«ኤኤፍዲ» እና መርሃ ግብሩ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 03.05.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

«ኤኤፍዲ» እና መርሃ ግብሩ

«አማራጭ ለጀርመን »የተባለው የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲ ባለፈው ቅዳሜና እሁድ ካካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ ይፋ ያደረገው መርሃ ግብሩ እዚህ ጀርመን ከየአቅጣጫው ትችቶች እየተሰነዘሩበት ነው ። የዛሬው አውሮጳና ጀርመን ዝግጅታችን ትችት የቀረበበትን የፓርቲው መርሃ ግብር ፣ እንዲሁም የፓርቲውን አነሳስና አካሄድ ያስቃኘናል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:58
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:58 ደቂቃ

«ኤኤፍዲ» እና መርሃ ግብሩ

አማራጭ ለጀርመን» በምህፃሩ AFD የተባለው ቀኝ ጽንፈኛው የጀርመን ተቃዋሚ ፓርቲ እድሜ ትንሽ ቢሆንም የጀርመንን የፖለቲካ መድረክ በተቀላቀለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ያገኘው ውጤት ግን የሚናቅ አይደለም ። ምናልባት ፓርቲው ሲመሰረት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለው የገመቱ ካሉ እጅግ ጥቂቶች ሊሆኑ ይችላሉ ።የዛሬ ሦስት አመት የተቋቋመው ይኽው ፓርቲ በአሁኑ ጊዜ ከ16ቱ የጀርመን ፌደራል ክፍላተ ሃገር በ8ቱ የፓርላማ መቀመጫዎች አግኝቷል ። ፓርቲው በጎርጎሮሳዊው 2013 ሲመሰረት ዓላማው ጀርመን የዩሮ ተጠቃሚ አባል ሃገር መሆንዋን ማስቀረት ነበር ። ይሁንና ባለፈው ዓመት ፀረ-የውጭ ዜጎች አጀንዳዎችንም ማካተት ሲጀምር መሥራቹ ቤርንድ ሉከ ከፓርቲው ከተሰናበቱ በኋላ የዘመቻውን ትኩረት መንግሥት የሚከተለውን የስደተኞች ጉዳይ ፖሊሲ በመቃወም ላይ አደረገ ። በርካታ ስደተኞች ወደ ጀርመን በገቡበት ባለፈው አመት፣ ጀርመን የድንበር ቁጥጥር እንድትጀምርም አጥብቆ መሟገት ጀመረ ። በየጊዜው አዳዲስ አጀንዳዎችን የሚያነሳው ይኽው ፓርቲ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው ደግሞ ሌሎች አወዛጋቢ ጉዳዮችን ያካተተበትን መርህ ግብሩን ይፋ አድርጓል ። የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤል እንደሚለው መርሃ ግብሩ በአመዛኙ የውጭ ዜጎች ጥላቻ

የተንፀባረቀበት ነው ። ከመካከላቸው ዋና ዋናዎቹም የሚከተሉት ናቸው ።
ከዚህ ሌላ AFD በፕሮግራሙ ዋና ዋና በሚባሉ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ የሃሐገሪቱ ጉዳዮች ላይ የጀርመን ፓርላማ ውሳኔ ከሚሰጥ ይልቅ ህዝበ ውሳኔ እንዲካሄድም ጠይቋል ።
የአራት ሚሊዮን ሙስሊሞች መኖሪያ በሆነችው በጀርመን AFD በፓርቲ ፕሮግራሙ «እስልምና የጀርመን አካል አይደለም » ማለቱ ከጀርመን ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ትችት ተሰንዝሮበታል ። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚመሩት የክርስቲያን ክርስቲያን ዴሞክራት ፓርቲ ፣ AFD ያሳለፈውን ውሳኔ በሁሉም ሃይማኖቶች ላይ የተሰነዘረ ጥቃት ብሎታል ። ሜርክል የጀርመን ህገ መንግሥት ለሃይማኖት ነፃነት ዋስትና የሚሰጥ መሆኑን እስልምናም የጀርመን አካል እንደሆነ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል ። የፓርቲው ምክትል ሊቀ መንበር አርሚን ላሼት በጀርመን እስልምናን ባዕድ አካል ያደረገው የፓርቲው ውሳኔ ከፋፋይና «እምነት ትርጉም አለው» ለሚለው ለፓርቲያቸው አስደንጋጭ መሆኑን ገልፀዋል ።የAFD ፍላጎትም አሁን በግልፅ ሊታወቅ መቻሉንም አስገንዝበዋል ።
«AFD የሚፈልገውን በግልፅ በጥቁር እና ነጭ ጠረጴዛ ላይ አስቀምጧል ። ፓርቲው ሌላ ጀርመን ነው የሚፈልገው ። ያ

ጀርመን ግን የኮናርድ አደናወርና የሄልሙት ኮል ፣የጀርመን ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አይደለም ።»
የአረንጌዴዎቹ ፓርቲም የAFDን ፕሮግራም አድሃሪና የህብረተሰቡን ለመከፋፈል ያለመ ነበር ያለው። በጀርመን የሙስሊሙ ማህበረሰብ መሪዎችም ከአጠቃላዩ የጀርመን ህዝብ 5 በመቶው ሙስሊም በሆነበት በህብረተሰቡ ውስጥ ፀረ እስልምና አስተሳሰብ ለመንዛት የሚደረገውን ሙከራ አውግዘዋል ። ከመካከላቸው ጀርመን የሚኖሩ ሙስሊሞች ምክር ቤት ሊቀ መንበር አይማን ማትስዬክ ይገኙበታል ።
በሙስሊሞች ላይ ጥላቻው ከየት እንደመጣ እንጠይቃለን ። በዚህ የተነሳም ነው ነገሮችን በቅጡ ሳይረዱ ድምዳሜ ላይ የሚደርሱት ።ልንገምት የምንችለው ስለ ሙስሊሞች ምንም ዓይነት ልምድ እንደሌላቸው ነው ።በሃገራችን በእስልምና ላይ ጥላቻን በመንዛት ጉዳዩን የፖለቲካ መጠቀሚያ ሊያደርጉት እየሞከሩ ነው ።»
AFD የተቋቋመው የዛሬ ሦስት አመት ቢሆንም ቡድኑ የተጠነሰሰው ግን ከዛሬ 14 ዓመት በፊት የጀርመን መገበያያ ገንዘብ ማርክ በጋራው ሸርፍ ዩሮ ከተተካ በኋላ ነው ።በወቅቱ ጉዳዩ ያሳስበናል ያሉ የኤኮኖሚ ምሁራንና ጋዜጠኞች እንዲሁም ከዋና ዋናዎቹ ፓርቲዎች በተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉ አባላት ዩሮ የጀርመን መገበያያ ገንዘብ መሆኑን በመቃወም መሰባሰብ

ጀመሩ።እነዚሁ ወገኖች የዛሬ ሶስት አመት በአውሮጳ የገንዘብ ቀውስ ከተከሰተ በኋላ ጉዳዩን አጠናክረው ብቅ አሉ ። ምክንያታቸውም በነዚህ ሃገራት የደረሰው ችግር መዘዝ ለኛም እንዳይተርፍ እንከላከል የሚል ነበር ።
በየጊዜው አዳዲስ ጉዳዮችን የሚያነሳው AFD በ6 የጀርመን ፌደራል ክፍላተ ሃገር የፓርላማ መቀመጫዎች መያዙ ከዚህ ቀደም ፈፅሞ የሚታሰብ አልነበረም ። በተለይ ከሁለት ወር በፊት በተካሄዱ አካባቢያዊ ምርጫዎች ፓርቲው ያገኘው ውጤትም ፍፁም ያልተጠበቀ ነበር ። እንደገና ይልማ
በዚህ መልኩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ በመሄድ ላይ ያለው AFD በመጪው የጀርመን አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ላይ ተፅእኖ ማሳደሩ እንደማይቀር ይገመታል ።ፓርቲው በተለይ የህዝቡን ስሜት ሊኮረክሩ ይችላሉ በሚላቸው ጉዳዮች ላይ የሚከፍተው ዘመቻ በዘልማድ ድምጽ ለመስጠት የማይወጣውን የህብረተሰብ ክፍል ለመያዝ እንዳበቃው ይነገራል ።ይህም በመጪው ምርጫ በጀርመን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ የማግኘት እድሉን ያሰፋዋል የሚል ግምት አለ ።

ኂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic