«ኤች አይ ቪ ኤይድስ» ና መለስተኛው የመከላከያ ክትባት፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 30.09.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

«ኤች አይ ቪ ኤይድስ» ና መለስተኛው የመከላከያ ክትባት፣

«ጦርነቱ፣ ሁላችንም ጎበዝ ተዋጊዎች እንድንሆን ይጠብቃል!።» ይህን ያለችው፣ ሚላን ኢጣልያ ውስጥ ከትናንት በስቲያ ማታ በተደረገ አንድ ልዩ ዝግጅት ተገኝታ፣

default

31,2% ብቻ መሳካቱ የተነገረለት በታይላንድ የተሞከረው፣ ጸረ ኤይድስ ክትባት፣

ከ አንድ ሚልዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንዲገኝ ያበቀችው የእጅግ ታዋቂው የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ እኅት፣ ታዋቂዋ ፖፕ ሙዚቀኛ ጃኔት ጃክሰን ናት።
በዚያ ምሽት እርሷና ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች የፈረሙበት አንድ ጃኬት 36,000 ዩውሮ ሲሸጥ፣ ባለፈው ዓመት ሰኔ 18 ቀን 2001 ዓ ም፣ በ 50 ዓመቱ ላረፈው የፖፕ ሙዚቃ ንጉስ ማይክል ጃክሰን ከማስጌጫ የከበሩ ድንጋዮች ጋር በእጅ የተሠራውና ፣ ማይክል አንድም ቀን ሳይጫመተው ተቀምጦ የነበረ አንድ ጫማም በ 10,000 ዩውሮ ተሸጧል።

እ ጎ አ ከ 1981 ዓ ም አንስቶ በይፋ የታወቀው፣ ሰውነት፣ በሽታ የሚያስከትሉ ተኀዋስያንን የሚከላከልበትን አቅም አዳክሞ፣ ሠራ አካላትን አሰልስሎ ለኅልፈተ ህይወት የሚዳርገው Aquired Immune Deficiency Syndrome (AIDS)ባልታሰበ ፍጥነት ነው በመላው ዓለም የተዛመተው። ምንጩ፣ በትክክል ከምን እንደሆነ ያልታወቀው፣ ባለፉት 25 ዓመታት ውስጥ የ 25 ሚሊዮን ህዝብ ህይወት የቀጠፈው፣ በአሁኑ ጊዜም ፣ 33 ሚሊዮን ሰዎች የዚሁ አደገኛ የጤና ጠንቅ የሆነ ተኀዋሲ ምርኮኞች እንዲሆኑ ያደረገው ኤች አይ ቪ ኤይድስ፣ እውን ፍቱን መድኀኒት ተገኝቶለታል? ባለፈው ሐሙስ ፣ እስያዊቷ ሀገር ታይላንድ ፣ 31,2 ከመቶ አስተማማኝ የሆነ ክትባት አግኝቼአለሁ ማለቷ ፣ በእርግጥ የቱን ያህል አስተማማኝ ነው? አድማጮቻችን የዛሬው ሳይንስና ኅብረተሰብ ቅንብራችን ዋና ትኩረት፣ በዚሁ ኤች አይ ቪ ኤይድስ ምርምር ዙሪያ ይሆልን ፣ አብራችሁን ቆዩ።

ሬዮንግ በተሰኘው የደቡብ ታይላንድ ክፍለ ሀገር ፣ 16,402 ሰዎች ራሳቸውን ለምርምር መፈተሻ ዝግጁ በማድረግ ሲተባባሩ የቆዩ ሲሆን ፣ የአገሪቱ

ጤና ጥበቃ ሚንስትር፣ ዊትሃያ ኬውፓራዴይ፣ በአገራቸውና በዩናይትድ እስቴትስ ተማራማሪዎች ትብብር የተካሄደው የ 6 ዓመት ምርምር፣ አዎንታዊ ውጤት አስመዝግቧል ነው ያሉት።

ቪትሃያ ኬውፓራዴይ-----

«የምርምሩን ውጤት በተመለከተ ዛሬ ማለት የምንችለው፣ የክትባቱ መድኀኒት፣ የተኀዋሲውን መዛመት በ 31,2 ከመቶ እንደሚቀንሰው ነው። ነገር ግን፣ በደም ውስጥ የተኀዋሲ ክምችትን ገና እንዲቀነስ የሚያደርግ አይደለም»።

የሚንስትሩ፤ የመሥሪያ ቤት ባ ልደረባ ዶ/ር ሱፓቼ ሬርክስ-እንጋርም በበኩላቸው፣ ስለምርምሩ ውጤት እንዲህ ነበረ ያስረዱት።

«ውጤቱ እንዳሳየው፣ ክትባቱ 31,2 ከመቶ ፍቱን ሲሆን፤ ካልተከተቡ ሰዎች ይልቅ የተከተቡት ተኀዋሲውን መቋቋም እንደሚችሉ ተረጋግጧል። ይህ በሳይንስ ረገድ ዐቢይ እመርታ ነው። ክትባት፣ በተከተቡ ሰዎች መካካል ተኀዋሲ ሊዛመት እንደማይችል ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠ ሆኗል። ይህ ደግሞ ወደፊት ለመከላከል የሚበጅ፣ ተጨማሪ ክትባት ለማዘጋጀት አንድ እመርታ ነው።»

የአንድ ጊዜው ፀረ ኤይድስ ክትባት የሚያገለግለው ለ 3 ዓመት ነው።

በአንድ የማኅበረሰብ አባላት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰፊው ሙከራ ሲካሄድ፣ የደቡብ ታይላንዱ ፣ በዓለም ውስጥ፣ የመጀመሪያው መሆኑ አልታበለም። ለዚህ የክትባት ሙከራም ሆነ ምርምር ፣ ባለፉት 6 ዓመታት በአጠቃላይ 123 ሚሊዮን ዶላር ነው ወጪ የተደረገው ። በበጎ ፈቃደኛነት ራሳቸውን ለመሞከሪያ ያዘጋጁት ዕደሜአቸው በ 18 እና 30 ዓመት መካከል ሲሆን፣ በ ኤች አይ ቪ ኤይድስ፣ እጅግ የመጠቃት ፈተና የሚያጋጥማቸውም በዚሁ የዕድሜ እርከን የሚገኙት ወጣቶችና ጎልማሶች መሆናቸው የሚያጠራጥር አይደም። ከ 16 ሺው መካከል ገሚሱ ፣ ክኒን (እንክብል) የተቀሩት 8 ሺ ገደማው ደግሞ የክትባት መርፌ ነበረ የሚወጉት። እናም ውጤቱ እንዳሳየው፣ እንክብል ከተሰጣቸው መካከል 74 ከመቶው በኤች አይ ቪ ሲያዙ፣ ሁለት መድኀኒቶች የተቀላቀሉበትን ክትባት ያገኙት 51 ከመቶ ብቻ ነው ተኀዋሲው ሊሸጋገርባቸው የቻለው።

ይህን በመሰለውን አስቸጋሪ የኤች አይ ቪ ተኀዋሲን የመታገል ምርምር በኅብረት ያካሄዱት ፣ የታይላንድ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር፣ የትምህርት ተቋማት፣ እንዲሁም፣ የመንግሥት ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸው። ታይላንድ ለ ኤች አይ ቪ ኤይድስ መከላከያ የሚሆን ክትባት ፍልጋ ባደረገችው ምርምር መወደሷ አልቀረም። ከ 5 ዓመት በፊት ሙከራውን መካሄድ በተጀመረ በዓመቱ 22 ዕውቅ አሜሪካውያን ሳይንቲስቶች፤ ውጤት የሚገኝበት አይደለም በማለት ከመንቀፋቸውም፣ የዋሽንግተን አስተዳደር ለዚህ ውጤት ለማያመጣ ምርምር ለምን ከ 100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ሰጠ? ሲሉ እስከመክሰስ ነበረ ርቀው የሄዱት፣ ይሁንና 6 ዓመታት የወሰደው ምርምር ከንቱ ሆኖ አለመቅረቱን በመጨረሻ ለማሳዬት በቅቷል።

ከክትባት መድኀኒቶቹ መካከል አንደኛውን ፣ ያዘጋጀው Sanofi Pasteur የተባለው የመድኀኒት ፋብሪካ ነው። የክትባቱ መድኃኒት አዲስ ሳይሆን፣ የሳኖፊ-ፓስተር፣ ALVAC canarypox/HIV እና ፣ የ AIDSVAX ፣ የሁለት መድኃኒቶች ቅልቅል ነው። ፣ AIDSVAX ሳን ፍራንሲስኮ ፣ ዩናይትድ እስቴትስ በሚገኘው VaxGen በተሰኘው ኩባንያ፣ ለክትባት ቀደም ባለው ጊዜ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በተናጠል ውጤታማ ሆኖ የተገኘ አልነበረም።

በእስያና ሰላማዊው ውቅያኖስ አካባቢ አገሮች፣ የዚህ ኩባንያ የምርምርና ዕድገት ጉዳይ ኀላፊ አለን ቡከኑግ፣ በክትባት ነል ምርምር፣ ባለፉት ዓመታት ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተው አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ አዎንታዊ ውጤት የመመዝገቡ ዜና መስተጋባቱ እሰዬው የሚያሰኝ ነው ባይ ናቸው።

በታይላንድ የዩናይትድ እስቴትስ አምባሳደር ኤሪክ ጅ ጆን፣ በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ተስፋ አስጨባጭ ውጤት መገኘቱ ቢታወቅም፣ ኤች አይ ቪ ኤይድስን ገና ፈጽሞ መግታት አልተቻለም ነው ያሉት።

«በዓለም ዙሪያ፣ ብዙዎች መንግሥታት ፣ እስካሁን ከኤች አይ ቪ -ኤይድስ ጋር ሥርጭቱን ለመግታት በመታገል ላይ ናቸው። ዩናይትድ እስቴትስንና ታይላንድን በመሳሰሉ አገሮችም ቢሆን፣ ኤይድስ እንደገና በሰፊው በመሠራጨት ድቀት ሊያስከትል ይችላል። ይህን አስፈሪ በሽታ ለመታገል ፣ ትልቁ ተስፋችን ጸረ-ኤች አይ ቪ ክትባት ማግኘት ነው።»

በእስያ፣ ከ 5 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ከ ኤች አይ ቪ ተኀዋሲ ጋር የሚኖር ነው። የተባበሩት መንግሥታት የጤና ጥበቃ ድርጅት እንደሚለው ከሆነ፣ በዓለም ዙሪያ በየዕለቱ 7,500 ሰዎች በተኅዋሲው መተላለፍ ይጠቃሉ። ከ 2 ዓመት በፊት ብቻ ፣ ኤይድስ 2 ሚሊዮን ሰዎች ገድሏል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ ታይላንድን ካምቦዲያንና ምያንማርን በመሰሰሉ አገሮች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ የኤይድስን መሥፋፋት ለመግታት የተቻለ ሲሆን፣ በኢንዶኔሺያ፣ ፓኪስታንና ቪየትናም ግን እየተዛመተ በመሄድ ላይ ነው። እርግጥ ነው ፣ ታይላንድ ኤች አይ ቪ ኤይድስ ያለባቸው 610,000 ያህል ዜጎች እንዳሏት የታወቀ ነው። እ ጎ አ ከ 1981 ዓ ም ወዲህ ከኤይድስ ጋር በተያያዘ በሽታም 400,000 ተወላጆችዋ ህይወታቸውን አጥተዋል።

በዓለም ውስጥ፣ 75 ከመቶው (¾ኛዎቹ) የኤች አይ ቪ ኤይድስ ሰለባዎች የሚገኙት

ከሰሐራ በስተደቡብ ባሉ የአፍሪቃ አገሮች ነው። እ ጎ አ በ 2007 ዓ ም፣ በኤይድስ ሳቢያ በዓለም ዙሪያ ህይወታቸውን ካጡት መካከል 75 ከመቶውም አፍሪቃውያን እንደነበሩ አልታበለም።

HIV-AIDS አንድ ቀን ምናልባት ፍቱን የክትባት መድኃኒት ይገኝለት ይሆናል። ዋናውና ምንጊዜም አስተማማኙ ክትባት ግን በወሲባዊ ህይወት ፍጹም የማያወላዳ የባኅርይ ለውጥ ማድረግ ፣ ማለት አንድ- ለአንድ፣ ፍንክች በማይል፣ የእርስ- በርስ ታማኝነት ተወስኖ መኖር ነው። ይህን ማሟላት የሚሳናቸው ደግሞ ፤ Condom በሚባለው ሰው-ሠራሽ መከላከያ፣ ምንም ቢሆን መቶ በመቶ ሊተማመኑ አይችሉም።

ተክሌ የኋላ፣

አርያም ተክሌ፣