1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እምቦጭ ለጣና ሐይቅ የህልውና ሥጋት ሆኗል

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 9 2017

“ የወራት ጉዳይ ካልሆን በስተቀር የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች የጣና ሐይቅን አያዩም፣ ምክንያቱም የእምቦጭ አረም ከተማዋ ጫፍ ደርሷል” የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሐ አካላት ጥበቃና ልማት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ

https://p.dw.com/p/4lz4b
Äthiopien | Universität Gondar | Forschung zur Verwendung von „Emboch“ für Biogas und Düngemittel
ምስል Dr. Dessie Tibebe/Gondar University

“የወራት ጉዳይ ካልሆን በስተቀር የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች የጣና ሐይቅን አያዩም“


በጣና ሐይቅ ላይ የተንሰራፋውን እምቦጭ አረምማስወገድ የሚያስችል የተባለለትና አረሙን ወደ ግብርና ግብዓት መቀየር የሚያስችል ምርምር ወደ ትግበራ ሊያስገባ እንደሆነ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ። በሌላ በኩል አረሙ ከምንጊዜውም በላይ መስፋፋቱን አርሶአደሮች እየገለፁ ነው።

የእምቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ በስፋት መታየት የጀመረው በ2004 ዓ ም አካባቢ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜዎች ሲገለጽ ቆይቷል። አረሙን ለማስወገድም በማሽንና በሰው ጉልበት በዘመቻ መልክ ጭምር ሲሰራ ቢቆይም አረሙ  ከመቀነስ ይልቅ በየጊዜው መጠኑን እያሰፋ እንደሚገኝ በሐይቁ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮች ይናገራሉ።

የእምቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ መስፋፋት
ሰሞኑን አስተያየት የሰጡን አርሶ አደሮችም “በዚህ ዓመት አረሙ ከምንጊዜውም በላይ ጨምሯል” ነው ያሉት።
ከአርሶ አደሮቹ አንዱ እንደገለጹልን አረሙ ከአለፈው ዓመት በዚህ ዓመት በማይታመን ሁኔታ  ጨምሯል ብለዋል። የውሐው አካል ተወሯል፣ መፍትሔ ካልተገኘ የሐይቁ ህልውና ጥያቄ ውስጥ እንደሚገባ ነው ያስረዱት።
ሌላው አስተያየት ሰጪ አርሶአደርም፣ “... አረሙ በጣም በጣም ጨምሯል፣ እየተስፋፋ ነው” ሲሉ ነው አስተያየታቸውን የሰጡን።

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አረሙን ወደ ግብርና ግብዓትነት መቀየር የሚያስችል ምርምር እያካሄደ መሆኑን
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አረሙን ወደ ግብርና ግብዓትነት መቀየር የሚያስችል ምርምር እያካሄደ መሆኑንምስል Dr. Dessie Tibebe/Gondar University

የአረሙ መስፋፋት ሐይቁን ሙሉ በሙሉ ሊሸፍነው ይችላል
የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሐ አካላት ጥበቃና ልማት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ በበኩላችው በክልሉ ያለው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ተጨምሮ አሁን ያለው አረሙን በማሽንና በሰው ኃይል የማስወገድ ሥራ በመቀዛቀዙ አረሙ ባሕር ዳር ከተማ ጫፍ ደርሷል ብለዋል። ከጥቂት ጊዜ በኋል የከተማዋ ነዋሪዎች ሐይቁን የማየት እድል አንደማይኖራቸው ገልጠዋል። እምቦጭ ከዚህ ቀደም ባልነበረባቸው የሐይቁ ዳርቻዎችና መሐል እየተሰራጨ እንደሆነም አክለዋል።
“ የወራት ጉዳይ ካልሆን በስተቀርየባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች የጣና ሐይቅን አያዩም፣ ምክንያቱም የእምቦጭ አረም ከተማዋ ጫፍ ደርሷል” ብለዋል። አረሙ በአሁኑ ሰዓት ከምሰራቅ ወደ ምዕራብ በማስፋት ወደ ቁንዝላ፣ ዘጌና ባሕርዳር እየተስፋፋ እንደሆን ነው ያሰረዱት ።

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እምቦጭን ለግብርና ግብዓትነት ለመጠቅም ምርምር እያካሄደ ነው
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እምቦጭን ለግብርና ግብዓትነት ለመጠቅም ምርምር እያካሄደ ነውምስል Dr. Dessie Tibebe/Gondar University

ጎንደር ዩኒቨርሲቲ እምቦጭን ለግብርና ግብዓትነት ለመጠቅም ምርምር እያካሄደ ነው
 የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አረሙን ወደ ግብርና ግብዓትነት መቀየር የሚያስችል ምርምር እያካሄደ መሆኑን ለዶይቼ ቬሌ አመልክቷል። በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ቀመር ሳይንስ ኮሌጀ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ደሴ ጥበበ እንዳሉት አረሙን ለግብርና ግበዓትነትና ለባዮ ጋዝ አገልግሎት ማዋል የሚያስችሉ የቤተ ሙከራ ምርምሮች ተጥናቅቀው ወደ መስክ ምርምር ተገብቷል።
ዩኒቨርሲቲው እንደ ጎርጎሮሳዊያን አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ የተለያዩ ምርምሮችን ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው፣ አሁንም አረሙን ለማዳበሪያ፣ ለአማራጭ ኃይል /Bio gas/ ለአሲዳማ አፈር ማከሚያነትና ለሌሎች ግብዓቶችም ለማዋል ተስፋ ያለው ምርምር እየተካሄደ መሆኑም ተመራማሪው ተናግረዋል።
ከጣና ሐይቅና ሌሎች የውሐ አካላት ጥበቃና ልማት ተቋምና ከሌሎችም አካላት አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር  እየተደረገላቸው መሆኑንም ዶ/ር ደሴ አመልክተዋል።

የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሐ አካላት ጥበቃና ልማት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አያሌው ወንዴ እየተደረገ ላለው ምርምር እውቅና እንዳላቸው ገልጥዋል። ሥራውም ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት እንዳላቸውና መንግስትም ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የእምቦጭ አረም በውሀ ብዘሀ ህይዎት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስና በሂደትም የውሀ አካላት እንዲጥፉ የሚያደርግ የውሀ ላይ ተንሳፋፊ አረም መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ። የእምቦጭ አረም በጣና ሐይቅ አዋሳኝ በሆኑ ሶስት ዞኖች፣ ዘጠኝ ወረዳዎችና ከ35 በላይ ቀበሌዎች በ4,300 ሄክታር የሐይቁ ክፍል ላይ መስፋፋቱን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር