እልባት ያላገኘው የድንበር ውዝግብ | የጋዜጦች አምድ | DW | 13.12.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

የጋዜጦች አምድ

እልባት ያላገኘው የድንበር ውዝግብ

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ከግንቦት 1990 እስከ ሰኔ 1992 ዓም ድረስ ለተካሄደው አስከፊው የድንበር ጦርነት መንሥዔ ለሆነው አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ርዝመት ላለው አከራካሪው የጋራ ድንበር ውዝግብ መፍትሔ ይሆናል የተባለው ውሳኔ የተደረሰው ሚያዝያ 1994 ዓም ነበር። ሁለቱ ሀገሮች በጋራ ድንበራቸው ባሉ ግዛቶች የባለቤትነት ጥያቄ የተፋለሙበትን የብዙ ሺህ ሕዝብ ሕይወት አጥፍቶ በሚልዮን የሚቆጠሩ ከቤት ንብረታቸው ያፈናቀለው ደም አፋሳሽ ጦርነት መጀመሪያ ሰኔ 1992 ዓም በተፈራረሙት የተኩስ አቁም ደምብ፡ በኋላም ታህሳስ 1992 ዓም በአልዥየ በደረሱት የሰላም ውል አማካይነት ነበር ያበቁት። በሰላሙ ውል መሠረት፡ አንድ አምስት አባላት የሚኖሩት ነፃ ኮሚስዮን እንዲቋቋምና ለጦርነቱ መንሥዔ የሆነውን አወዛጋቢውን የድንበር ጥያቄ አጣርቶ ውሳኔ እንዲያሳልፍ፡ እንዲሁም ኢትዮጵያና ኤርትራ ኮሚስዮኑ የሚሰጠውን ውሳኔ እንደመጨረሻና እንደ አሣሪ ሊቀበሉት ነበር የተስማሙት። ኮሚስዮኑ ውሳኔውን እስኪሰጥና የድንበሩ ማካለል ተግባር እስኪጠናቀቅ ድረስ አራት ሺህ ሁለት መቶ ወታደሮች የሚያሰልፍ አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ጓድ የሁለቱን ተቀናቃኝ ሀገሮች ጦር ኃይላት በሚለያየው በኤርትራ ግዛት ውስጥ ሀያ አምስት ኪሎ ሜትር ዘልቆ በገባው የደህንነት ቀጠና እንዲሠማራና የተኩስ አቁሙ ደምብ መከበሩን እንዲቆጣጠርም ነው የተወሰነው። የድንበሩ ኮሚስዮን ኢትዮጵያና ኤርትራ ያቀረቡለትን ማስረጃዎችና ወደ ሁለት መቶ የሚጠጉ ካርታዎች ካጠና በኋላ ሚያዝያ 1994 ዓም ብያኔ ቢያሳልፍም፡ ከዚያን ጊዜ ወዲህ አከራካሪውን ድንበር በመከለሉ ረገድ እስካሁን አንዳችም ሂደት አልተንቀሳቀሰም። የኢትዮ ኤርትራን ድንበር ጉዳይ የተመለከተው ኮሚስዮን በሰጠው ውሳኔ መሠረት፡ አሁንም በኢትዮጵያ ቁጥጥር ሥር የምትገኘዋ የባድመ ከተማ ከኤርትራ ግዛት ጋር እንድትጠቃለል ነው የበየነው። ይሁንና፡ ኢትዮጵያ የኮሚስዮኑ ብይን ሕጋዊና ትክክለኛ አይደለም በሚል ውድቅ ካደረገች ወዲህ፡ በአልዥየ የተደረሰው የሰላም ውል ትልቅ እክል ተደቅኖበታል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ሀገራቸው ኮሚስዮኑ ባድመን ከኤርትራ ግዛት ጋር ትጠቃለል ያለበት ብይኑ እንደማትቀበል ባለፈው መስከረም ወር ለፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ በማስታወቅ፡ ምክር ቤቱ ለዚሁ ጉዳይ ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ጥያቄ አቅርበዋል። እርግጥ፡ ምክር ቤቱ የኮሚስዮ ብይን አሣሪና ይግባኝ የማይባልበት ነው በሚል የኢትዮጵያን ጥያቄ በፍፁም እንደማይቀበል ግልፅ አድርጎ ነበር። የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት የተ መ ድ በያመቱ ለሰላም አስከባሪው ጓድ ከአንድ መቶ ሀምሣ ሚልዮን ዶላር በላይ የሚያወጣበትን ተልዕኮ ባፋጣኝ ማብቃት ነው የሚፈልገው። ይሁን እንጂ፡ አንዳንድ ዲፕሎማቶች ካለፉት ጥቂት ሣምንታት ወዲህ እንዳመለከቱት፡ የተ መ ድ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን፡ ኢትዮጵያና ኤርትራ የደረሱት የሰላም ውል የተጓጎለበትን ሁኔታ ለማብቃት የሚቻልበትን መንገድ እንዲያፈላልጉ በፀረ ሰው ፈንጂ ምርትና ዝውውር ላይ ዓለም አቀፍ ዕገዳ እንዲደረግ ሰፊ ድርሻ ያበረከቱትን የቀድሞውን የካናዳ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሎይድ አክስልን ልዩ ልዑካቸው አድርገው ሳይሠይሙ አይቀሩም። ኤርትራም በበኩልዋ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ ኢትዮጵያ የድንበሩ ኮሚስዮን ውሳኔን እንድትቀበልና የድንበር ማካለሉን ተግባር ያስተጓጎለችበትን ድርጊት እንድታበቃ ግፊቱን እንዲያሳርፍ ጥረት ጀምራለች። ለድንበሩ ውዝግብ የተሰጠው ብይን ተግባራዊነት የተሰናከለበትን ሂደት ለማስወገድ ከተ መ ድ ጎን ዩኤስ አሜሪካም ጥረት አካሂዳለች። ሁለት ጊዜ የተላለፈውና ባለፈው ጥቅምት ወር መጀመር የነበረበትና አሁን ላልተወሰነ ጊዜ የተላለፈው የድንበር ማካለሉ ሥራ ሂደት እንዲንቀሳቀስ የብሪታንያ ጠቅላይ ሚንስትር ቶኒ ብሌር ለኢትዮጵያና ለኤርትራ መሪዎች በጻፉት ደብዳቤ ላይ፡ ሁለቱ ሀገሮች የኮሚስዮኑን ብያኔ አሣሪነት በመገንዘብ ውሳኔውን ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉበትን ውይይት እንዲጀምሩ፡ ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብም ይኸው ውይይት ይካሄድ ዘንድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ገልፀዋል። ኢትዮጵያ የኮሚስዮኑን ብያኔ ውድቅ በማድረግ ሌላ አማራጭ መፍትሔ እንዲፈለግ፡ ኤርትራም ኢትዮጵያ የኮሚስዮኑን ብያኔ እንድትቀበል ዓለም አቀፉ ኅብረተ ሰብ ግፊት እንዲያሳርፍባት ጥረት በያዙበት በዚሁ ወቅት፡ የድንበሩ ማካለል ተግባር ባለመጀመሩና ባካባቢውም ውጥረቱ እየተካረረ በመጣበት ሁኔታ ከሦስት ዓመት በፊት የተካሄደው ዓይነቱ አስከፊ ጦርነት ከዛሬ ነገ ይነሣ ይሆን በሚል ብርቱ ሥጋት ያደረበት በድንበሩ አካባቢ የሚኖረው የሁለቱ ሀገሮች ሕዝብ ይኸው አወዛጋቢ የድንበር ጥያቄ ለዘለቄታው ምን ዓይነት መፍትሔ ያገኝ ይሆን በሚል ጉዳዩን በጭንቀት መከታተሉን ቀጥሎዋል።