1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

“እርዳታ ካገኘን 2 ዓመት ሆነን” በ2013 ከትግራይ የተፈናቀሉ ወገኖች

ዓርብ፣ ኅዳር 6 2017

በ2013 ዓም የሰሜኑ ጦርነት ወቅት ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማና አካባቢው የሚገኙ ተፈናቃዮች “እርዳታ ካገኘን 2 ዓመት ሆኖናል” አሉ፣ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በበኩሉ የእርዳታ አቅርቦት መዘግየት ቢኖርም “2 ዓመት የተባለው ግን የተጋነነ ስሞታ ነው” ብሏል።

https://p.dw.com/p/4n3aK
Äthiopien - IDPs in Debark, Amhara Region
ምስል Debark Woreda Food Security/Disaster prevention Office

“እርዳታ ካገኘን 2 ዓመት ሆነን” በ2013 ከትግራይ የተፈናቀሉ ወገኖች

በ2013 ዓ ም በህዝባዊ ወያን ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት መካክል በነበረው ጦርነት ከትግራይ ክልል የተልያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በሰሜን ጎንደር ዞን ደብርቅና አካባቢው የሚገኙ ተፈናቃዮች ለተራዘመና ለከፋ ማህበራዊ ቀውስ መዳረጋቸውን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፣ አንዳንዶቹ እስክ ልመና መውጣታቸውን ገልጠዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡን ተፈናቃዮች መካከል ለ20 ዓመታት በሽሬ ከተማ እንደኖሩ የነገሩን 10 አለቃ አማረ ሙሉ ለሁለት ዓመታት እርዳታ አላገኙም፣ መኖሪያና ማረፊያም የላቸውም፣ ወደ ቀደመ ቀያቸውም መመለስ ይፈልጋሉ።

“እርዳታ ከተቋረጠብን ሀዳር 2ኛ ዓመታችን ነው።”

“ እርዳታ ከተቋረጠብን ሀዳር 2ኛ ዓመታችን ነው።” ብዙዎቹ የሚያድሩት በየበረንዳው፣ በየቤተክርስቲያኑና በየትምህርት ቤቱ እንደሆነ ገልጠዋል። የቀን ሥራ ሰርቶ ለመኖርም ከባድ እነደሆነ የሚናገሩት 10 አለቃ አማረ መንግሥት እርዳታ የማይሰጠን ከሆን ዋስትና ወስዶ ወደ ቀደመ ቀያችን ይመልሰን ነው ያሉት።

«ከእርዳታ አውጡን» የአማራ ክልል ተፈናቃዮች
ከሽራሮ እንደመጡ የገለፁልን ወ/ሮ ሙሉንሽ ፋንታ የተባሉ ሌላ ተፈናቃይ ቀደም ሲል እርዳታ ያገኙ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ግን እርዳታው ከቆመ ሁለት ዓመት እየሞላው እንደሆነ አመልክተዋል። ቤት ተከራይቶ ለመኖርም የገንዘብ እጥረት በመኖሩ በጣም በችግር ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል። “መንግሥት ወይ በቂ እርዳታ ይስጠን አሊያ ወደነበርንበት ይመልሰን” ሲሉ ጠይቀዋል። ሁኔታው ልመና እንዲወጡ እንዳስገደዳቸው እኚሁ አስተያየት ሰጪ አብራርተዋል።

“እርዳታ በመቋርጡ ለልመና ወጥተናል” ተፈናቃዮች

ወ/ሮ ዘውድነሽ ገብሬ የተባሉ ተፈናቃይ እንዳሉት ደግሞ፣ ባለባቸው ችግር ምክንያት ባህርዳር ህክምና ላይ ያለውን ባለቤታቸውን እንኳ መጠየቅ አልቻሉም፣ ያሏቸውን 3 ልጆች እየለመኑ እንደሚያስተዳድሩ ሀዘን በተጫነው ስሜት ነው የነገሩን።
“መድረሻና መጠለያ አጣን” ያሉት እኚህ ተፈናቃይ፣ ህፃናትና በሽተኞች በየቤታችው እያለቀሱ እንድሆኑ አስረድተዋል። “በሽተኛ ነኝ” ያሉት እኚህ እናት ተዳክመው በአልጋ ላይ ላሉት ከተማ ወጥተው ለምነው የሚያገኙትን እንደሚመግቡ አስረድተዋል።

እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎች
እርዳታ የጫኑ ተሸከርካሪዎችምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሠላምይሁን ሙላት በተፈናቃዮች የቀረበውን አቤቱታ በማስመልከት በሰጡት ምላሽ “ሁለት ዓመት እርዳታ አላገኘንም” የሚለው ክስ ስህተት ነው ብለዋል፣ በእርግጥ የዘግየ እርዳታ መኖሩን አምነዋል፣ በዞኑ 39 ሺህ ያክል ተፈናቃይ በሁሉም የዞኑ ወረዳዎች እንደሚገኝ ያመለከቱት አቶ ሠላምይሁን፣ ከ98 ከመቶ በላይ የሚሆኑት በሰሜኑ በነበረው ጦርነት ከትግራይ የተፈናቅሉ እንደሆኑ ነው ያስረዱት።

ተፈናቃዮች ያቀረቡት የእርዳታ ጥሪ

“እርዳታ ለማድረስ እየተሰራ ነው” የሰሜን ጎንደር ዞን አደጋ መከላከል ጽ/ቤት

እርዳታም ወደ አካባቢው እንዲመጣ ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋሰትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ደብዳቤ መፃፉንና ምላሽ እየጠበቁ እንደሆነ ተናግረዋል።
ጉዳዩን በተመለከት ተጨማሪ አስተያየት ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋሰትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን ለማካተት ዋና ኮሚሽነሩን ጨምሮ ለሚመለከታቸው ኃላፊዎች ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ማንሳት አልቻሉም፣ ይሁንእጂ የማስተባበሪያ ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል የተፈናቃዮችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ጥናት እየተካሄድ እንደሆን በቅርቡ ገልፀው ነበር።

“ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ጥናት እየተካሄደ ነው” የአማራ ክልል

ኮሚሽነሩ፣ “ጥናት ተጠንቷል፣ የተፈናቃዮቹ አጠቃላይ አማራጮች ምንድን ናቸው? የሚለው መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ ተጠንቷል፣ ጥናቱ ሰሞኑን ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ባሉበት ቀርቦ  ወደ ተግባር ይገባል” ብለዋል።

ደቡብ ወሎ መጠለያ ካምፕ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሮሮ
በአማራ ክልል በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት ከ2 ሚሊዮን በላይ የእለት እርዳታ ፈላጊ ወገኖች መኖራችውን ከአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች፣ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያሳያል።

ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ