኘት ማለት አንድ ሰው እምነቱን በነፃ መከተል ሲችል ነው። በሌላ አነጋገር እውቅና ማግኘት ለሀይማኖት ነፃነት አስፈላጊ ነው። ለእምነትም አስፈላጊውን አክብሮት የመስጠት ሁኔታንም ያስገኛል። ሕጋዊ እውቅና መስጠት ማለት ደግሞ በዚች ሀገር ውስጥ የእስልምና እምነት ተከታዮች መኖራቸውን መቀበል ማለት ነው። »

ሙስሊሞች እኩል እውቅና ባለማግኘታቸው የተለያዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሙዋቸው የሕግ ባለሙያው ማርቲን ኸርሶግ ገልጸዋል። ከነዚህ ችግሮች አንዱ የቀብር ሥነ ሥርዓትን ይመለከታል።

« የእሥልምና ሀይማኖት በሚያዘው መሠረት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው እንዲከናወን ሲሉ ብዙ ሙስሊሞች አስከሬናቸውን ወደ ትውልድ ሀገራቸው ያስልካሉ። ይህን የሚያደርጉትም በዚያ ወጪው ዝቅተኛ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ እዚህ ጀርመን ሀገር ውስጥ በቀብር ወቅት ተግባራዊ ሊሆኑ የማይችሉ ሥርዓቶች በመኖራቸውም። »

ይሁንና፣ ካለፉት ዓመታት ወዲህ ይህን በተመለከተ አንዳንድ ለውጦች የተደረጉ ሲሆን፣ ከግማሽ የሚበልጡ የጀርመን ፌዴራዊ ክፍላተ ሀገር ሙስሊሞች በሥርዓተ ቀብር ወቅት ከእምነታቸው ውጭ በመሄድ፣ የሬሳ ሳጥን መጠቀም እንደማይገደዱ፣ እንዲሁም፣ ማዘጋጃ ቤቶች በሚያስተዳድሩዋቸው ቦታዎች ከተቀበሩ የአስከሬኑ አቀማመጥ ወደ ሜካ አቅጣጫ እንዲሆን መፈቀዱን ማርቲን ኸርሶግ አመልክተዋል። ይሁንና፣ የሙስሊሙ ማህበረ ሰብ ራሱ የመቃብር ቦታ ማስተዳድር አይችልም። ማዘጋጃ ቤቶች ለአንድ ማህበረ ሰብ ይህን ፈቃድ የሚሰጡት ብዙ ሕዝብ የሚያስተዳድሩ ተወካዮች ወይም ድርጅቶች ሲኖሩት ነው። በወቅቱ ይህን ያሟላ አንድም የሙስሊሞች ድርጅት እንደሌለ ኸርሶግ አስረድተዋል።

የጀርመን የእስልምና እምነት ተከታዮች ግን ይህን እንደ አሳማኝ ምክንያት አልተቀበሉትም። ዋናው ምክንያት እስልምና በጀርመን ህገር እንደ ክርስትና እና ይሁዳዊነት በሀገር አቀፍ ደረጃ እኩል እውቅና አለማግኘቱ ነው ይላሉ የእስልምና እምነት ተመራማሪ ራይም ሽፒልሀውስ። ከግማሽ በሚበልጡት የጀርመን ፌዴራዊ ክፍላተ ሀገር የተወሰዱ የማስተካካያ ርምጃዎች ይበልጥ ሊሻሻሉ እና በመላ ጀርመን ውስጥ ሊስፋፉ እንደሚገባ ነው ሽፒልሀውስ ያሳሰቡት።

ቤቲና ማርክስ

አርያም ተክሌ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic