ኤድስ--እጅግ ከባድ የልማት መሰናክል | ኤኮኖሚ | DW | 24.06.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

ኤድስ--እጅግ ከባድ የልማት መሰናክል

አሁን ከየአግጣጫው እንደሚመለከተው፣ በአፍሪቃ፣ በከራይብና በፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች ውስጥ እጅግ ከባድ የልማት መሰናክል ሆኖ የሚታየው ጎልማሳውን የኅብረተሰብእ ከፊል የሚቀጨው ቀሳፊው በሽታ ኤድስና የኤድሱ ተሃዋሲ ነው። መንግሥታዊ ያልሆነውና ከ፪ሺ የሚበልጡ የአውሮጳ የልማት ተቋማትን የሚያስተባብረው “ኮንኮርድ” የተሰኘው የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ቡድን ባቀረበው መረጃ መሠረት፣ ዛሬ ከ፲፫ ሚሊዮን የሚበልጡ፣ በዕድሜ ከ፲፭ ዓመታት በታች የሆኑ ሕፃናት

ናቸው በዚያው በቀሳፊው በሽታ ኤድስ ምክንያት እናት፣ አባት ወይም ሁለቱንም አጥተው እጓለማውታን የሆኑት።


ይኸው የሰብዓዊ መብት ቡድን እንደሚለው ከሆነ፣ ከእነዚሁ እጓለማውታን መካከል ፹ በመቶ ያህሉ ከሰሓራ በስተደቡብ ባሉት የአፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ነው የሚገኙት። እንግዲህ፣ ከአውሮጳው ኅብረት ጋር በልማት ትብብር የተጣኣመሩት የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ(አከፓ) ሀገሮች ኤድስና የኤድስ ተሃዋሲ የሚፈጥረውን የኤኮኖሚና የልማት መሰናክል ለማስወገድ ይበቁ ዘንድ፣ የእጓለማውታኑን ብቻ ሳይሆን በቀላሉ ለአደጋ ሊጋለጡ የሚችሉትንም ሕፃናት ዕድል ለማቃናት ሰፊ ውዒሎተንዋይ መዘርጋት ይኖርባቸዋል። ዓለምአቀፉ ችግር ዓለምአቀፍ የልማት ትብብርን እንደሚጠይቅ የሚያስገነዝበው የሰብዓዊው መብት ጥበቃ ቡድን ኮንኮርድ በሚሰጠው መረጃ መሠረት፣ የኤድስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ስድሳ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ነው በተሃዋሲው የተያዘው፣ እስካሁን በኤድስ ሕመም ሕይወታቸውን ያጡት ፳ ሚሊዮን ናቸው። ሕይወትን ብቻ ሳይሆን ኤኮኖሚንም የሚያወድመው ጠንቀኛ በሽታ ከያዛቸው ሚሊዮኖች መካከል ከ፺፭ በመቶ የሚበልጡት፥ በሚደረጁት ሀገሮች ውስጥ ነው የሚገኙት።

ከጥቂት ሣምንታት በፊት የአውሮጳው ኅብረትና የአከፓ ሀገራት ሚኒስትሮች በጋቤሮኔ/ቦትስዋና ባካሄዱት በ፳፱ነኛው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ይኸው ጉዳይ በሰፊው ነበር የተወሳው። የዚሁ በሽታ መስፋፋት በሚያስከትለው ጠንቅ ከኅብረተሰቡ መካከል እጅግ ተጠቂ ሆነው የሚታዩት በተለይ ሕፃናት መሆናቸውን ያው ጉባኤ አስገንዝቧል። በያመቱ የሚዘጋጀው ያው የአውሮጳው ኅብረትና የአከፓ ሀገራት ጉባኤ የአውሮጳውን ኅብረት አባል-ሀገራት የልማት ሚኒስትሮችና የ፸፱ኙን የአፍሪቃ፣ የከራይብና የፓሲፊክ አካባቢ ሀገራት ሚኒስትሮች እያሰባሰበ ስለ ወቅታዊ የልማት ጥያቄዎች ያወያያል።

የኤድስ ተሃዋሲ የሚስፋፋበት ሂደት በብዙ ሀገሮች ውስጥ የሚገታበት ሁኔታ የጀመረ ሆኖ ቢታይም፣ በእጓለማውታኑ ላይ የሚያስከትለው መከራ በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ግብረሠናዩ ድርጅት ኮንኮርድ እንደሚለው፥ ለተጠቂዎቹ ሕፃናት ከለላ በመስጠት ረገድ ከባድ እንቅፋት የሚሆነው፣ እነርሱው የሚጓደልባቸው የፖለቲካው ግፊት ነው። የእንክብካቤው ጉድለት ለአደጋ የሚጋለጡት ሕፃናት የኋላ ኋላ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚሆኑበትን፣ የሚበዘበዙበትን፣ ለውትድርናም የሚዳረጉበትን መከራ ነው የሚያስከትለው። ይህንኑ ችግር ለመፍታት ይቻል ዘንድ፣ የአውሮጳው ኅብረትና አከፓ-ሀገሮች ስለሚወሰዱት ርምጃዎች አንድ የትብብር ሠነድ መፈራረማቸው ይታወቃል።

ከእነዚሁ ርምጃዎች አንዱ፥ እጎአ እስከ ፪ሺ፲፭ ድረስ የዓለም ድህነት በግማሽ እንዲቀነስ፣ የትምህርት ይዘትና የጤናጥበቃውም አገልግሎት እንዲሻሻል በተባ መ ዘንድ እጎአ በ፪ሺ ዓ.ም. የተተለመው የአሠርቱ ምእት ግብ ነው። ግን፣ የአውሮጳው ኅብረትና የአከፓ-ሀገሮች ከድህነት ጋር ስለተያያዙ በሽታዎች ባለፈው የካቲቲ አንድ የጋራ ምክርቤታዊ ጉባኤ ባካሄዱበት ወቅት እንደተገመተው፣ በሕፃናት ላይ የሚደርሰው የሞት አደጋ እንዲቀነስ፣ የእናቶች ጤና ጥበቃ አገልግሎት እንዲሻሻል፣ እንዲሁም በኤድስና በኤድስ ተሃዋሲ አንፃር የሚደረገው ትግል እንዲጠናከር የተተለሙት ሦሥቱ ግቦች እስከታሰበው ጊዜ(ማለት እጎአ እስከ ፪ሺ፲፭) ድረስ ሊደረስባቸው የሚችሉ መስለው አይታዩም። ያሁኑ ሂደት ከቀጠለ፣ ለሕዝብ ጤንነት ማሻሻያና ለፀረኤድስ ዘመቻ የሚመደበው ወጭ በመንማናነቱ ከቀጠለ፣ ጤንነትንና ኤድስን የሚመለከተው የአሠርቱ ምእት ግብ የሚተገበርበት ዕድል እንደማይኖር ነው የተመለከተው።

ስለዚህ፥ ግብረሠናዩ ድርጅት ኮንኮርድ እንደሚያስገነዝበው፣ የአውሮጳው ኅብረትና አከፓ-ሀገሮች ከድህነት ጋር የተያያዙ በሽታዎችን ለመታገል በሚነሱበት ጊዜ ለሴቶች፣ ለሕፃናትና ለሽማግሎች የተለየውን ትኩረት እንዲሰጡ አጥብቆ በማሳሰብ ላይ ነው የሚገኘው። ይኸውም፥ መንግሥታቱ ለእናቶች፣ ለሕፃናትና ለሽማግሎች ደኅንነት የሚያደርጉትን አገልግሎት በልማት መርሐግብራቸው ውስጥ እንዲያቀናብሩት አስፈላጊ ነው የሚሆነው። በኮንኮርድ አመለካከት መሠረት፣ በአውሮጳው ኮሚሲዮን በጀት ውስጥ አንድ ልዩ ሂሳብ ተመድቦ፣ ለኤድስ ሕሙማኑ ሕፃናት የሕግ ድጋፍና የጤና ጥበቃ አገልግሎት እንዲሰጥበት ተገቢ ሆኖ ነው የሚታየው። ግብረሠናዩ ድርጅት እንደሚለው፥ ይህ ካልተደረገ በስተቀር፣ በአከፓ-ሀገሮች ውስጥ ዘላቂውን ልማት ለማስገኘትና ድህነትን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት ሁሉ ከንቱ እየሆነ ነው የሚቀረው።

የተባ መ ጤና ጥበቃ ድርጅት አሁን ባቀረበው መረጃ መሠረት ደግሞ፥ አፍሪቃ ውስጥ አሁን ከምንጊዜውም ይበልጥ ያሠጋው የልጅነት ልምሻ የሚሰኘው የፖሊዮ በሽታ ክስተት ነው። ለዚሁ አሁን አንድ ምሳሌ ሆኖ የተጠቀሰው፣ ሱዳን ውስጥ በዳርፉር አካባቢ በሽታው የደረሰበት አንድ ሕፃን አካለ-ስንኩል የሆነበት ድርጊት ነው። ሀገሪቱ ውስጥ የተከሰተው ይኸው የልጅነት ልምሻ ከ፫ ዓመታት ወዲህ መጀመሪያው ነው። ከአንድ ዓመት በፊት በሽታው በ፫ ያፍሪቃ ሀገሮች ውስጥ ብቻ ነበር የተከሰተው፣ ዛሬ ግን እዚያው አፍሪቃ ውስጥ ፲፫ ሀገሮችን አዳርሷል ነው የሚባለው።

በተባ መ ጤና ጥበቃ ድርጅት ውስጥ ይህንኑ የልጅነት ልምሻ ለመግታት የሚጥሩት ጠበብት አሁን እንደሚያስገነዝቡት፣ የበሽታው ተሃዋሲ አፍሪቃ ውስጥ የሚስፋፋበት ፍጥነት በጣም አስደንጋጭ ሆኖ ነው የሚታየው። በእነዚሁ የዓለሙ ድርጅት ጠበብት ግምት መሠረት፣ በመጭው መፀው ይብሱን እንደሚስፋፋ የሚታሰበው ወረርሽኝ አእላፍ የአፍሪቃ ሕፃናትን ዕድሜ ሙሉ አካለ ስንኩል ሊያደርግ እንደሚችል ክፉኛ ነው የሚያሠጋው።

በሽታው አሁን በድንገት ሱዳን ውስጥ የተከሰተበት ሁኔታ፣ ያንኑ የሕፃናት ጤን’ነት ፀር እስከመጭው ዓመት መጨረሻ ድረስ ከመላው ዓለም ለማጥፋት የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት በሚያደርገው ትግል ረገድ አንድ እክል የደቀነ ሆኖ ነው የሚታየው። እስካሁን ድረስ በሽታው በብዛት የተከሰተው ናይጀሪያ ውስጥ ነበር። የሕፃናትን አካል የሚያሽመደምደው በሽታ እስካሁን ከተከሰተባቸው ሌሎቹ የአፍሪቃ ሀገሮች መካከል በተለይ በኒን፣ ቡርኪናፋሶ፣ ካሜሩን፣ ማዕከላዊት አፍሪቃ ሬፑብሊክ፣ ቻድ፣ ጋና፣ ኮትዲቯር እና ቶጎ ናቸው። እነዚሁ ሀገሮች በሙሉ ከፖሊዮ ነፃ ሆነዋል ተብለው ነበር ባለፉት ዓመታት፤ በሽታው አሁን እንደገና ማገርሸቱ ነው። በደቡባዊው የአፍሪቃ ከፊል የምትገኘው ሀገር ቦትስዋና ባለፈው የካቲት ነበር በሽታው እንደገና አዲስ መከሰቱን በይፋ ያስታወቀችው። በሽታው ገና ባልተወገደባቸው ግብጽ፣ ፓኪስታን፣ አፍጋኒስታን እና ሕንድ አሁንም የክትባቱ ዘመቻ እየተካሄደ ነው። ይኸው የክትባት ዘመቻ፣ የዓለም ጥና ጥበቃ ድርጅት እንደሚለው፣ በሽታው የሚስፋፋበትን ሂደት እስከመጭው ዓመት መጨረሻ ድረስ እንደሚገታው ነው ተሥፋ የተጣለበት።

ይኸው የተባ መ ጤና ጥበቃ ድርጅት የልጅነት ልምሻ/ወይም ፖሊዮ ከምድር ገጽ እንዲቀረፍ ለማድረግ ከ፲፮ ዓመታት በፊት፣ በ፲፱፻፹ ዓ ም ነበር መርሐግብሩን የዘረጋው። በዚያው ዘመን በሽታው በ፩፻፳፭ ሀገሮች ውስጥ ነበር ተሥፋፍቶ የተገኘው። ግን ከዚያ ወዲህ በአውሮጳ፣ በሰሜንና በደቡብ አሜሪካ፣ እንዲሁም በአውስትራሊያና በብዙ የእስያ አካባቢዎች መወገዱ፣ ዘመቻው መሳካቱ የተረጋገጠ ሆኖ ነው የቆየው። ዘመቻው በተጀመረበት ወቅት በየቀኑ ሺህ ሕፃናት ነበሩ በበሽታው የተያዙት። ባለፈው ዓመት በመላው ዓለም ውስጥ በበሽታው ከተያዙት ፮፻፸፯ ሕሙማን ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ናይጀሪያውያን ነበሩ።

እንግዲህ አፍሪቃ ውስጥ የሕይወትና የኤኮኖሚ ውድመት ምንጭ በሆነው ኤድስ አንፃር ከሚደረገው ትግል ጎን ፀረፖሊዮ ክትባቱም ዘመቻ መጠናከር እንዳለበት የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት ማስጠንቀቂያውን አጉልቷል።