እሳተ ገሞራና የምድር ሙቀት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 26.02.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

እሳተ ገሞራና የምድር ሙቀት

ባለንበት ምዕተ ዓመት የምድራችን የሙቀት መጠን ከ 2 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ እንዳያሻቅብ ሥጋት መኖሩ ቢታወቅም፤ ባንዳንድ የተፈጥሮ ክሥተቶች ሳቢያ ክፍተት ሊፈጠር ሚችልበትን ፤ ባጭሩ የሙቀቱ መጠን የሚቀነስበትን ሁኔታ ፣ አነስተኛ የእሳተ ገሞራ

ፍንዳታዎች ፍንጭ እየሰጡ ነው። እ ጎ አ ከ 2000 ዓ ም ወዲህ ፣ ማለት ባለፉት 14 ዓመታት ገደማ ቢያንስ 17 እሳተ ገሞራዎች የፈነዱ ሲሆን፤ ፣የኢንዲኔሺያው ሜራፒ፣ የአላስካው ካሳቶቺ፣ የኢትዮጵያው አርታሌና ሌሎች ጭምር ከተፉት እሳተ ገሞራ፤ የሚፈነጥቀው ድኝ፤ እስከምን ድረስ የፀሐይን ብርሃንና ሙቀት እንደሚገድብ ፣ የአየር ንብረት ጉዳይ ተመራማሪ ጠበብት እምብዛም ሰፋ ያለ ትኩረት አላደረጉበትም ነበር።

ምድራችን ፣ ከፀሐይ በሚፈነጥቀው፤ የፀሐይ ነፋስ በሚሰኘው፤ የአቶም ፍንጣቂ እንዳትጠቃ በተለይ ከሰሜንና ደቡብ ዋልታዎቿ መግነጢሳዊ ጣቢያ በተመሳሳይ ሁኔታ ወደ ኅዋ መልሶ የሚያንጸባርቀው የጨረር ተከላካይ ኃይል ነው ዘብ ቆሞ የሚጠብቃት። ከባቢ አየሯም ለሰውና እንስሳት እንዲሁም እጽዋት እጅግ አደገኛ ከሆኑት ፣ «ኮስሚክ» ም ሆነ «ጋማ » ጨረር ከሚሰኙት በመታደግ የራሱ የሆነ ድርሻ አለው።

ፀሐይና ከባቢ አየር ፣ ለምድራችን የአየር ንብረትም ሆነ የአየር ጠባይ ዓይነት ሰፊ ድርሻ ያላቸው መሆኑ የታመነ ነው። የተቃጠለ አየር ልቀት መብዛትና ከከባቢ አየር ጋር መቀላቀል ፤ የምድራችን የሙቀት መጠን ከሚገባው በላይ እንዲጨምር ያደርጋል በማለት የተፈጥሮ አካባቢ ነክ ሊቃውንት በተደጋጋሚ ከማስጠንቀቅ የቦዘኑበት ጊዜ የለም።

በሌላ በኩል ከዚሁ የተቃጠለ አየር ልቀት ጎን ለጎን፤ የእሳተ ገሞራዎች ጢስ የተፈራውን የምድር ሙቀት መጨመር የሚያርቅ ስለመሆኑ በመነገር ላይ ነው። እንዴት የሚለውን ከማንሳታችን በፊት ፤ በዓለም ዙሪያ ምን ያህል የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ እንደሚያጋጥም እንመልከት--።

ምድራችን ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ ፣ ምናልባት በሚሊዮን የሚቆጠር የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ አጋጥሞ ይሆናል። ባለፉት 10 ሺ ዓመታት የሆነው ሆኖ፣ ከየብስ የሚፈነዱ እቶናቸው ያልበረደ 1,500 ያህል እሳተ ገሞራዎች ይገኛሉ። ከእነዚህ በቁጥር የሚልቁትን ከውቅያኖስ ወለልም ሆነ በውቅያኖስ ከተሸፈኑ ተራሮች የሚፈነዱትን ለማወቅ ይበልጥ አስቸጋሪ ነው። በአሁኑ ዘመን ፣ 600 ያህል ከዚህ ቀደም በታሪክ የተመዘገበላቸውና ዛሬም የሚያሠጉ እንዲሁም ዘመን እየጠበቁ የሚፈነዱ አሉ። ከ 50 እስከ 60 የሚሆኑት አሁንም ያለማቋረጥ በያመቱ እሳት የሚተፉ ናቸው። በአማካይ፣ 20 ያህል እሳተ ገሞራዎች ነበልባል ያላቸው ናቸው።

በተለይም ፤ የእሳት ቀለበት በተሰኘው የዓለም ክፍል በሚገኙት፣ ኢንዶኔሺያ ፤ ፓፑዋ ኒው ጊኒ፤ ፊሊፒንስና ጃፓን ፣ እንዲሁም ማዕከላዊ አሜሪካና ሜክሲኮ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው። በቅርቡ ፤ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከፈነዱት መካከል 1731 ሜትር ከፍታ ካለው ኮረብታ እሳት የተፋው በጃባ ደሴት ፤ ኢንዶኔሺያ የሚገኘው ከሉድ የተባለው እሳተ ገሞራ ነው። ያለማቋረጥ እሳት ከሚተፉት መካከል፤ ቀደም ሲል ያወሳነው፤ የኢትዮጵያው አርታሌ፣ በኮንጎ ዴሞካራቲክ ሪፓብሊክ የሚገኘው ንያራጎንጎ የታንዛንያው ኦል ዶይንዮ ሌንጋይ፤ በሲሲሊ ደሴት የሚገኘው የኢጣልያው ኤትና፣ ፣ በህንድ ውቅያኖስ የሚገኙት «ኸርድ» ና «ባረን አይላንድ» እንዲሁም የጃፓኑ ሱዋኖስጂማ ይጠቀሳሉ።

እሳተ ጎሞራ በሰውና እንስሳት ላይ ብርቱ አደጋ እንደሚያስከትል የታወቀ ቢሆንም፤ የሚተፋው የተቃጠለ አፍርና የላመ ድናጋይ ጥሩ የአፈር ማዳበሪያ መሆኑ አይታበልም። ዓመዱ ፤ ከሰው-ሠራሹ ስሚንቶ በበለጠ ሁኔታ፤ ለግንባታ ልዩ ጥንካሬ እንዳለውም ነው የሚነገረው። በ NATURE መጽሔት የመልክዓ ምድር ሳይንስ ጥናታዊ ውጤት እንደሚጠቁመው ከሆነ ደግሞ፤ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ የምድራችንን የግለት መጨመር

በመጠኑም ቢሆን በመግታት ፤ አስተዋጽዖ በማድረግ ላይ ነው። በተለይ በሰኔ ወር 1983 ዓ ም፤ በፊሊፒንስ

ከ ሉዞን ደሴት የፈነዳው ፒናቱቦ እሳተ ገሞራ ፣ ለተጠቀሰው መላ ምት ማረጋገጫ መሆኑም ነው የተጠቀሰው። የእሳተ ገሞራ ጢስ ፤ ከዚህም ጋር የድኝ ፍንጣቂ ፤ የፀሐይን ብርሃን አንጸባርቆ በመመለስ ታችኛውን ከባቢ አየር በመጠኑም ቢሆን እንዲቀዘቅዝ ያደርጋል ነው የተባለው። ይሁን እንጂ ፤ ምንም እንኳ የአሳተ ገሞራ ፍንዳታ በተደጋጋሚ ያጋጥም እንጂ ፣ እስካሁን የፒናቱቦን ያህል ምልክት የሰጠ አላጋጠመምና ፣ የምድራችንን ግለት ይገታል ብሎ ፈጽሞ መዘናጋት እንደማያሻ የሚያስጠነቅቁ ጠበብትም

አሉ። የምድራችን ግለት ገደብ እንዲደረግለት ከሚፈለገው የ 2 ዲግሪ ጭማሪ በበለጠ ሁኔታ ሊያሻቅብ የሚችልበት አደጋ ስለመኖሩ ፣ ጠበብት፣ በመሠረተ ሐሳብ ይስማሙበታል።

የምድራችን ተፈጥሮና ባሕርይ

ሰማያዊ ፕላኔት በመባል የምትታወቀው የአኛዋ ምድር የ 4,6 ቢሊዮን ዓመት ገደማ ዕድሜ ያላት ስትሆን፤ ሰማያዊ ፕላኔት የምትባለውም ፣ አሁን ባላት የውጭ ገጽዋ ሳቢያ ነው። ውስጧ ግን ቀለሙ ሌላ ነው። ምድራችን የእሳት ሉል እንደነበረች ነው የሚነገረው። አሁንም ፈጽሞ አልበረደችም፤ ለዚህም ፣ በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው የሚፈነዱት እሳተ ገሞራዎች ምልክቶች ናቸው። የምድራችን ውሳጣዊ አካል ፣ ከ 7,000 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የማያንስ ሙቀት ያለው የቀለጠ የብረት ውቅያኖስ የሚንቦጫቦጭባት መሆኑም ነው በከርሰ ምርምር ተማራማሪዎች የሚነገረው። ክብደቷ 5,972 ሴክስቲሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሆን፤ በሰቋ ዙሪያ ፣ ወርዷ ፣ 40,075 ኪሎሜትር ነው። ከሞላ ጎደል ¾ኛው አካልዋ በውሃ የተሸፈነ መሆኑ የታወቀ ነው።

29 ከመቶው ደግሞ ቋጥኝ ነው። የላይኛው የየብስ ክፍል፤ 30 ኪሎሜትር ጥልቀት ያለው ሲሆን፤ ከዚያ 3,600 ኪሎሜትር እርከን ወዳለው ክፍል ቢወረድ፤ ፈሳሽነት ያለው የከርሰ ምድር ንጣፍ ይሆናል የሚገኘው። ከዚያም 2,400 ኪሎሜትር ዲካ ድረስ ጣጣሩ የፕላኔታችን አካል ይገኛል። ከላይ ጫፍ፤ እስከ መኻል፣ እምድራችን ልብ ድረስ 3 እርከኖች አሉ ማለት ነው። የምድራችን ውስጣዊ አካል ምን እንደሚመስል መረጃ የሚያቀርቡ በዓለም ዙሪያ በየጊዜው የሚፈነዱ እሳተ ገሞራዎች ናቸው። የእሳተ ገሞራ ጠበብት እንደሚያስረዱት ከ 109 ንጥረ ነገሮች(ኬሚካልስ ) መካከል 93 ቱ የመሬትን የብሳዊ አካል በመገንባቱ ረገድ አስተዋጽዖ ያደረጉ ናቸው።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች