1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኤኮዋስ እየከሰመ ይሆን?

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20 2016

የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ«ኤኮዋስ» የክፍለ አህጉሩን የኢኮኖሚ ዕድገትና መረጋጋት ለማረጋገጥ የተቋቋመ ድርጅት ነዉ። አንዳንድ አባላቱ ከህብረቱ መዉጣታቸዉ ኤኮዋስ እየከሰመ ነውን የሚል ጥያቄን አጭሯል። በቅርቡ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶና ማሊ ዉስጥ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ ከህብረቱ መውጣታቸው ይታወቃል።

https://p.dw.com/p/4inEs
የኢኮዋስ መሪዎች ከክልላዊ ቀውስ የሚወጡበትን መንገድ ማስተካከል ይችላሉ?
የኢኮዋስ መሪዎች ከክልላዊ ቀውስ የሚወጡበትን መንገድ ማስተካከል ይችላሉ?ምስል Kola Sulaimon/AFP/Getty Images

ኤኮዋስ እየከሰመ ይሆን?

ኤኮዋስ እየከሰመ ይሆን? 

የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ «ECOWAS» » የክፍለ አህጉሩን የኢኮኖሚ ዕድገትና መረጋጋት ለማረጋገጥ የተቋቋመ ድርጅት ነዉ። ግን አንዳንድ አባላቱ ከህብረቱ መዉጣታቸዉ ኤኮዋስ ቀስ በቀስ እየፈረሰ ነውን የሚል ጥያቄን አጭሯል።

በቅርቡ ኒጀር፣ ቡርኪናፋሶ እና ማሊ ከህብረቱ መውጣታቸውን ተከትሎ የምዕራብ አፍሪቃ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኤኮዋስ) ውዥንብር ውስጥ ገብቷል። በአሁኑ ወቅት በወታደራዊ አገዛዝ ስር የሚገኙት ሦስቱ የቀድሞ የኤኮዋስ አባል ሃገራት ፤ ከድርጅቱ ጋር  ያላቸውን ግንኙነት ካቋረጡ በኋላ ሃገራቱ ባለፈው መስከረምወር  የሳህል መንግስታት ጥምረት የሚባል አዲስ የፀጥታ ህብረትን መስርተዋል።

አገራቱ ከህብረቱ የመዉጣት ዉሳኔ የመጣዉ የኤኮዋስ የመርህ ርምጃን በመቃወም ነበር።ኤኮዋስ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደባቸዉን ሃገራትበማዉገዙ እና ማዕቀቦችን በመጣል ብሎም ወታደራዊ ጣልቃ እንደሚገባ ማስጠንቀቁን ተከትሎ ነበር። 

በወታደራዊ አገዛዝ ስር የሚገኙት ማሊ፤ ቡርኪናፋሶ እና ኒጀር አዲስ በመሰረቱት ህብረት ወታደራዊ ጥንካሬያቸዉን  ተጠቅመው ማንኛውንም የውጭ ጣልቃ ገብነትን እንደሚመክቱ ተናግረዋል።

የማሊ ወታደራዊ አገዛዝ አሲሚ ጉየታ
የማሊ ወታደራዊ አገዛዝ አሲሚ ጉየታ ምስል Francis Kokoroko/REUTERS

በምዕራብ አፍሪቃ አለመረጋጋት ተጠያቂው ማን ነው?

ሬሊ ሪስክ በተሰኘዉ ተቋም የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የፀጥታ ጉዳይ ተንታኝ የሆኑት ጋናዊዉ ፊዴል አማክዬ ኦውሱ እንደሚሉት  የኤኮዋስ አወቃር፣ ፖሊሲዎች እና መግባብያ ሰነዶች በአካባቢው ለተከሰቱ አለመረጋጋቶች ተጠያቂ ሊሆኑ አይችሉም የሚል እምነት አላቸዉ።

«የመፈንቅለ መንግስቶቹ ዋንና ምክንያትከኤኮዋስ በኩል የመጣ አይደለም። ይልቁንም ከጸጥታ ማጣት፣ ሰሜን ማሊ የነበረው ጽንፈኝነት፤ አካባቢው ላይ በመስፋፋቱ ነበር። ህብረቱ እነዚህን መፈንቅለ መንግሥቶች ለመከላከል አቅምም አልነበረዉም።»

የፀጥታ ጉዳይ ተንታኙ ፊዴል አማክዬ ኦውሱ፤ የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ፤ በሃገራቱ በታየዉ መፈንቅለ መንሥት ምላሽ መስጠቱን አስምረዉበታል። በህብረቱ መግባብያ ሰነዶች መሰረት ፤ በሃገራቱ የተካሄዱትን መፈንቅለ መንግሥቶች ማዉገዝ እና ማዕቀብ መጣልን ያጠቃልላል። ይሁን እና ባለፉት አራት ዓመታት የህብረቱ ይህ መርህ እና እርምጃ ፤ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱትን ሃገራት ያስደነገጣቸዉ አይመስልም። ተንታኙ እንደሚሉት የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ጉዳዩን በጥንካሪ አልያዘዉምም።  

«[ECOWAS] ሁኔታውን በጥንካሪ አልያዘዉም፤ እርምጃዉ ጥሩ አልነበረም። መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት ሃገራት ክስ እንደማይመሰረተባቸዉ ፤ ክትትል እንደማይደረግባቸዉ ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። ይህ በእርግጥ ህብረቱን ጥርስ የሌለው አንበሳ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት ነዉ፤ ማሊ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ ጥር ወር ከህብረቱ እንዲወጡ የመጨረሻ ምክንያት የሆነዉ። »

ECOWAS ባለፉት አራት ዓመታት ድርጅቱን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ በርካታ ማሻሻያዎችን ለማድረግ   ሲሞክር ቆይቷል፤ ህብረቱ ከደካማ ብሔራዊ መንግሥታት ጋር ይህን ራዕዩን ለማሳካት አልቻለም፤ የሕብረቱ ቁርጠኝነትም ደካማ ነው፤ ያሉት  በጋና አክራ በሚገኘው የጃቲካይ የደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኝ አዲብ ሳኒ ናቸዉ።

በኒጀር ከተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በኋላ
በኒጀር ከተካሄደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት በኋላምስል AFP

ኤኮዋስ ምን ችግር ገጠመዉ?

«ከአባል ሀገራት ቁርጠኝነት ማነስ የተነሳ ለህብረቱ ፈተና ሆኖ ቆይቷል። የኤኮዋስ የስኬት መጠን የሚወሰነው አባል ሀገራቱ ባሳዩት ቁርጠኝነት ነው፤ አልያም የኤኮዋስ ስኬት በአብዛኛው የሚመካው በመንግስታቱ ላይ ነው። ኤኮዋስ በድርጅቱ እና በምዕራብ አፍሪቃውያን መካከል በመተማመን እና በሙሉ ቁርጠኝነት መስራት አለበት። ነገርግን በብዙ መልኩ ኤኮዋስ  ህጋዊነቱን አጥቷል፣ ድርጅቱ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የፕሬዝዳንቶች ክለብ  እንጂ የብዙ ምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት ዜጎችን ፍላጎትን የሚንፀባርቅ አልሆነም።»

የፀጥታ ጉዳይ ተንታኙ ፊዴል ኦውሱ፤ በበኩላቸዉ በምዕራብ አፍሪቃ የመልካም አስተዳደር አስፈላጊነትን አፅኖት ሰጥተዋል። በአካባቢዉ ላይ መልካም አስተዳደር ያለመኖሩ ማሳያ፤ ዜጎች የመንግሥት ግልበጣ በተካሄደ ወቅት በደስታ ሲጨፍሩ ማየቱ አንዱ ማሳያ ነዉ ብለዋል።

የኢኮዋስ መሪዎች ድርጅቱ የገባበትን ኪሳራ በማሰብ ፤ በህብረተሰብ ዘንድ ያለዉን ተቀባይነት ለማጠናከር እና መልሶ ለመገንባት ተስፋን ሰንቀዋል።  በያዝነዉ ወር መጀመርያ ናይጄሪያ ላይ በተካሄደዉ የምዕራብ ሃገራት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ የመሪዎች ጉባኤ ላይ፤ መፍትሄ ለመፈለግ እና በአካባቢው መሪዎች መካከል ያለውን ያለመተማመን ለመፍታት ተስማምተዋል። ከቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር እና ማሊ ጋርም ውይይታቸውን ለመቀጠል እና ሃገራቱን ወደ ድርጅቱ መልሶ ለማምጣት እንደሚሰሩ ቃል ገብተዋል።

የኤኮዋስ አባል ሃገራት የመሪዎች ስብሰባ  በናይጄሪያ አቡጃ 2023
የኤኮዋስ አባል ሃገራት የመሪዎች ስብሰባ በናይጄሪያ አቡጃ 2023 ምስል Kola Sulaimon/AFP

ኤኮዋስ ቢከስም ሊከተል የሚችለዉ ውጤት

የምዕራብ አፍሪቃ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ «ECOWAS» » ብዙ ፈተናዎች ቢኖሩትም በምዕራብ አፍሪቃ የኢኮኖሚ እድገት እና የፖለቲካ መረጋጋትን ለመፍጠር እጅግ አዋጭ ህብረት እመሆኑን እንደሚያምኑ፤  የደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኙ ሳኒ ተናግረዋል። ድርጅቱ በምዕራብ አፍሪቃ ሃገራቱን በአንድ የኢኮኖሚ ጥላ ስር ለማዋሃድ” ከመፈለግ በተጨማሪ ECOWAS አሁንም አካባቢዉ ላይ የፀጥታ ሁኔታን  ወደነበረበት ለመመለስ” በተወሰነ ወታደራዊ ኃይል እንዳለዉ አክለዋል። እንደ ሳኒ ፤  ሴራሊዮን እና ላይቤሪያ በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የፀጥታ ችግር ሲገጥማቸው፤ ECOWAS ችግሮችን ለመቅረፍ ወታደሮቹን አሰማርቷል። "በእነዚህ ሀገራት እና በሌሎች ሃገራት የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ ኤኮዋስ ሰላም እንዲሰፍን ለዓመታት መስራቱን የደህንነት እና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኙ ተናግረዋል። 

አዜብ ታደሰ / አይዛክ ካሊጂ

እሸቴ በቀለ